የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ሲደረጉ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ፋሲል ከነማ ድል ቀንቷቸዋል።
በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ የዓምናው ሻምፕዮን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውድድር ዓመቱ እየተቸገረ ያለውን ሀዋሳ ከተማን 2 – 0 አሸንፏል።
በጨዋታው አዲስ ግደይ በ26ኛው ደቂቃ ላይ በራሱ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ከመረብ አሳርፏል።
የሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ ሁለተኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሳይመን ፒተር የበፀሎት ልዑል ሰገዱን ቡድን መሪነት ወደ 2 – 0 አሳድጓል።
- ማሰታውቂያ -
ውጤቱንም ተከትሎም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነጥቡን 21 በማድረስ ደረጃውን ወደ 13ኛ ከፍ አድርጓል።
በ15 ነጥብ ላይ ለመቆየት የተገደደው ሀዋሳ ከተማ የመጀመሪያውን ዙር በወራጅ ቀጠና ውስጥ ሆኖ ማጠናቀቁን አረጋግጧል።
በ19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወላይታ ድቻ ሲጫወት ሀዋሳ ከተማ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎቹን አጠናቋል።
በዕለቱ ሁለተኛ እና በሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ደግሞ የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን በፋሲል ከነማ የ1 – 0 ሽንፈትን አስተናግዷል።
በጨዋታው አንዋር ሙራድ በ76ኛው ደቂቃ ላይ በግሩም ሁኔታ ያስቆጠረው ግብ ለአፄዎቹ ጣፋጭ ሶስት ነጥቦችን አስገኝቷል።
አንዋር ሙራድ በተከታታይ ሶስተኛ የሊግ ጨዋታ ያስቆጠረው ግብም ሆኖ ተመዝግቧል።
የውድድር ዓመቱን አራተኛ ድል ያስመዘገበው ፋሲል ከነማ ነጥቡን 23 በማድረስ ወደ 8ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችሏል።
ከ107 ቀናት በኋላ ሽንፈት ያስተናገደው ኢትዮጵያ መድን ከተከታዮቹ ያለውን የነጥብ ልዩነት ማስፋት የሚችልበትን ዕድል ባይጠቀምም በ32 ነጥቦች በመሪነቱ ቀጥሏል።
በመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ፋሲል ከነማ ከባህርዳር ከተማ እንዲሁም ኢትዮጵያ መድን ከድሬዳዋ ከተማ ይጫወታሉ።


