“ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኳስ እንቅስቃሴም ሆነ በውጤት ምርጡንና የተሻለውን ቡና እየተመለከትን ነው”ሚኪያስ መኮንን /ኢትዮጵያ ቡና/

“ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኳስ እንቅስቃሴም ሆነ በውጤት ምርጡንና የተሻለውን ቡና እየተመለከትን ነው”

“ለኢትዮጵያ ቡና መጫወት እድለኝነትን ይጠይቃል፤ በኢንተርናሽናል የውድድር መድረክ ላይም ቡናን ማየት ከወዲሁ አጓጉቶኛል”
ሚኪያስ መኮንን /ኢትዮጵያ ቡና/

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በሐዋሳ ዩንቨርስቲ ሜዳ ላይ በትናንትናው ዕለት ተጠናቋል። ፋሲል ከነማ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሻምፒዮና መሆኑን ባረጋገጠበት ጨዋታ ውድድሩ ትናንት ሲዘጋ ኢትዮጵያ ቡና ከአዳማ ከተማ እና የመጨረሻ ጨዋታቸውን ያደረጉ ሲሆን ቡናም ከ2004 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢንተርናሽናል የውድድር መድረክ መመለሱን ያረጋገጠበትን ውጤት አስመዝግቧል።

ኢትዮጵያ ቡና በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ፋሲል ከነማን ተከትሎ የሁለተኛ ደረጃ ውጤትን ያስመዘገበ ሲሆን የቡድኑ የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች አቡበከር ናስር ደግሞ የኮከብ ግብ አግቢ ከመሆኑ ባሻገር አስቀድሞ በጌታነህ ከበደ ተይዞ የነበረውንም ሪከርድ ውድድሩ ሳይጠናቀቅ ሊሰብር ችሏል።
ኢትዮጵያ ቡና በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁን በማስመልከትና ስለዘንድሮ የውድድሩ ጉዞ እንደዚሁም ከራሱ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የክለቡን ምርጥ የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ሚኪያስ መኮንንን የሀትሪክ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ትናንት ከጨዋታ በፊት አነጋግሮት ምላሹን ሰጥቷል።

ኢትዮጵያ ቡና ለአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ አልፎ እንደሆነ

“በእግር ኳስ ጨዋታ ምን እንደሚፈጠር ባይታወቅም በትናንትናው ዕለት ከአዳማ ከተማ ጋር ያደረግነውን ጨዋታ ለማሸነፍ ወደ ሜዳ ስለገባን ለውድድሩ ያለን የማለፍ እድላችን ሰፊ ነው። ደግሞም እናልፋለን”።

ኢትዮጵያ ቡናን በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ

“ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ምርጡንና የተሻለውን ኢትዮጵያ ቡናን በሜዳ ላይ እንቅስቃሴም ሆነ በውጤት ደረጃ እየተመለከትን ነው። የአሁኑ ቡናም በእነዚህ ጊዜያቶች ውስጥ የሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቆም አያውቅምና በውጤቱ ደስተኞችም ነን”።

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ ተብሎ ስላጠናቀቀው የቡድናቸው ተጨዋች አቡበከር ናስር

“እሱ ጓደኛዬና አብሮ አደጌ ነው። በሜዳ ላይም ሁሌም ከአጠገቡ አብሬው እየተጫወትኩ ስለማየው በጣም እየተሻሻለ ነው የመጣው። በዛ ላይም በጌታነህ ከበደ ተይዞ የነበረውንም የግብ ሪከርድ ከአራት ዓመታት በኋላም ከመስበር ባሻገር የግብ ቁጥሩንም ከፍ አድርጎም የሰቀለና ከሜዳ ውጪ ባለው ባህሪም እንደ ችሎታው ምርጥ ስለሆነም በዚሁ አጋጣሚም ይህን የሊጉ ክስተት የሆነውን ተጨዋች እንኳን ደስ ያለህ ልለውም እወዳለው”።

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ አቡበከር ናስር ኮከብ ተጨዋች ይባላል?

