በመጀመሪያው አጋማሽ እጅግ ማራኪ እግር ኳሰን በሁለቱም በኩል ተመልክተናል ።አብይ አካዳሚዎች በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃ ብልጫ በመውሰድ ጫና ቢፈጥሩም ጎል ማስቆጠር ግን አልቻሉም በአንፃሩ ምስራቆችም በመልሶ ማጥቃት ጎል ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም የአብይ አካዳሚ ተከላካዮችን ማለፍ አልቻሉም ።
ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ምስራቆች በቢንያም ባንጫ የሚመራው የመሐል ሜዳው ክፍል ጨዋታውን በሚገባ በመቆጣጠር በተደጋጋሚ ጎል ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል ።በተደጋጋሚ ያገኛቸውን የጎል አጋጣሚዎችን መጠቀም ሳይችል የቀረው ታምራት ዋና የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ግሩም ጎል አስቆጥሮ የመጀመሪያው አጋማሽ በምስራቆች አንድ ለባዶ መሪነት ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ ሀይላቸውን ወደ ማጥቃት የቀየሩት አብይ አካዳሚዎች በተደጋጋሚ ወደ ጎል ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት በምስራቅ ተከላካዮች ይጨናገፍባቸው ነበር።ምስራቆችም በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ጎል ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት ሳይሳካለቸው ቀርቷል።
አብይ አካዳሚዎች በረጅሙ ለኮርግንግ የጣሉትን ኳስ ግብ ጠባቂው ጠልፎ ጥሎታል በማለት የመሐል ዳኛው የሰጡትን ፍፁም ቅጣት ምት አብይ አካዳሚዎች አስቆጥረው አንድ አቻ ሆኑ።
- ማሰታውቂያ -
ከጎሉ በኋላ ረጃጅም ኳሶችን ለኮርግንግ መጣል የጀመሩት አብይ አካዳሚዎች የምስራቅ የመሐል ተከላካይ ኮርግንግ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ እንዲሰናበት አድርጓል።
መደበኛው ጨዋታ በአንድ አቻ ተጠናቆ ወደ ፍፁም ቅጣት ምት አምርተው የሲዳማ ክልል ተወካዩ ምስራቅ ክ/ከተማ አራት ለሁለት በማሸነፍ ወደ ፍፃሜ አልፏል።
ሌላኛውን የፍፃሜ ተፋላሚ ለመለየት በተደረገ ጨዋታ ዱራሜ ከነማ እና ቡሳ ከነማን ሁለት ለባዶ አሸንፏል።
ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው የሁለቱ ጨዋታ ብዙም ሳቢ አልነበረም ።ከደቂቃዎች በኋላ ወደ ጨዋታ የተመለሱት ሁለቱ ቡድኖች በተደጋጋሚ ወደ ጎል መድረስ ቢችሉም ጎል ማስቆጠር ግን አልቻሉም።
በተደጋጋሚ የቡሳ ከነማን የግብ ክልል ሲፈትሹ የነበሩት የዱራሜ ከነማ ተጫዋቾች በመጨረሻ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ ጎል ማስቆጠር ችለዋል።ከቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲተፋው በውድድሩ ከተካላካይ መስመር እየተነሳ ሶስት ጎሎችን ያስቆጠረው በፋ ጎሉን አስቆጥሯል ።
ከጎሏ በኋላ ጨዋታውን የተቆጣጠሩት ዱራሜ ከነማዎች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ብዙም ደቂቃ አልፈጀባቸውም ።ከመሐል ሜዳ መሬት ለመሬት የተሰጠውን ኳስ በኮከብ ጎል አግቢነት እየተፎካከረ የሚገኘው ሀይሌ አለሙ የውድድሩን ድንቅ ጎል ማስቆጠር ችሏል ።ሀይሌ አለሙ ጎሏን ከማስቆጠሩ በፊት ከጓደኛው ኳሷን የቀበለበት መንገድ እና ተጫዋቹን ያለፈበት ሁኔታ ከብዙዎች አድናቆት ተችሮታል። የመጀመሪያው አጋማሽም በዱራሜ ከነማ ሁለት ለባዶ መሪነት ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ተሽለው መቅረብ የቻሉት ቡሳ ከነማዎች በተደጋጋሚ ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል ።በአንድ ሁለት ቅብብል በተደጋጋሚ ወደ ዱራሜ ከነማ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም የሚያገኙትን አጋጣሚዎች ግን መጠቀም አልቻሉም ።
በአንድ አጋጣሚ በመልሶ ማጥቃት ያገኙት አጋጣሚ የዱራሜን ሁለት ተከላካይ ለአራት ቢያገኙም በአግባቡ መጠቀም ግን አልቻሉም ።ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሞከሩት ዱራሜዎች በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ጎል ለመድረስ ቢሞክሩም መጨረሻ ላይ ይቋረጥባቸው ነበር ።ለአጥቂው ሀይሌ አለሙ በረጅም የሚሰጡት ኳሶችም ሲባክኑ ተመልክተናል።
የዱራሜ ከነማ የፊት መስመር ተጫዋቹ ሀይሌ አለሙ ዛሬ ባሳየው ድንቅ እንቅስቃሴ ከደጋፊዎች አድናቆት ተችሮታል።በመጨረሻም ጨዋታው በዱራሜ ከነማ ሁለት ለባዶ አሸናፊነት ተጠናቋል።
ዱራሜ ከነማ ሀሙስ በሚደረገው የፍፃሜ ጨዋታ ላይ አብይ አካዳሚን በፍፁም ቅጣት ምት ያሸነፈውን ምስራቅ ክ/ከተማን ይገጥማል።