“ተወዳጅነትን ካተረፍኩበት ኢትዮጵያ ቡና መለየቴ ስሜቱ ከባድ ሆኖብኛል”
“በሀድያ የተሳካ ጊዜን ለማሳለፍ ዝግጁ ነኝ”
እያሱ ታምሩ /ሀድያ ሆሳዕና/
“በኢትዮጵያ ቡና ያለፉት ስድስት ዓመታት ቆይታዬ በአብዛኛው ጥሩና ደስ የሚሉ ጊዜያቶችን ነው ያሳለፍኩት፤ ከእነዚህ ወቅቶች በኋላም የውል ጊዜዬ በመጠናቀቁ ምክንያት ከክለቡ ጋር የምቀጥልበት ዕድሉ ስላልነበረኝና የእግር ኳስ ጨዋታ ደግሞ እንጀራዬና ስራዬም ስለሆነ በጣም የምወደውን ቡድን ተለያይቼ ወደ አዲሱ ቡድኔ ሀድያ ሆሳዕና አምርቼያለው”። ካለ በኋላ በዚህ ቡድን ውስጥ በነበረኝ ቆይታም ከዚህ ታላቅና ተወዳጅ ቡድን ጋር ለአንድም ጊዜ ቢሆን እንኳን የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት ፈልጎ ይኸውን ዕድል ሊያሳካ ባለመቻሉና ከቡናም ጋር በመለያየቱ በጣም እንደሚቆጨው ከሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር በነበረው አጠር ያለ ቆይታው አስተያየቱን ሰጥቷል።
በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኑ ለትውልድ አካባቢው ክለብ ወሊሶ ከተማና በኋላም ላይ ለሀላባ ከተማ ተጫውቶ ካበቃ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ቡና አምርቶ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴም ሆነ ባለው መልካም ባህሪው በአጠቃላይ የክለቡ ደጋፊና የቡድኑ ተጨዋቾች ብሎም ደግሞ አመራሮች ዘንድ በጣሙን የሚወደደውን ይኸውን ተጨዋች ከቡና ጋር ከተለያየ በኋላ በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ አናግረነው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቶናል።
ሀትሪክ፦ ኢትዮጵያ ቡናና እያሱ ታምሩ ከስድስት ዓመታት ቆይታ በኋላ ተለያዩ፤ በዚህ ዙሪያ ምን ትላለህ?
እያሱ፦ የኢትዮጵያ ቡና ያለፉት ስድስት ዓመታት ቆይታዬ ለእኔ በጣም ጥሩና መልካም ጊዜያቶችንም ያሳለፍኩባቸው ስለነበሩ የውል ጊዜዬ መጠናቀቁን አስመልክቶ ከክለቡ ጋር የምቀጥልበት ዕድሉ ስላልነበረኝና ኳስ ጨዋታ ደግሞ እንጀራዬና ስራዬም ስለሆነ ከዚህ ታላቅ ቡድን ጋር ለአንድም ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ሳላነሳ በመለያየቴ በጣም ነው ያዘንኩት፤ በጣምም ነው የተከፋሁት።
ሀትሪክ፦ በኢትዮጵያ ቡና የነበረህ ቆይታ በቋሚ ተሰላፊነት የተጫወትክባቸውና አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ወደ ቡድኑ ከመጣ በኋላ ደግሞ በተጠባባቂነት የቆየክባቸው ናቸውና ይህን በተመለከተስ ምን የምትለው ነገር አለ?
እያሱ፦ በመጀመሪያ ደረጃ ከሀላባ ከተማ ወደ ቡና ካመራሁበት ጊዜ ጀምሮ ለእዚህ በብዙዎች ዘንድ ለሚደገፍና እኔም ከፍተኛ ፍቅርን ላገኘሁበት ተወዳጅ ቡድን የራሴን አንድ አሻራ ማሳረፍ አለብኝ በሚል በቋሚ ተሰላፊነት በተጫወትኩባቸው ጊዜያቶች አቅሜንና ጉልበቴን ሳልቆጥብ በጥሩ መልኩ ከእኔ የሚጠበቀውን ሚና ልወጣ ችያለሁ። አዲሱ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ወደ ቡድኑ ከመጣም በኋላ ደግሞ ምንም እንኳን በቋሚ ተሰላፊነት የመጫወት ዕድሉ ቢነፈገኝም ሁሌም ግን በልምምድ ሰዓት ላይ እንደ አንድ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋች ለቀጠረኝ ክለብ ስራዬን በአግባቡ በመስራትና አሰልጣኙም ለሚከተለው አጨዋወት ተገዢ በመሆንና ስራውንም በሟሟላት የተጓዝኩባቸው አጋጣሚዎችም ስለነበሩ በእዚሁ ሁኔታ ነው ከቡና ጋር ያሳለፍኩት።
ሀትሪክ፦ ለአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ አጨዋወት ተገዥ ነበርኩ፤ ልምምዱንም በአግባቡም አሟልቼ እሰራ ነበር ካልክ እንዴት ታዲያ እሱ ወደ ክለቡ ካመራ ጀምሮ በቋሚ ተሰላፊነት ላትጫወት ቻልክ?
