በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአንደኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ ቀዳሚ ጨዋታ ፋሲል ከነማን ከአዳማ ከተማ አገናኝቶ በፋሲል ከተማ አሸናፊነት የ2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
በአሰልጣኝ ሀይሉ ነጋሽ የሚመሩት ፋሲል ከነማዎች በቋሚ አሰላለፍ ሚካኤል ሳማኪ ፤ አምሳሉ ጥላሁን ፤ ከድር ኩሊባሊ ፤ አስቻለው ታመነ ፤ ዓለምብርሀን ይግዛው ፤ ሽመክት ጉግሳ ፤ በዛብህ መለዮ ፤ ይሁን እንደሻው ፤ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ፤ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ፍቃዱ አለሙ የተሰለፉ ሲሆን በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳሉ በሚመሩት አዳማ ከተማ በኩል ደግሞ ሰይድ ሀብታሙ ፤ ጀሚል ያዕቆብ ፤ ሚሊዮን ሰለሞን ፤ አዲስ ተስፋዬ ፤ ደስታ ዮሀንስ ፤ አማኑኤል ጎበና ፤ መስዑድ መሐመድ ፤ ዊሊያም ሰለሞን ፤ ዳዋ ሆጤሳ ፤ አብዲሳ ጀማል ፤ እና አሜ መሐመድ በቋሚ አስራአንድ የተሰለፉ ተጫዋቾች ናቸው ።
የቀትሩ ጨዋታ በሁለቱም በኩል በሁለቱም በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ፍላጎት በታየበት የጨዋታ እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን በ14 ደቂቃዎች ውስጥም ሁለት ግቦች ተስተናግደውበታል ።
- ማሰታውቂያ -
በቀጥተኛ አጨዋወት ወደ ግብ የመድረስ አዝማሚያዎች በተስተዋሉበት ጨዋታ አፄዎቹ በ8ኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል ። የፋሲል ከነማን የፊት መስመር የሚመራው ፍቃዱ አለሙ ከሽመክት ጉግሳ በተከላካዮች መካከል የደረሰውን ኳስ በአዳማ ከተማ መረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል ።
ነገር ግን የአፄዎቹ መሪነት ከስድስት ደቂቃዎች በላይ የዘለቀ አልነበረም ። በግሩም ቅብብል በሳጥኑ የግራ አቅጣጫ ይዘው የገቡትን ኳስ በአንጋፋው ተጫዋች መስዑድ መሐመድ አቀባይነት በአሜ መሐመድ ጨራሽነት አዳማ ከተማዎች አቻ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋውል ።
የአዳማ ከተማዎች ደስታ እየገለፁ ባሉበት ቅፅበት ግን የመሀል ክፍል ተጫዋቻቸው ዊልያም ሰለሞን በሁለተኛ የቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል ።
ምንም እንኳን አዳማ ከተማዎች የቁጥር ብልጫ ቢወስደባቸውም በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ይየ ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር የአፄዎቹን የኋላ መስመር ለመፈተን ጥረቶችን አድርገዋል ።
ቀስ በቀስ ፋሲል ከነማዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ወስደው በመጫወት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ የቻሉባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር ቢችሉም የአዳማ ከተማን የኋላ መስመር አልፈው ግብ ለማስቆጠር አልቻሉም ነበር ።
የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ ፋሲል ከነማዎች በተሻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ከተጋጣሚያቸው በተሻለ በመንቀሳቀስ መጫወት የቻሉ ሲሆን በዚህም በ53ኛው ደቂቃ ላይ ዳግም መሪ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል ።
ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በግራ መስመር አቅጣጫ ከአምሳሉ ጥላሁን የተቀበለውን ኳስ በግሩም ሁኔታ የአዳማ ከተማ ተከላካዮችን አልፎ ለፍቃዱ አለሙ ያቀበለው ኳስን አጥቂው ለራሱ እና ለክለቡ ሁለተኛ ግብ አድርጎ አስቆጥሯል ።
የቁጥር ብልጫ የነበራቸው አፄዎቹ በተሻለ እንቅስቃሴ ሶስተኛ ግብ ለማከል በሚጫወቱበት ሰዓት በነሱም በኩል ሽመክት ጉግሳ በ68ኛው ደቂቃ ላይ በሁለተኛ የቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል ።
በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ አዳማ ከተማዎች ተጭነው በመጫወት የግብ ዕድል ለመፍጠር ያደረጓቸው ጥረቶች ሳይሰምሩ ጨዋታው በፋሲል ከነማ አሸናፊነት ተጠናቋል ።
በሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው መስከረም 27 አርብ 10:00 ላይ አዳማ ከተማ ከመቻል ሲጫወት ፋሲል ከነማ በበኩሉ ባለበት የኮንፌዴሬሽን ካፕ ጨዋታ ምክንያት ከድቻ የሚያደርገውን የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታ ህዳር 27 10:00 ላይ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ያደርጋል ።