የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሲደረጉ የዓምናው ሻምፒዮን ከሳምንታት በኋላ ወደ ድል ሲመለስ የሊጉ መሪ መቻል ከድሬዳዋ ከተማ ነጥብ ተጋርቷል።
በቀዳሚው መርሐግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክን የገጠመው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዲስ ግደይ ድንቅ የቅጣት ምት ግብ 1 – 0 አሸንፏል።
ባለፉት ስድስት ተከታታይ ጨዋታዎችን ሳያሸንፍ ለተጓዘው ቡድኑ ድሉ እፎይታን እንደሚሰጥ ይጠበቃል። በተጨማሪም ውጤቱ በጊዜያዊነት ከወራጅ ቀጠናው ለመላቀቅ አሰችሎታል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዓምናው የሻምፒዮንነት ጉዞ ትልቅ ሚናን ከተወጡ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው አዲስ ግደይም በውድድር ዓመቱ ያስቆጠራቸውን የግብ ብዛቶች 5 ማድረስ ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበኩሉ ሊጉ በዚህ ፎርማት መደረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአዳማ ሳይንሰና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም አሁንም ድል ማድረግ አልቻለም።
በቅዱስ ጊዮርጊስ እስከተረታበት ጨዋታ ድረስ በዘጠኝ ተከታታይ ጨዋታዎች ያልተሸነፈው ቡድኑ በውድድር ዘመኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከታታይ ሽንፈትን አስተናግዷል።
ሁለቱ ቡድኖች ከቀናት በፊት በኢትዮጵያ ዋንጫ ተገናኝተው የአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገዱ ቡድን አሸናፊ እንደነበረም ይታወሳል።
በቀጣይ ሳምንት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሀድያ ሆሳዕና እንዲሁም ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከመቀሌ 70 እንደርታ ይጫወታሉ።
በዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ደግሞ መሪው መቻል ከተከታዮቹ ያለውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ የሚችልበትን ዕድል ሳይጠቀም ቀርቷል።
ድሬዳዋ ከተማን የገጠመው ቡድኑ ግብ ሳያስቆጥርም ሳያስተናግድም በአቻ ውጤት ተለያይቷል።
ጦሩ ባለፉት አራት ተከታታይ የሊግ ጨዋታችም በአንዱ ብቻ ሙሉ ሶስት ነጥቦችን አሳክቷል።
የመቻል ነጥብ መጣል ለተከታዮቹ መልካም ዜና ይመስላል።
በተለይም ሀድያ ሆሳዕና በ15ኛው ሳምንት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ማሸነፍ ከቻለ የሊጉን መሪነት ዳግም መልሶ ያገኛል።
የአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለው ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ በሊጉ አራተኛ ተከታታይ የአቻ ውጤትን ያስመዘገበበት ጨዋታ ሆኗል።
ቡድኑ ከዚህ ጨዋታ ቀደም ብሎ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ባህርዳር ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ተጋርቷል።
በመከላከሉ ረገድ ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ሁለት ግብ ብቻ ያስተናገደው ቡድኑ በአራቱ ጨዋታዎች ግን በተጋጣሚዎቹ ላይ ግብ ማስቆጠር አልቻለም።
ቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪውን መሐመድኑር ናስርን በጉዳት ካጣ በኋላ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ አስቆጥሯል።
በቀጣይ ሳምንት መቻል ከፋሲል ከነማ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ይጫወታሉ።


