“ኢንተርናሽናል ዳኝነት ርስት አይደለም አቅም የሌላቸው ዳኞችም ቦታ የላቸውም” ብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴ

አሁን ያሉት ኢንተርናሽናልና ዋና ረዳት ዳኞች ጠንክረው ካልሠሩ ቦታው ርስት እንዳልሆነ ሊያውቁት እንደሚገባ ብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴ አሳሰበ።

በእስካሁኑ በነበረው የፕሪሚየር ሊጉ የዳኝነት ሂደቱ ችግሮች ቢኖሩም ከሞላ ጎደል መልካም ጎኑ እንደሚያመዝን ገልጾ በቀጣይ ግን የሊጉን ጥንካሬ ማስጠበቅ የግድ በመሆኑ ከብዛትና ከኮታ አሰራር የጸዳና በብቃት ላይ መሠረት አድርጎ እንደሚሰራ አስታውቋል።ከመስከረም ጀምሮ ስልጠና በመስጠት ከፌዴራል ወደ ኤሊት ከኤሊት ደግሞ ወደ ኢንተርናሽናል ዳኝነት የማሳደግ ስራ እንደሚሰራና ሁሉም ግን አቅምና ብቃት ተኮር እንደሚሆን ኮሚቴው አስታውቋል።

ያሉትን ዳኞች የማብቃት ስራ እንደሚሰራና ሰብረው ወጥተው በተገቢው መንገድ ካልሰሩ በስመ ኢንተርናሽናል ሁሌ መቆየት እንደማይቻል ሁሉም ዳኞች ብቃታቸው ላይ ሊሰሩ እንደሚገባ ኮሚቴው አሳስቧል።
አሁንም ኮሚቴው ብቃት የሌላቸውንና የሚጠበቀውን ያህል የማይሰሩትን ወደታች የማውረድ አቅም ኖሯቸው ቦታ ያጡትን ተገቢ ቦታ እንዲያገኙ የማድረግ ስራ እንደሚሰራ ገልጿል።

ሁሌ የአመቱ ኮከብ ዳኛ የሚሆነው ኢንተርናሽናል ብቻ ለምን ይሆናል? ፌዴራል ዳኛስ ኮከብ የመሆን እድል ለምን ይነፈጋል? በሚል ለቀረበው ጥያቄ ኮሚቴው በሰጠው ምላሽ “ፌዴራሎችን የአመቱ ኮከብ ማለት ብዙ ትርጉም የለውም አቅም ያለውን ፌዴራል ዳኛ ኢንተርናሽናል ሳያደርጉ የአመቱ ኮከብ ማለት ትርጉም የለውም አቅም ያላቸውን ፌዴራል ዳኞችን ተተኪ ኢንተርናሽናል ለማድረግ በግልጽነት ላይ የተመሠረተ ስራ ለመስራት እንጥራለን” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport