በ23ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ፋሲል ከተማን ከባህርዳር ከተማ አገናኝቶ በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ በተካሄደው እና በርካታ ክስተቶችን ባስተናገደው ጨዋታ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ፍቃዱ አለሙ ባስቆጠረው የፍፁም ቅጣት ምት ግብ አፄዎቹ ማሸነፍ ችለዋል ።
ፋሲል ከተማ በ23ኛው ሳምንት ሲዳማ ቡናን በረቱበት ጨወላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ሶስት ለውጦችን በማድረግ ከድር ኩሊባሊ ፤ አምሳሉ ጥላሁን እና ይሁን እንደሻውን በአስቻለው ታመነ ፤ ሰኢድ ሀሰን እና ሀብታሙ ተከስተ ምችክ ሲያሰልፉ በባህርዳር ከተማ በኩል ደግሞ በሳምንቱ ከወላይታ ድቻ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 በተመሳሳይ ሶስት ለውጦችን በማድረግ ፉአድ ፈረጃ ፤ ፍቅረሚካኤል አለሙን እና ተመስገን ደረሰን በአለልኝ አዘነ ፤ በረከት ጥጋቡ እና አደማ አባስ ምትክ አሰልፈዋል ።

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ብርቱ ሊባል የሚችል የሜዳ ላይ ፉክክር የተደረገ ሲሆን በፋሲል ከተማ በኩል በጥሩ የኳስ ቅብብል ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ይዘው የሚሄዱት ኳስ በጣና ሞገዶቹ የኋላ መስመር ተጫዋቾች ይበላሽባቸው የነበረ ሲሆን በባህርዳር ከተማ በኩል በተለይም በፈጣን ሽግግር ወደ ፊት መድረስ ቢችሉም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ ረገድ ደካማ ነበሩ ።
ለደቂቃዎች በግብ ሙከራ ያልታጀበው ጨዋታ በ25ኛው ደቂቃ ላይ ነበር ለግብ የቀረብ የመጀመሪያ አጋጣሚን ያስመለከተን ። አሊ ሱሌማን ከፍፁም አለሙ በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ሆኖ የደረሰውን ግሩም ኳስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።
በቀጣይ ደቂቃዎች ላይ አፄዎቹ በተከታታይ ሁለት የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር ። በ30ኛው ደቂቃ ላይ ኦኪኪ አፎላቢ ከርቀት የቅጣት ምት ወደ ግብ የላከው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል ። ከደቂቃዎች በኋላም በረከት ደስታ ከሱራፋል ዳኛቸው የደረሰውን ኳስ በጠንካራ ምት ወደ ግብ ቢልከውም ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑሪ አድኖታል ።
የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ባህርዳር ከተማዎች ወሳኝ የሆነወሰ ተጫዋቻቸው ፍፁም አለሙ በሁለተኛ የቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቶባቸዋል ።

ፋሲል ከተማዎች የቁጥር ብልጫውን ይጠቀማሉ ተብሎ ቢጠበቅም የሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ አራተኛ ደቂቃ ላይ ያሬድ ባየህ በተመሳሳይ ሁለተኛ የቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ ባህርዳር ከተማዎች በተሻለ ወደ ፊት የመድረስ አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም የአፄዎቹን የኋላ ክፍል አልፈው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው ነበር ።
ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ የግብ ሙከራዎችን ለመመልከት ረጅም ደቂቃዎችን ያስጠበቀን አጋማሹ በ75ኛው ደቂቃ ላይ በባህርዳር ከተማ በኩል የተፈጠረ የግብ ዕድል አስመልክቶናል ። ተመስገን ደረሰ በመልሶ ማጥቃት የመጣን ኳስ ከአብዱልከሪም ኒኪማ በጥሩ ሁኔታ ደርሶት የነበረ ቢሆንም የተመስገንን ኳስ ዓለምብርሀን ይግዛው ተደርቦ አውጥቶታል ።
የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ አፄዎቹ ወደ ባህርዳር ከተማ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ ለመድረስ ያደረጓቸው ጥረቶች በ87ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ ዕድል ይዞላቸው መቷል ። ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታውን ኳስ መናፍ ዐወል ለመደረብ ሲሞክር በእጁ በመንካቱ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ፍቃዱ አለሙ ከመረብ ላይ አሳርፎታል ። ተቀይሮ ገብቶ ግቡን ያስቆጠረው ፍቃዱ አለሙ በ23ኛ ሳምንት ጨዋታ ፋሲል ከተማ ሲዳማ ቡናን ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ ቀይሮ ገብቶ የማሸነፍ ግብ ማስቆጠሩ ይታወሳል ።

ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከተማ ነጥቡን 43 በማድረስ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለወሰን የነጥብ ልዩነት ወደ 8 ዝቅ ሲያደርግ ባህርዳር ከተማ በበኩሉ በ26 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል ።

በ24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ግንቦት 8 ( ማክሰኞ ) 7:00 ላይ ባህርዳር ከተማ አዳማ ከተማን ሲገጥም በተከታዩ ቀን ግንቦት 9 ( ረቡዕ ) በተመሳሳይ ሰዓት ፋሲል ከተማ መከላከያን የሚገጥም ይሆናል ።
አስተያየት ይስጡ