“ለእኔ ይመስለኛል። ምክንያቱም እሱ ምርጥ የውድድር ዘመንን ከማንም ተጨዋች በላይ ሆኖ አጠናቋልና። ከዛም ውጪ በእግር ኳሱ 13 ክለቦች ብቻ በተሳተፉበት የሊጉ ውድድርም 29 ግቦችን አስቆጥሮም በኮከብ ግብ አግቢነት የውድድር ዘመኑን ስላጠናቀቀ ቢሸለም የሚያንስበት እንጂ የሚበዛበት አይደለም”።

የኮከብ ተጨዋች ሽልማት ብዙ ጊዜ ሻምፒዮና ከሆነ ቡድን የሚመረጥ መሆኑ

“ዓለም ላይ ብዙ ጊዜ ይህ ሽልማት በዛ መልክ የሚሰጠው ብዙ ውድድሮች ስላሉ ነው። ወደ እኛ ሀገር ስትመጣ ግን አንድ ውድድር ነው ያለው። በዚህ ውድድርም አንድ ቡድን ዋንጫን ስላነሳ ብቻ ከዛ ቡድን ውስጥ ዋንጫው ብቻ መስፈርት ሆኖ ተጨዋችን መምረጥ ተገቢ ነው ብዬ አላስብም። ለዛ ተጨዋች የኮከብነቱን ሽልማት ልትሰጠው የሚገባው ዓመቱን ሙሉ ለቡድኑ ጥሩ ሆኖ ከተጫወተም ነው። ስለዚህም ዘንድሮ በነበረው ውድድር ኮከብ ተጨዋች ሆኖ መመረጥ ያለበት ምንም እንኳን ቡና ዋንጫን ባያነሳም የቡድኑ ተጨዋች አቡበከር ናስር በአጥቂ ስፍራ ላይ ሁሉንም ባሳመነ መልኩ ጥሩ ተጫውቷልና ለእሱ ነው ሽልማቱ የሚገባው”።

አቡበከር ናስር ለኢትዮጵያ ቡና በመጫወት ከ60 በላይ ግቦች ያስቆጠረውን የታፈሰ ተስፋዬን የግብ ሪከርድ ይሰብር እንደሆነ

“የታፈሰ የግብ ቁጥር ስንት እንደሆነ ባላውቅም አቡበከር በመጪው ጊዜ እዚህ ሀገር ላይ የመጫወት እድሉ ጠባብ ስለሆነ አሁን ላይ ሆኜ ይህን ሪከርድ ይሰብረዋል ብዬ ለመናገር አልደፍርም። አቡበከር አሁን ባለው ብቃትና ጨዋታዎቹም በዲ ኤስ ቲቪ እየተላለፉ በመሆናቸው ሀገር ውስጥ ይጫወታል ብዬ አላምንም። ምንአልባት ወደ ሀገር ውስጥ ተመልሶ መጥቶ ሲጫወት የግብ ሪከርዱን ሊሰብረው ይችላል”።

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ለአቡበከር ናስር አይመጥነውም ተብሎ ስለመነገሩ

“ይሄ አባባል ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። ሊጉ ለእሱ አይመጥነውም መባሉም ውድድሩን ማውረድም ነው። ግን አቡኪ ዘንድሮ ምርጥ ብቃቱን ስላሳየ ወደ ሌላ ሀገር ሄዶ መጫወትም ይችላል”።

ፋሲል ከነማ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ማሸነፉ

“ሻምፒዮናነቱ ግልፅ ነው ይገባቸዋል። ከእኛ ጋር ያላቸው የነጥብ ልዩነትም በጣም ሰፊ ስለሆነ ክብር ልንሰጣቸውም ይገባል”።

በሜዳ ላይ ከሚያሳየው ብቃት አንፃር በየጨዋታው አቡበከር፣ አቡበከር፣ አቡበከር ተብሎ በተደጋጋሚ እየተጠራ ይገኛል፤ ሚኪያስ፣ ሚኪያስ፣ ሚኪያስ የሚለውንስ ስም መች የምንሰማው ይሆናል

“አቡበከር ለእኔ ወዳጄና ጓደኛዬም ስለሆነ የእሱ ስም በዚህ መልኩ መጠራቱ በጣም ነው እያስደሰተኝ ያለው። እኔም በቀጣይ ጊዜ የኳስ ህይወቴ ፈጣሪ ሲፈቅድ ጥሩ ነገርን ለቡድኔ በመስራት ስሜን በከፍተኛ ደረጃም የማስጠራበት ጊዜ ሩቅ አይደለምና ያን ወቅት እየጠበቅኩት ነው የምገኘው። አሁን ባለኝ ብቃት ግን ቡና ውስጥ ጥሩ ጊዜን እያሳለፍኩ ነው። ቡድኔንም ጥሩ እያገለገልኩትም ነው። በችሎታዬም የከፋ ነገርንም አላሳለፍኩም”።

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ከአቡበከር ውጪ ለአንተ ምርጥ ጊዜን እያሳለፈ የሚገኘው ተጨዋች

