አዳማ እና ሀዋሳ ላይ በተደረጉ አራት የሊጉ ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ሲጠናቀቁ መሪዎቹ ሦስቱም ማሸነፍ አልቻሉም።
ሀዋሳ ከተማ 1 – 1 ድሬዳዋ ከተማ
አዳማ ላይ ሀዋሳ ከተማን ከድሬዳዋ ከተማ ጋር አገናኝቶ ነጥብ ተጋርቶ መሪነቱን ከፍ የሚያደርግበትን ዕድል አበላሽቷል። ሀዋሳዎች በብዙ ረገድ የተሻሉ ቢመስሉም ለመመራት በተገደዱበት የመጀመሪያው አጋማሽ 18ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር የተሻማችውን ኳስ በሀዋሳው ተከላካይ ምንተስኖት ቶማስ ተደርቦ ሳጥኑ ጠርዝ የደረሰችውን ኳስ ድልአዲስ ገብሬ አክርሮ መቶ አስደናቂ ጎል በማስቆጠር ብርቱካናማዎቹን መሪ አድርጓል።
ከዕረፍት መልስ ከቆሙበት የመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫቸው የቀጠሉት ሐይቆቹ 61ኛው ደቂቃ ላይ የአብስራ ደግፌ ኳስን ከተቃራኒ ተጫዋች ጋር ተሻምቶ ተጨርፋ ሽመልስ በቀለ እግር ስር ስትገባ አማካዩ ወደ ጎልነት ለውጧት ሀዋሳን ወደ አቻነት በማሸጋገር ጨዋታው ተጨማሪ ጎል ሳያሳየን 1ለ1 ተጠናቋል።
- ማሰታውቂያ -

ሲዳማ ቡና 0 – 0 ወልዋሎ አዲግራት ዩ.
ሲዳማ ቡና በሊጉ የታችኛው ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ጋር ያደረገውን ጨዋታ ማሸነፍ ሳይችል ቀርቷል። ከሜዳ ውጫ ያሉበትን ፈተናዎቹ አገባዶ ለዛሬው ጨዋታ የበቁት ወልዋሎች በአንፃራዊነት በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫን ሲወስዱ በሁለተኛው አጋማሽም ተመጣጣኝ እንቅስቃሴን ብናስተውልም ጨዋታው 0ለ0 ተጠናቋል።
አርባምንጭ ከተማ 1 – 1 ነገሌ አርሲ
ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ሜዳ ላይ በሊጉ ግርጌ የተቀመጠው አርባምንጭ ከተማ ከነገሌ አርሲ ጋር ያደረጉት መርሀግብር 1ለ1 በሆነ የአቻ ውጤት ተቋጭቷል። ነገሌዎች በተሻለ የማጥቃት ደመ ነብስ ጥሩ ለመንቀሳቀስ የሞከሩበት አርባምንጮች በበኩላቸው በመልሶ ማጥቃት በቁጥር ባነሳ የማጥቃት ሂደት ለመጫወት ጥረት ያደረጉበት ቀዳሚው አጋማሽ ነገሌዎች መሪ የሆኑት 18ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። በረጅሙ ከራሳቸው ሜዳ የለጉትን ኳስ የግብ ዘቡ ፂሆን መርዕድ ከኢብሳ በፍቃዱ ጋር ታግሎ ለማውጣት ጥረት ሲያደርግ ግብ ክልሉን ለቆ በመውጣቱ ኳሷን ያገኘው ዳዊት ተፈራ በጥሩ ዕይታ መረቡ ላይ አስቀምጦ ሰጎኖቹን መሪ አድርጓል።
ከዕረፍት መልስ ቅያሪ ተጫዋቾችን በማድረግ ተሽለው ወደ ሜዳ የተመለሱት አዞዎቹ 48ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ከገባ በኋላ ፈጣን ሙከራን አድርጎ የነበረው ይድነቃቸው ቃሲም ከቀኝ መስመር ያሻማትን ኳስ ያገኘው በፍቅር ግዛቸው ቡድኑን አቻ አድርጓል። ጨዋታው ቀጥሎ 63ኛው ደቂቃ ላይ የአርባምንጩ አምበል እና ተከላካይ አበበ ጥላሁን መሐል ሜዳው አካፋይ ላይ ዳዊት ተፈራን አደገኛ በሆነ አጨዋወት ጉዳት በማድረሱ የዕለቱ ዳኛ ሀይማኖት አዳነ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ አስውጥቶታል። በቀጣይ ደቂቃዎች አርባምንጮች በጥብቅ መከላከል የተጋጣሚያቸውን ማጥቃት በደንብ በማስቆም አንድ ነጥብን ይዘው ወጥተዋል ጨዋታውም 1ለ1 ተቋጭቷል።
ሸገር ከተማ 0 – 0 ኢትዮ ኤሌክትሪክ
አመሻሹን ሸገር ከተማን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ አገናኝቶ የነበረው መርሀግብር በብዙ መመዘኛዎች ተመጣጣኝ የሚመስል የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴዎችን አስመልክቶን 0ለ0 ሊጠናቀቅ ችሏል።


