“አሁንም ገና ተማሪ ነኝ ሙሉ አሰልጣኝ ሆኛለሁ ማለት አልሻም ህዝቡም ደጋፊዎቹም ተጨዋቾቼ ሳይቀሩ እያገዙኝ ነኝ ገና ወደፊት ብዙ የምማራቸው ጉዳዮች አሉኝ” ሙሉጌታ ምህረት /ሀዋሳ ከተማ/

ሀዋሳ ከተማ በሊጉ ዋንጫ ካነሱ አራት የክልል ክለቦች መሀል አንዱ ነው፤ በታሪካዊ ክለብነቱ በርካቶችን በቁጥጥሩ ስር ማዋሉ የሚነገርለት ሀዋሳ ከተማ ዘንድሮ ስጋት ከነበረባቸው ክለቦች መሀል አንዱ ቢሆንምበአጠቃላይ 24 የሊግ ጨዋታ በሊጉ ከ1-6 ባለው ደረጃ ላይ ሆኖ ማጠናቀቁ በተለይ ለአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት እፎይታን ፈጥሯል፡፡ 3 ክለቦች በሚወርዱበትና 13 ክለቦች በተፋለሙበት ሊግ ሀዋሳ ከተማ የወራጅ ስጋቱን ማስወገዱ ለቀጣዮቹ አመታት ጠንካራ ቡድን ለመፍጠር እድሉን ሰጥቶታል በወጣቶች የተገነባው የአሰልጣኝ ሙሉጌታ ስብስብ ጠንካራ ክለቦችን ማሸነፉ ደግሞ ጥሩ የውድድር አመት ማሳለፉን ያሳያል፡፡ የሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ከአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ጋር በነበረው ቆይታ ስለ አመቱ ጉዞ፣ ድል አድርጎ ስለተደሰተበትና ተሸንፎ ስላዘነበበት ጨዋታ፣ በሊጉ ስለገረመው ጉዳይ፣ ስለ አቡበከር ናስርና ስለ ኮከብ ተጨዋች፣ በአምስቱ ከተሞች ስለነበራቸው ጥሩ መጥፎ ውጤቶች ስለ ኮቪድ 19 ስጋት፣ ስለ ዳኞችና ምርመራው፣ ከአሰልጣኞች ጋር ስላለው ግንኙነት፣ ለሲዳማ ቡና አለቀቅንም ስለማለቱና ስለ ቀጣዩ ኮንትራቱ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ምላሹን ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡- 24 ጨዋታ አድርጋችሁ በ35 ነጥብና 4 ግብ 5ኛ ደረጃ ይዛችሁ አጠናቃችኋል… ደስተኛ ነህ…?

ሙሉጌታ፡- በጣም ደስተኛ ነኝ ከነበረው ሁኔታ አንፃር ደስተኛ ነኝ፡፡ ቡድኖቹ 13 መሆናቸው፣ 3 ወራጅ መሆኑ፣ የሊጉ ፎርማትና የመሳሰሉት ውድድሩን ከባድ አድርገውታል ቡድናችን ወጣት ተጨዋቾችን በብዛት ከመያዙ አንፃር ክፍተቶች ቢኖሩበትም ተወጥተነዋል፡፡ በነበረን ቆይታ ወጣት ከመሆናቸው አንፃር ሁሉንም እኩል ያለማየት ችግር ነበረብን ትልልቅ ለምንላቸው ቡድኖች ትኩረት የመስጠት መለስተኛ ናቸው ለሚባሉት የትኩረት ማነስ ችግሮች ነበሩብን ያን የማስተካከል ስራ ተሰርቷል ያም ቢሆን አሁን ለደረሰንበት ደረጃ ደርሰናል አመቱን ስንመግም በያዝነው ደረጃና ውጤት ደስተኛ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- አመቱን ስትገመግሙት ካሰባችሁት በላይነው ወይስ ከጠበቃችሁት በታች…?

