በአዳማ የተደረጉ ጨዋታዎች በመሸነፍ ሲቋጩ የሀዋሳ ጨዋታዎች በበኩላቸው በአቻ ውጤት ተቋጭተዋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 0 – 2 መቻል
በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሜዳ ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከመቻል ያገናኘው ጨዋታ መቻልን ወደ ድል የመለሰ ውጤት ተመዝግቦበታል። 14ኛው ደቂቃ አለምብርሀን ይግዛው ከቀኝ መስመር አቅጣጫ የሰጠውን ኳስ በጉዳት ክለቡን ማገልገል ብዙም እየቻለ ያልሆነው ዩጋንዳዊው አጥቂ ቻርለስ ሙሴጌ ሲያስቆጥር 83ኛ ደቂቃ ላይ በረጅሙ የተጣለለትን ኳስ ቸርነት ጉግሳ በግንባር ከጀርባ ለነበረው አለምብርሀን ይግዛው ጨርፎለት ከሳጥኑ ጠርዝ ተጫዋቹ በማስቆጠር መቻልን 2ለ0 አሸናፊ አድርጓል።
ወልዋሎ አዲግራት ዩ 1 – 0 ምድረ ገነት ሽረ
- ማሰታውቂያ -
ሌላው አዳማ ላይ ማምሻውን በተደረገ ጨዋታ ሁለቱን የትግራይ ክለቦች ያገናኘው መርሀግብር ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲን 1ለ0 በሆነ ውጤት ምድረገነት ሽረን ረቷል። 18ኛው ደቂቃ ላይ ስምኦን ማሩ የሽረው ተከላካይ ፀጋአብ ዮሐንስ ላይ ሳጥን ውስጥ ጥፋት ሰርተሀል በሚል የዕለቱ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ምት ኮንኮኒ ሀፊዝ መቶ የግብ ዘቡ ሪችሞንድ አይ ሲመልሳት ኳሷን ያገኘው ጌትነት ተስፋዬ መረብ ላይ ያሳረፋት ጎል ለቡድኑ ብቸኛዋ የአሸናፊነት ግብ ነች።
60ኛው ደቂቃ ላይ የሽረው ግብ ጠባቂ ሪችሞንድ አይ ኮንኮኒ ሀፊዝ በሰራው አደገኛ ጥፋት በቀጥታ በቀይ ተወግዷል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ 0 – 0 ነገሌ አርሲ
ሀዋሳ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከነገሌ አርሲ ያገናኘው ከቀትር መልስ የተከናወነው ጨዋታ ያለ ጎል ተቋጭቷል። በጨዋታው ብዙም ሳቢ ያልነበሩ እና በሙከራዎች መታጀብ ያልቻለ ሲሆን ከዕረፍት መልስ ነገሌዎች የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ከቤ ብዙነህ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ሸገር ከተማ 1 – 1 ኢትዮጵያ መድን
አመሻሹን ኢትዮጵያ መድን እና ሸገር ከተማን ያገናኘው ጨዋታ 1ለ1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል። 82ኛው ደቂቃ ላይ ሸገሮች ቡልቻ ሹራ ከቀኝ ወደ ውስጥ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ያሻማውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ዳዊት ካሳው አግኝቶ ወደ ግብ መቶ የባህሩ ነጋሽ ስህተት ታክሎበት ቡድኑ መሪ መሆን ቢችልም በጭማሪው ስድስት ደቂቃ ውስጥ 90+1 ደቂቃ ላይ ያሬድ ካሳዬ ከግራ ያሻማውን ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አዲሱ የመድን ፈራሚ ሳሙኤል ሳሊሶ በመጀመሪያ ጨዋታው የቡድኑን የአቻነት ግብ ከመረብ አዋህዷል።


