የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 14ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታድየም በዛሬው ዕለት ተደርገዋል።
በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ከፋሲል ከነማ አገንኛቶ በቡናማዎቹ የ1 – 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ለአሰልጣኝ ነፃነት ክብሬው ቡድን የማሸነፊያውን ግብ ዲቫይን ዋችኩዋ በ66ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል።
አንተነህ ተፈራ ከበፍቃዱ አለማየሁ የተቀበለውን ኳስ በሳጥኑ የግራ አቅጣጫ ይዞ ገብቶ ወደ ግብ ሞክሮት በግብ ጠባቂው ዮሐንስ ደርሶ ቢመለስም በቅርብ የነበረው ዲቫይን ዋቹኩዋ ከመረብ አሳርፎታል።
- ማሰታውቂያ -
ግቡም ለናይጄሪያዊው ተጫዋች በቡናማዎቹ ማልያ ያስቆጠረው ሁለተኛ ግቡ ሆኖ ተመዝግቧል።
ውጤቱንም ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና ነጥቡን 17 በማድረስ ወደ 7ኛ ከፍ ማለት ችሏል።
ጨዋታውን ግብ ሳይቆጠርባቸው ያጠናቀቁት ቡናማዎቹ ባለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ምንም ግብ ሳያስተናግዱ መቀጠል ችለዋል። ይህም በውድድር ዘመኑ በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ባለማስናገድ ብቸኛ ቡድን አድርጓቸዋል።
በተጨማሪም በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታድየም ተከታታይ ያለመሸነፍ ጉዟቸውን 10ኛ ጨዋታ ላይ አድርሰዋል።
በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው ፋሲል ከነማ በበኩሉ ሌላ መጥፎ ሽንፈትን ያስተናገደበት ዕለት ሆኖ አልፏል።
ኢትዮጵያ ቡናን በ2003 ዓ.ም የሊግ ዋንጫ አሸናፊ ማድረግ የቻሉት ውበቱ አባተ ፋሲልን እየመሩም ለመጀመሪያ ጊዜ በቀድሞ ክለባቸው ተረተዋል።
በውድድር ዘመኑ በሶስት ጨዋታዎች ብቻ ድል የቀናው የጎንደር ከተማው ተወካይ ከአምስት ሽንፈት አልባ ጨዋታዎች በኋላ ሽንፈትን ቀምሷል።
ቡድኑ በቀጣይ ከሚያደርጋቸው ተከታታይ አራት ጨዋታዎች መካከል በሶስቱ በደረጃ ሰንጠረዡ እስከ አራተኛ(መቻል ፣ ኢትዮጵያ መድኅን እና ባህር ዳር ከተማ) ከሚገኙ ክለቦች ጋር ማድረጉ ደግሞ ሁኔታዎችን ሊያከብድበት እንደሚችል እንዲገመት አድርጓል።
አፄዎቹ አሁን ላይ ከወራጅ ቀጠናው በሁለት ነጥቦች ብቻ ርቀት ላይም ይገኛሉ።
በ15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ፋሲል ከነማ የሊጉን መሪ መቻልን ሲገጥም ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ በሳምንቱ አራፊ ቡድን ነው።
በዕለቱ ሁለተኛ እና በሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ኢትዮጵያ መድኅን ሀዋሳ ከተማን 2 – 0 ረቷል።
በጨዋታው መሐመድ አበራ እና ዳዊት ተፈራ የኢትዮጵያ መድኅንን ግቦች ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።
በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው መድኅን በተከታታይ እያስመዘገባቸው ባለው ውጤቶች ከመሪው መቻል በሁለት ነጥቦች ርቀት ብቻ ለመቀመጥ ችሏል።
ቡድኑ የውድድር ዓመቱ ብቸኛውን ሽንፈት በሶስተኛው ሳምንት በሲዳማ ቡና ካስተናገደ በኋላ ባለፉት ተከታታይ ዘጠኝ ጨዋታዎች አልያም 88 ቀናት ያለ ሽንፈት መጓዝ ችሏል። ቡድኑ በዚህ ጉዞው በስድስቱ ጨዋታዎች ሶስት ነጥቦችን ይዞ ወጥቷል።
በተጨማሪም በመከላከል ረገድ ጠንካራ ሆኖ የቀጠለው ቡድኑ ከ12 ጨዋታዎች ለሰባተኛ ጊዜ ግብ ሳያስተናግድ ያጠናቀቀበት ጨዋታ ሆኗል።
እጅግ መጥፎ የውድድር ዘመን እያሳለፈ ያለው ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ በሊጉ ከድል ከተራራቀ ሶስተኛ ወሩን ደፍኗል።
ክለቡ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን አሰናብቶ በጊዜያዊ አሰልጣኞች ቢመራም በኢትዮጵያ ዋንጫ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከረታበት ጨዋታ ውጪ በሊጉ ደጋፊዎቹን ማስደሰት አልቻለም።
ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በተለይም በኤርትራዊው አሊ ሱሌይማን የሚመራው የፊት መስመሩ በርካታ ግቦችን ማስቆጠር ቢችልም ዘንድሮ እስካሁን ባለው ቁጥር የሊጉ ሁለተኛ ዝቅተኛ ግብ አስቆጣሪ ቡድን ሆኗል።
ባለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎችም ሐይቆቹ ኳስና መረብን አንድም ጊዜ ማገናኘት አልቻሉም።
ቡድኑ አሁንም ከ13 ጨዋታዎች 10 ነጥቦችን ብቻ በመያዝ ወልዋሎ አዲግራትን ብቻ በልጦ 17ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በቀጣይ ሳምንት ጨዋታዎች ሀዋሳ ከተማ ከተከታዩ ወልዋሎ አዲግራት ሲገናኝ ኢትዮጵያ መድኅንም ተከታዩን ባህርዳር ከተማ ይገጥማል።