እያሱ፦ ይሄ እንግዲህ የአሰልጣኝ ውሳኔ ነው። እኔ ተጨዋች ነኝ። ተጨዋች ስለሆንኩም ያልተሰለፍኩበትን ምክንያት ትክክል አይደለም ብሎም ለመናገር ሞራሉ አይኖረኝም። በቡና ቆይታዬ የአሰልጣኜን ውሳኔና ስራ ማክበር ስለነበረብኝ በዛ ውስጥ ሆኜ መልካም ጊዜያቶችን አሳልፌያለሁ። ከአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ጋርም መልካም ግንኙነትም ነበረኝ። በእሱ ስር ሆኜ ያልተሰለፍኩትም አሰልጣኙ ለእኔ ይሆኑኛል የሚላቸውን አስራ አንድ ተጨዋቾችን ወደ ሜዳ ስላስገባና ከእነዛ ውስጥ አንዱ ደግሞ እኔ ስላልሆንኩኝ ነው ለቡና በእሱ ጊዜ በቋሚ ተሰላፊነት ያልተጫወትኩትና በእኔ አለመሰለፍ ዙሪያ ትክክለኛውን ምላሽ ሊሰጣችሁ የሚችለው እሱ ብቻ ነው።
ሀትሪክ፦ ከኢትዮጵያ ቡና መለያየት ስሜቱ ከባድ ነው?
እያሱ፦ በጣም! ግን እንደ ራስህ ይወሰናል። ለእኔ በጣም ነው ከባድ የሆነብኝ። በዚህ ቡድን ቆይታዬ ከሁሉም ጋር ነበር መልካም ግንኙነት የነበረኝ። በተለይም ደግሞ ደጋፊውና ተጨዋቾቹ የሚሰጡኝ ያላሰለሰ ፍቅር ሁሌም ቢሆን ከአህምሮዬ አይጠፋምና ከምወደው ቡድን ጋር መለያየቴ ቆጭቶኛል።
ሀትሪክ፦ ወደዚህ ቡድን ዳግም የምትመለስ ይመስልሃል?
እያሱ፦ ዛሬ ላይ ሆኜ በእዚህ ጉዳይ ዙሪያ መልስ ለመስጠት እቸገራለሁ። ሁሉንም ነገር ፈጣሪም ነው የሚያውቀው። አሁን ላይ ግን እኔ የአዲሱ ቡድኔ የሀዲያ ሆሳዕና ተጨዋች ነኝ። ከዚህ በኋላም ለቀጠረኝ ክለብም ነው ምርጥ ግልጋሎትን በመስጠትና ክለቡንም ለተሻለ ውጤት በማብቃት በቡና ውስጥ የነበረኝን የቀድሞ ስምና ዝናን ዳግም መመለስ የምፈልገውና ለዛም ከወዲሁ ራሴን እያዘጋጀው ነው።
ሀትሪክ፦ በኢትዮጵያ ቡና በነበረህ ቆይታህ በደጋፊው፣ በክለቡ አመራሮችና በሌላ ወገኖች ጭምር ተወዳጁ ተጨዋች ነህ፤ ይህን በክለቡ ውስጥ እያለክና አሁን ከለቀክም በኋላም ከሚሰጡክ አድናቆትና ምስጋና በመነሳት ልንረዳም ችለናል፤ የእዚህ ሚስጥሩ ምንድን ነው?
