መቻል በእጁ የገባውን ነጥብ ለወላይታ ድቻ አሳልፎ ሲሰጥ ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ባህርዳር እና አዳማ ከተማም ሦስት ነጥቦችን አግኝተዋል።
ወላይታ ድቻ 4-3 መቻል
የፕሪምየር ሊጉ የሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ቀን አራት ጨዋታዎች አዳማ እና ሀዋሳ ዩኒቨርሰቲዎች ሜዳዎች ላይ ተደርገው ሁሉም ጨዋታዎች በመሸናፍ ተጠናቋል። አዳማ ላይ ድራማዊ ክስተቶች በነታየበት ጨዋታ መቻል በመጀመሪያው አጋማሽ ገና 2ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ ወደ ቀኝ የሳጥኑ ክፍል የደረሰውን ኳስ አክርሮ መቶ የግብ ዘቡ አብነት ሀብቴ ሲተፋው አጠገቡ የነበረው ቸርነት ጉግሳ የልጅነት ክለቡ ላይ ኳሷን መረቡ ላይ አሳርፏታል። 39ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ ቅብብል መሐመድ አበራ ያገኛትን ኳስ ወደ ጎል ሲመታው በድቻ ተከላካዮች ኳሷ ተደርባ ስትመለስ በረከት ደስታ ሁለተኛ ጎል አድርጓታል።
ከዕረፍት መልስ የተጫዋች ለውጥን በማድረግ ስል ሆነው ወደ ሜዳ የተመለሱት የጦና ንቦቹ ተአምራዊ በሆነ መልኩ ውጤቱን ቀይረውታል። 47ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ዮናታን ኤልያስ በጥሩ የእግር ስራ ተቀባብሎ በመጨረሻም ከቴዎድሮስ ሀይለማርያም የደረሰውን ኳስ ቡድኑን ወደ ጨዋታ የመለች ጎል አክሏል። በብዙ ረገድ የተለወጡት እና በማጥቃት ደመ ነብስ አልቀመስ ያሉት ድቻዎች 52ኛው ደቂቃ ላይ የናትናኤል ናሲሩ ጥረት ታክሎ ከቀኝ ወደ ውስጥ የላከውን ኳስ ቴዎድሮስ ሀይለማርያም የአቻነት ጎል አድርጓታል።
- ማሰታውቂያ -
ግሩም ሀጎስን በአምስት ቢጫ ማጣታቸው የፈቱዲን ጀማል እና ታውላ ቲዎፍልን ጥምረት ማዋሀድ ያቃታቸው መቻሎች ዮናታን ኤልያስ ባስቆጠራት ሦስተኛ ጎል መመራት ጀምረዋል። 81ኛው ደቂቃ ናትናኤል ወደ ጎል መቶ በአግዳሚ ብረቱ ስትመለስ ሌላኛው ተቀይሮ የገባው ካርሎስ ዳምጠው ወደ 4ለ2 ቡድኑን አሸጋግሮ ጮቤ አስረግጧል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተሰጠው ጭማሪ ላይ 90+5 ላይ ቸርነት ጉግሳ ለመቻል ጎል ቢያስቆጥርም ጨዋታውን ከእጃቸው ያመለጣቸው መቻሎች 4ለ3 ለመሸነፍ ተገደዋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3-1 ፋሲል ከነማ
አሰልጣኝ አምሳሉ እስመለአለም ከቡድኑ ተጫዋቾች ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ባልመሩት ጨዋታ ፋሲል ከነማ 3ለ1 በሆነ ውጤት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መረታት ችለዋል። ዩጋንዳዊው አጥቂ ሳይመን ፒተር 25ኛው ደቂቃ ላይ ከሳምሶን ቹቹ የተቀበለውን ኳስ ጎል በማድረግ ሀምራዊ ለባሾቹን ቀዳሚ አድርጓል። ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል አሁንም ከቆሙበት የቀጠሉት ንግድ ባንኮች 73ኛው ደቂቃ ናትናኤል ዳንኤል ያመቻቸለትን ኳስ ከሴካፋ ከ17 አመት ቡድን የተገኘው ሁዘይፋ ሻፊ በሊጉም ለቡድኑም ሁለተኛ ጎል ማድረግ ችሏል። ሳምሶን ቹቹ ለንግድ ባንክ እንዲሁም አዲሱ ፈራሚ ታምራት እያሱ በበኩል ለፋሲል ከነማ በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ጎሎችን ካስቆጠሩ በኋላ ጨዋታው 3ለ1 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸናፊነት ተቋጭቷል።
ሀድያ ሆሳዕና 0-1 ባህርዳር ከተማ
ሀዋሳ ላይ ባህርዳር ከተማ ሀድያ ሆሳዕናን 1ለ0 በረታበት ጨዋታ ሊጉ ተመልሷል። በአንፃራዊነት የአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ባህርዳ የተሻለ በሆነበት የመጀመሪያው አጋማሽ 36ኛው ደቂቃ ሙሴ ካቤላ ሳጥን ውስጥ በእጅ ኳስን በመንካቱ የተሰጠን የፍፁም ቅጣት ምት ግርማ ዲሳሳ ወደ ጎልነት ለውጦ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። በቀጣዮቹም ደቂቃዎች ባህርዳሮች በዮሐንስ ደረጀ እና በአዲሱ ፈራሚ አንተነህ ተፈራ አማካኝነት ያለቀላቸውን ዕድል አግኝተው ማምከን ችለዋል። በጨዋታው መሐልም የሀድያ ሆሳዕና የቡድን አባላት ተደጋጋሚ ተቃውሞን ያሰሙ ሲሆን ቡድን መሪውም በቀይ ካርድ በዕለቱ ዋና ዳኛ ሔኖክ አበበ ተመዞባቸዋል።
ኢትዮጵያ መድን 0-1 አዳማ ከተማ
አዳማ ከተማ ተቸግሮም ቢሆን ሦስት ነጥብን ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል ከኢትዮጵያ መድን ላይ ወስዷል። በንፅፅር በመጀመሪያዎቹ ሀያ ደቂቃዎች አዳማዎች ጥሩ በነበሩበት አጋማሽ የኢትዮጵያ መድንን የጥንቃቄ ሽፋን ማስከፈት ከብዷቸው መመልከት የቻልን ሲሆን አጋማሹም በሙከራዎች የደመቀ አልነበረም።
መድኖች በይበልጥ ንቁ በነበሩበት ሁለተኛው አጋማሽ ያለቀላቸውን ዕድሎች ፈጥረው በአጨራረስ ድክመት የተነሳ ኳስን ከመረብ ማዋሀድ ግን አልቻሉም። ቢኒያም ዐይተን በአንድ አጋጣሚ ካደረጋት ሙከራ በስተቀር ብዙም ማጥቃቱ ላይ ብልጫን ያልወሰዱት አዳማዎች 61ኛው ደቂቃ ላይ የመድኑ የግብ ዘብ አቡበከር ኑራ አቡበከር ሳኒ ላይ ሳጥን ውስጥ በሰራው ጥፋት የዕለቱ ዳኛ አባይነህ ሙላት የሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ቢኒያም ዐይተን ከመረብ አገናኝቶ አዳማን 1ለ0 አሸናፊ እንዲሆን አስችሏል። በጨዋታ ላይ የዳኝነት ክፍተትን ያስተዋልን ሲሆን የመድኑ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ሐይሌም ብስጭታቸውን ሲገልፁ ተመልክተናል።