ሙሉጌታ፡- እውነት ለመናገር ሊጉ እንደዚህ ይከብዳል ብዬ አልጠበኩም ቡድኖቹ 13 ቢሆኑም ደርሶ መልስ ስለነበር ብዙም ይከብዳል ብዬ አልሰጋሁም 3 ወራጅ መሆኑና በአንድ ከተማ ላይ ተሰባስበን መሆኑ ግን ሊጉን ከባድ አድርጎታል ስኳዱ ከፍ ያለና ሲኒየር ተጨዋቾች የበዙበት ቢሆን ይመረጣል የኛ ግን ወጣቶች ናቸው ጨዋታዎቹ በየአራት ቀን የሚካሄድ መሆኑ ደግሞ ልምድ ይፈልጋልና ሙሉ ወጣት ቡድን መሆኑ ከባድ አድርጎብን ነበር በዚያ ላይ ተደጋጋሚ ሽንፈቶቹ የቡድኑን ሞራል አውርዶብን ነበር በኋላ ላይ እያገገምን መጥተን እዚህ መድረሳችን ኢትዮጵያ ቡናን ካሸነፍን በኋላ ምንም ነገር ማድረግ እንደምንችል ማመናችን ትልቅ ለውጥ አምጥቷል፡፡ ወላይታ ድቻና ባህርዳር ከተማን በተከታታይ ስናሸንፍ ያሰብነውን ማድረግ እንደምንችል በማመናችን ጥሩ ደረጃ ላይ ልንደርስ ችለናል ከዚህ አንፃር ጥሩ ተፎካካሪ ከመሆን እቅዳችን በላይ በመጓዛችን በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- በማሸነፋችሁ በጣም የተደሰትክበት ጨዋታ በመሸነፋችሁም የተቆጨህበት የትኛው ነው…?

ሙሉጌታ፡- /ሳቅ/ የተለየ ደስታ የለውም ከሁሉም 3 ነጥብ ነው የሚገኘው መናገር ካለብኝ ግን ጠንካራውን ኢትዮጵያ ቡናን ማሸነፋችን የበለጠ አስደስቶኛል ምክንያቱም ከተደጋጋሚ ሽንፈት በኋላ የመጣ ድል መሆኑ ደስታ ፈጥሮልኛል፡፡ ጠንካራ ቡድን እንደመሆኑ ቡድኔ ላይ ትልቅ መነሳሳት መፍጠር ችሏል፡፡ የተከፋሁበትጨዋታ በአዳማ ከተማ የተረታንበት ጨዋታ ነው ትልቁ ችግራችን በተፈጠረብን የትኩረት ማነስ የተከሰተ ሽንፈት መሆኑ አበሳጭቶኛል ትልልቆቹ ላይ ጠንካራ ሆነን መለስተኛ ናቸው ብለን እናሸንፋለን ያልነው ጨዋታ ላይ ተሸንፈን እንወጣለን ለዚህ ነው በአዳማ ከተማ የደረሰብን ሽንፈት ያበሳጨኝ፡፡

ሀትሪክ፡- በእስካሁኑ በሊጉ ላይ ያየኸውና የገረመህ ምንድነው…?

ሙሉጌታ፡- ዘንድሮ የገረመኝ ኮቪድ 19 ነው የሁሉም ቡድን አሰልጣኝና መሪ ይመስል ነበር ልምምድ አሰርተን ቡድናችንን ስናዘጋጅ የኮቪድ 19 ውጤት ሲመጣ ከቤስት 11 ውስጥ 3 ወይም 4 ይወስድብናል ይሄ ደግሞ ከቡድኖቹ በላይ ትልቁ ፈተና የሆነብን ኮቪድ 19 ነው እንድል አስገድዶኛል ማን ይወጣል ማን ነፃ ይሆናል የሚለው አሳስቦን ነበር የሁሉም አሰልጣኝ ስጋት በኮቪድ ማን ይወጣብናል የሚለው እንጂ በጉዳት ማንን እናጣለን አይደለም ይሄ ትልቅ ገጠመኝ ነበር ለእንደኛ አይነቱ ነው በጣም ከባድ ነበር ከዚያ ውጪ የእግር ኳሱ ፉከክር ተቀራራቢ ነበር በተለይ ዲ.ኤስቲቪ በመኖሩ ጠንከራ ፉክክር እንዲኖር አድርጓል፡፡ ይሄም ገርሞኛል ክለቦቹ የአቅም ልዩነታቸው ቢለያይም ለ3 ነጥቡ ሲሉ ጠንካራ ፍልሚያ ማድረጋቸው ሊጉን አድምቆታል ግምት ተሰጥቷቸው የሚገቡ ክለቦች ሲቸገሩ ደመወዝ የሚከፍለውም ይሁን የማይከፍለው፣ ልምምድ ያደረገውም ሆነ ያቆመው ክለብ እኩል ፍልሚያ ሲያደርግ የታዩበት ነው 4 ወይም 5 ቀን ልምምድ ያልሰሩ ክለቦች ውጤት ሲያስመዘግቡም አይተናል እንደታዘብኩት እግር ኳሳችን መለወጥ አለበት ባይ ነኝ ሁሉንም ተጋጣሚ በእኩል አይን ያለማየት ሁኔታው መቀየር አለበት ትንሽም ስናሸንፍ የሚገኘው ነጥብ 3 ትልቁንም ስንረታ የሚገኘው ነጥብ 3 መሆኑን ማወቅ አለባቸው ባይ ነኝ በሊጉ በተወሰነ መልኩ የታዘብኩት ይህን ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የዚህ አመት የሀዋሳ ከተማ ኮከብ ማነው…?