እያሱ፦ ይሄ ሚስጥር ያለው አይመስለኝም። ወደ ቡና ከገባሁበት ጊዜ ጀምሮ ለክለቡ አቅሜን ሳልሰስት ነበር ሁሉን ነገሬን ሰጥቼ እጫወት የነበረው። ለቡድኑም ጥልቅ ፍቅርም አለኝ ከዛ ውጪም ከሁሉም የቡድኑ አባላቶች ጋርም ያለኝ መቀራረብና ሌላው ደግሞ በማህበራዊ ግንኙነት ወቅትም አዲስ ከሆኑም ሆነ ከነባር ተጨዋቾች ጋር ከኳሱ ውጪም ወደፊት ስለሚገጥመን ሁኔታ የምንወያይበትና እኔም በዚህ ዙሪያ ምክሬን የምለግስበት ሁኔታም ስላለ የዛ ድምር ውጤት ነው በደጋፊዎቻችንና በሰዎች ዘንድ ሊያስወድደኝ የቻለው።
ሀትሪክ፦ ወደ ሀዲያ ሆሳዕና ስላደረገው ዝውውርና በክለቡ ስለሚኖረው ቆይታ?
እያሱ፦ ይሄን ቡድን ሌሎች አማራጭ ሆነው ከቀረቡልኝ ክለቦች በማስቀደም ተመራጭ ላደርገው የቻልኩት አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በዓምናው የሐዋሳ ቡድን የሀላፊነት ዘመን ቆይታው ጥሩ ቡድንን የገነባና ለወደፊቱም ተስፋ የሚጣልበት አሰልጣኝ ስለሆነና ሀዲያ ሆሳዕናም ጠንካራ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዋንጫ ተፎካካሪ ክለብ ሆኖ ስላገኘሁት ከእነዚህ መነሻነት ነው ለቡድኑ ፊርማዬን ለማኖር የቻልኩት።
ሀትሪክ፦ የዘንድሮ ጊዜው የፋሲል ከነማና የአቡበከር ስለመሆኑ ምን አልክ?
እያሱ፦ ለሁለቱም ይሄ ዓመት ምርጥ ነበር። ፋሲል ወጥ አቋሙን በማሳየት ሻምፒዮና ሆኗል፤ አቡኪም በቡና በነበረው ቆይታ ያለ ምንም ጥያቄ ምርጡን ጊዜ ያሳለፈበት የውድድር ዓመት ነበርና ከዛ ውጪም ከዚህ በላይም አቅም ያለው ተጨዋች ስለሆነም ጊዜው የፋሲልና የእሱ ስለመሆኑ የሚያስማማ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ቡና ቆይታህ ስለ ክለቡ ብዙ ነገርን አውቀካልና በዛ ዙሪያ ምን ትላለህ?
እያሱ፡- ኢትዮጵያ ቡና ሁሌም ቢሆን ትልቅና ጥሩ አደረጃጀት ያለው ተወዳጅ ክለብ ነው፤ ብዙዎችም የሚደግፉት ነው፤ ህዝባዊ መሰረት ያለው ክለብ ስለሆነም ወደፊት ከዚህ በላይም ትልቅ መሆን ይችላልና ከሁሉም በላይ ደጋፊዎቹን ሊጠቀምባቸው ይገባል፡፡ ከእዚህ ውጪ ሌላ ልለው የምፈልገው በቡድኑ ቆይታዬ ክለቡን ከተቀላቀልኩበት ጊዜ አንስቶ ጥሩ ፍቅርን ያገኘሁበት መሆኑም ነው፤ በቡና ሳለው ከእነ መስሑድ መሐመድ ኤፍሬም ወንደሰን፣ ጋቶች ፓኖምና ኤልያስ ማሞን ከመሳሰሉ ተጨዋቾች ጋር አብሬ ነበርኩኝ፤ ከእነሱ ብዙ የተማርኳቸው ነገሮች ነበሩ፤ እነዛን ሰምቼ እኔ ይዤ የመጣሁትንም ጥሩ ሀሳብ ለሌሎች አዳዲስ ተጨዋቾችም በመንገር የበለጠ እውቀታችንን እያሰፋን የምንጓዝበት ሁኔታም ነበርና እነዚህን ጭምር ነው በቆይታዬ ላውቅ የቻልኩት፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ…?
እያሱ፡- ባሳለፍኩት የእግር ኳስ ህይወቴ ደስተኛ ነኝ፤ ያም ቢሆን ግን የሊግ ዋንጫን ማንሳትና ለብሔራዊ ቡድንም ተመርጬ መጫወትን እፈልጋለውና ይሄን እልሜን ለማሳካት ጊዜው ስላልረፈደ እና ብዙ ዕድሉም ስላለኝ ያን አጋጣሚ ለማግኘት ጠንክሬ እሰራለው፡፡
አስተያየት ይስጡ