በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ሲደረጉ ኢትዮጵያ መድኅን እና ፋሲል ከነማ ሶስት ነጥቦችን አሳክተዋል።
በቀዳሚው ጨዋታ የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድኅን በሶስት ርቆ ነጥቦች ከኋላው የሚከተለውን ሀድያ ሆሳዕናን ገጥሞ 1 – 0 አሸንፏል።
በጨዋታው የማሸነፊያውን ብቸኛ ግብ ዳዊት ተፈራ በ55ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል። ዳዊት ይህን ግቡንም ተከትሎ በውድድር ዓመቱ ያስቆጠራቸውን የግብ ብዛቶች አራት አድርሷል።
በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው ኢትዮጵያ መድኅን ነጥቡን 32 በማድረስ በአራት ነጥቦች ልዩነት ሊጉን መምራት ቀጥሏል።
- ማሰታውቂያ -

ተከታታይ ሁለተኛ ሽንፈት ያስተናገደው ሀድያ ሆሳዕና በበኩሉ በ26 ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል።
ኢትዮጵያ መድኅን በ18ኛ ሳምንት መርሐግብር ከፋሲል ከነማ ሲጫወት ሀድያ ሆሳዕና በበኩሉ ከአርባምንጭ ከተማ ይገናኛል።
በዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ደግሞ ፋሲል ከነማ ድሬዳዋ ከተማን 2 – 1 አሸንፏል።
ለአፄዎቹ ሀብታሙ ተከስተ በ27ኛው ደቂቃ ላይ አንዋር ሙራድ ደግሞ በ46ኛው ደቂቃ ላይ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ሙኽዲን ሙሳ በ53ኛው ደቂቃ ላይ ድሬዳዋ ከተማን ከሽንፈት ያልታደገች ግብ ማስቆጠር ችሏል።
ድሉ ለአፄዎቹ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ የተገኘ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ ለተከታታይ ስድስተኛ የሊግ ጨዋታ ያለ ድል የተጓዘበትን ውጤት አስመዝግቧል።
ፋሲል ከነማ ነጥቡን 20 በማድረስ ወደ 9ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ በ19 ነጥቦች 11 ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል።
በቀጣይ ሳምንት መርሐግብር ፋሲል ከነማ ከኢትዮጵያ መድኅን ድሬደዋ ከተማ ደግሞ ከወልዋሎ ኢዲግራት ይገናኛሉ።