ሙሉጌታ፡- ወደ 4 የሚጠጉ ኮከብ የምላቸው ጥሩ የነበሩ ተጨዋቾች አሉ ግብ ጠባቂው ሜንሣህ፣ ወንድማገኝ ኃይሉ፣ ምኞት ደበበና ደስታ ዮሀንስን መጥራት እችላለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ አቡበከር ናስር፣ ሀብታሙ ተከስተ፣ ያሬድ ባዬ ሙጅብ ቃሲም ወይስ ሌላ ኮከብ አለ…?

ሙሉጌታ፡- በርግጥ እንደ አሰልጣኝ የመረጥነው አለ ድሬደዋ እያለን ነው ወረቀቱ ተሰጥቶን የመረጥነው..ከዚያ በኋላ ሀዋሳ ላይ 10 ጨዋታ ተደርጓል ያኔ የመረጥኩት ተጨዋች ሀብታሙ ተከስተን ነበር ነገር ግን እስከ መጨረሻ ያለውን ስመለከት የተሻለ የሆነውን አቡበከር ናስርን አይቻለሁ አቡበከር በድሬደዋና በሀዋሳ የሚቀመስ አልሆነም ለማመን የሚከብድ ብቃቱን ነው ያየሁት… እናም አሁን ኮከብነቱ የአቡበከር ይመስለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- እናንተኮ አቡበከር ናስርን የያዝውን ኢትዮጵያ ቡና ረታችኋል… ድርብ ድል አይመስልህም…?

ሙሉጌታ፡- እውነት ነው በራሳችን መንገድ ተዘጋጅተን ገብተን ማሸነፋችን አስደስቶኛል ከዚያ በኋላ ነው በራስ መተማመናችን ጨምሮ ጥሩ አቋም ያሳየነው..ጥሩ ቡድን ነው ያሸነፍነው ኮከብ አግቢውና ኮከብ ተጨዋች ተብሎ ሊጠራ የሚችለው አቡበከርን ይዟል እንደዚያ ሆኖ በራሳችን ታክቲካል ዝግጅት ማሸነፋችን ያስደስታል /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- ፕሪሚየር ሊጉ ከተካሄደባቸው 5ቱ ከተሞች ጥሩ ጊዜ ያሳፋችሁትና ውጤታማ ያልነበራችሁበት ከተማ የትኛው ነው?

ሙሉጌታ፡- ጥሩ ውጤት የተመዘገበው በድሬደዋ ነው ከ5ት ጨዋታ ማሳካት ክለብን 15 ነጥብ አስሩን አሳክተናል መጥፎ ውጤት የተመዘገበው በባህርዳር ከተማ ነው ካደረግናቸው 4 ጨዋታዎች ማሳካት ከነበረብን 12 ነጥቦች ያገኘነው 2 ነጥብ ብቻ ነበር

ሀትሪክ፡- የድሬደዋ ቆይታችሁ በውጤት ቢታጀብም ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ የተፈጠረ ስጋት የለም…?