“የፋሲል ከነማው ሽመክት ጉግሳ ነዋ! እሱ እንደ አቡበከር ሁሉ ምርጥ ችሎታውን አሳይቷል”።

ለብሔራዊ ቡድን ተመርጦ ስለመጫወት

“በጣም ናፍቆኛል። ልጅ ስለሆንኩኝ በቀጣዩ ጊዜ ጠንክሬ በመስራት ያንን የመመረጥም የመጫወትንም ዕድል የማገኝ ይመስለኛል”።

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ቡናን ዘንድሮ ዋንጫ ያሳጣው

“የሻምፒዮናነቱን ድል ባናገኝሞ ያስመዘገብነው የሁለተኛ ደረጃ ጥሩ የሚባል ነው። ቡናን ዋንጫ እንዳያነሳ አድርጎታል ብዬ የማስበው ድሬዳዋ ላይ በነበሩን ጨዋታዎች ተደጋጋሚ ነጥብን ስለጣልንና ፋሲሎች በሶስት ጨዋታዎች ላይ ሙሉ ነጥብን ስላገኙ እንደዚሁም ደግሞ ባህርዳር ላይ በነበረን ጨዋታም ፋሲሎች እኛን ስላሸነፉ እነዚህ ውጤቶች ናቸው እኛን በነጥብ ከእነሱ አርቀውን ሻምፒዮና ላንሆን የቻልነው”።

ለኢትዮጵያ ቡና መጫወት ስለመቻልና ወደ ኢንተርናሽናል ውድድር ስለመመለሳቸው

“ለኢትዮጵያ ቡና መጫወት መቻል ከክለቡ ትልቅነት አኳያ እድለኝነትን ይጠይቃል፤ ጥሩ ስሜትም ይሰማሃል። ብዙዎች ክብርም ይሰጡሃል። ከዛ ውጪ የሌላ ቡድን ተጨዋቾች ሁሉ ለእዚህ ቡድን መጫወትንም ያልማሉ። ይህን ካልኩ ቡድናችን በዘንድሮው ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የሁለተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ወደ ኢንተርናሽናል የውድድር መድረክ ሊመለስ መቻሉ በጣም አስደስቶኛል። ቡናን በኮንፌዴሬሽን ካፕ ላይ መመልከትም ከወዲሁ አጓጉቶኛል”።

በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ በመጪው ዓመት ስለሚኖራቸው ተሳትፎ

“ይህን የውድድር መድረክ ከረጅም ዓመታት በኋላ ያገኘነው እንደመሆኑ ብዙዎች
ራሳቸውን ሊያሳዩበት ይፈልጋሉ። ደጋፊዎቻችንሞ በዚህ ውድድር ላይ ታድመው ምርጥ ደጋፊነታቸውንም ማስመስከር ስለሚፈልጉ በእነሱ ድጋፍ ታጅበንና የያዝነውንሞ የጨዋታ ፍልስፍና ለዓለም በማሳየትም ከዚህ ውድድር እኛ የምንፈልገው ተሳትፎ መመለስ ሳይሆን በአገራችን የኢንተርናሽናል የውድድር መድረክ ላይ የተያዘውን ሪከርድም መስበር ነው”።

 

ስለቀጣይ ጊዜ ህልሙ

“በኢትዮጵያ ቡና የምቆይበት ኮንትራት አለኝ። ከዚህ ቡድንና የጨዋታ ፍልስፍና ጋርም የሊግ ዋንጫን ማንሳት የቀጣይ ጊዜ እቅዴ ነው”።

ስለ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ

“ምርጥ አሰልጣኝ ነው ያለን። በተጨዋችነት ዘመኑም ጥሩ ተጨዋች እንደነበርም ላውቅ ችያለው። እሱን በጣምም ነው የምናከብረው። አይደለንም እኛ የተቃራኒ ቡድን ተጨዋቾችና አሰልጣኞችም በሚሰራው ስራ እያደነቁት ነው። እኔን ስላሰለጠነኝ ሳይሆን ብዙ ነገርን መስራትም የሚችል አሰልጣኝ ነው። ከእሱ ውጪ ሌሎቹም የኮቺንግ ስታፉ አባላቶችም አሪፍ የሚባሉ ናቸው”።

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሲጠቃለል

“አጠቃላይ ውድድሩ በዲ ኤስ ቲቪ ስለተላለፈና ምንም አይነትም የውድድር መቆራረጥ ስላልነበረበት የዘንድሮው ውድድር ምርጥ ነበር። ደጋፊ ቢኖር ደግሞ የበለጠም ያምር ነበር። እንደ ክፍተት የተመለከትኩት የአንድ አንድ ሜዳዎች ለጨዋታ ምቹ አለመሆናቸውን ብቻ ነውና ለቀጣዩ ጊዜ እነሱ ሊስተካከሉ ይገባል”።

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website