ሙሉጌታ፡-ሁሉም ክለብ የራሱን ተጨዋቾች መጠበቅ አለበት ኮቪድም የሚመጣበት አቅጣጫ አይታወቅምና ጥሩ መከላከል ማድረግ አለብን አወዳዳሪ አካሉም የራሱ የሆነ የመከላከል መንገድ ሊኖረው ይገባል በተለይ ከዳኞች ጋር ተያይዞ በምርመራ አሰጣጡም ሂደት መመርመር አለበት ከተለያየ ቦታ ከሆነ አስቸጋሪ ይሆናልና ይሄም መታሰብ ይኖርብታል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- በሊጉ የአንዳንድ ክለቦች ኮከቦች እንዳይጫወቱ ከምርመራ ክፍሉ ጋር እየተሞዳሞዱ አለባችሁ እያሉ ያስቀራሉ የሚል ነገርም ነበር… ይሄን እንዴት አየኸው…?

ሙሉጌታ፡-በርግጥ ወሬው ቢኖርም ማስረጃ አልተገኘም በምርመራው ጊዜ ማን ይመርመር የማን ይሰራ ምንም አናውቅም የህይወት ጉዳይ በመሆኑ ግን ኃላፊነት ያለባቸው ዶክተሮች ሊያስቡበት ይገባል በይበልጥ ጥንቃቄ መደረግ አለበት የህክምና ሰዎቹም ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ ብዬ አምናለው፡፡

ሀትሪክ፡- ዳኞች ሀዋሳ ሲገቡ ከተመረመሩ በኋላ እንደ ተጨዋቾቹ በየ ግጥሚያው አይመረመሩም.. ይሄስ ስጋት አይፈጥርም?

ሙሉጌታ፡- ወሬውን ሰምተናል ዳኞቹ በየጨዋታው አይመረመሩም የሚለው እውነት ይሁን ውሸት ባናውቅም መረጃውን አግኝተናል ይሄ ግን ማስረጃ ካለ በቀጣይም መታረም አለበት ኮቪድ በንክኪ ስለሚመጣ ድርጊቱ መታረም አለበት ሁሉንም በህጋዊ መንገድ መመርመር ካልተቻለ አደጋው የከፋ በመሆኑ ሊስተካከል ይገባል፡፡

ሀትሪክ፡- ከአልጣኞች ጋር የመከባበርና የመቀባበል ሁኔታ አለ?

ሙሉጌታ፡- ችግር አለ ብዬ አላምንም ከሁሉም ጋር ጥሩ ግንኙነት ነው ያለኝ… የማንንም ክብር ሳልነካ የራሴንም ክብር ሳላስነካ መኖር ነው የምፈልገው…. ከባለሙያዎች ጋር በስራችን ጣልቃ ሳናስገባ ጥሩ መከባበር አለን ብዬ አስባለው፡፡ በሙያዬ ላይ ጣልቃ የሚገባ ካለ ግን ለመቀበል እቸገራለው ጣልቃ አልገባም ማንም ጣልቃ እንዲገባብኝም አልፈልግም፡፡

ሀትሪክ፡- ከአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱና ፋሲል ተካልኝ ጋር በክለብ ተለያይታችሁ ስትገናኙ ምን ተሰማህ..?

ሙሉጌታ፡ /ሳቅ/ በርግጥ ሙያ በመሆኑ መገናኘታችን አይቀርም እንጂ ባንገናኝ ደስ ይለኝ ነበር ያም ሆኖ ከሜዳ ውጪ ጥሩ ወዳጃሞች ነን ሜዳ ውስጥ ግን ኃላፊነት ተሰጥቶን አደራ ተጥሎብን የምንገናኝ እንደመሆኑ ፉክክር ማድረጋችን አይቀርም ከሰበታ ጋር ሁለቴ ተጫውቼ አሸንፈውኛል ባህርዳር ከተማን ግን ሁለቴ ገጥሜ አሸንፌያለው ያለው እውነት ይሄ ነው፡፡ –

ሀትሪክ፡- ምነው ለአሠልጣኝ አብርሃም ራራህ…ለቀክለት እንዴ…?

ሙሉጌታ፡- /ሳቅ በሳቅ/ ምንድነው የምለቅቀው..በቃኮ ልንፋለም ሜዳ ገብተን መላቀቅ ብሎ ነገር የለም፡፡ ተጫውተን በጥሩ ፍልሚያ ተፋልመን ረተውናል ከዚያ ውጪ የምንለቀው ነገር የለም፡፡ እንደ ክለብም ሆነ ክልል ኃላፊነት ሰጥቶን የላከን ወገን እንደመኖሩ መላቀቅ አይታሰብም፡፡

ሀትሪክ፡- በሲዳማ ቡና 3ለ1 መሸነፋችሁ.. ለቀው ነው የሚል ቅሬታ አስነስቷል.. ምንድነው ምላሽህ…?

ሙሉጌታ፡- ለወሬዎች ቦታ የለኝም ነገር ግን በፍፁም አለቀቅንም ብዙ ጊዜ የተለያዩ አሉባልታዎች ይሰማሉ ነገር ግን እንደዚያ ብሎ ነገር የለም እኔም ለሙያዬ ለክለቤና ለደጋፊው ብሎም ለስፖርት ቤተሰቡ ፍቅርና ክብር አለኝ እንደዚህ አይነት ነገር ውስጥ ለመግባት አልሻም፡፡ ለማሸነፍ ሞክረናል በተለይ ግን በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ተከታታለው የገቡብን ግቦች ቡድናችንን አውርደውት ነበር በኋላ ላይ አንድ ግብ አግብተን አቻ ውጤት ስንጠብቅ ከማዕዘን ተመትቶ የተቆጠረው ግብ ሙሉ በሙሉ የጨዋታውን ሚዛን የወሰነ ሆኗል፡፡ ከዚያ ውጪ በፍፁም አለቀቅንም፡፡ ተጨዋቸቼም የሚችሉትን አድርገዋል ብዬ አምናለው በተረፈ ለሲዳማ ቡና አለቀቅንም ሙያዬንና ክብሬንም አላወርድኩም ያለው እውነት ይሄ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ከትላንት ዛሬ ለውጥ አለኝ ብለህ ታምናለህ…?

ሙሉጌታ፡ -አዎ አሁንም ገና ተማሪ ነኝ ሙሉ አሰልጣኝ ሆኛለሁ ማለት አልሻም ህዝቡም ደጋፊዎቹም ተጨዋቾቼ ሳይቀሩ እያገዙኝ ነኝ ገና ወደፊት ብዙ የምማራቸው ጉዳዮች አሉኝ፡፡ በርግጠኝነት መናገር የምሻው ግን እንደትላንቱ አይደለሁም፡፡

ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማ ሊጉን በድል ቋጭቷል.. ይገባዋል….?

ሙሉጌታ፡- በደንብ ይገባዋል እንጂ… በዲ.ኤስ.ቲቪ የታየ እውነታ ነው የሰበሰበው ነጥብም ያለው አቅምና ያሳየውን ብቃት ያሳያል ጥሩ ሆነው ቀርበው ዋንጫውን ወስደዋል እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ብሔራዊ ቡድናችን ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፉ ምን ተሰማህ…?

ሙሉጌታ፡-እንደሙያ ብቻ ሣይሆን እንደ ሀገር እንደ ዜጋ በተገኘው ድል ተደስቻለሁ በዚህ የማይደሰት ካለ ሌላ ችግር አለበት ማለት ነው፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ በማለፉ ተደስቻለው ለምቀርበው አሰልጣኝ ውበቱ አባተና ለሚቀርቡኝ ተጨዋቾች እንኳን ደስ አላችሁ ብያቸዋለው በድሉም ተደስቻለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ኮንትራትህ ተጠናቋል.. ምን አሰብክ…?
ሙሉጌታ፡- /ሳቅ/ ይሄ ጥያቄ ይለፈኝ.. ጊዜው ሲደርስ የምናገረው ይሆናል /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- ጨረስኩ የምታመሰግነው ካለ?

ሙሉጌታ፡- በመጀመሪያ አመቱ በዚህ መልኩ እንዲያልቅ ያደረገውን እግዚብሔርን አመሰግናለሁ፡፡ ቤተሰቦቼን ባለቤቴን፣ የክለቡ ደጋፊዎችና አመራሮች፣ ጓደኞቼ እና አብረውኝ
የሚሰሩ አሰልጣኞች ተጨዋቾቼን በሙሉ ማመስገን እፈለጋለው፡፡

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport