አዲስ አበባ እና አዳማ ላይ በተደረጉ አራት ጨዋታዎች ሁለት ጨዋታዎች በመሸናነፍ ሲጠናቀቁ ቀሪዎቹ ነጥብ በመጋራት ተቋጭተዋል።
ነገሌ አርሲ 1-1 ወላይታ ድቻ
ወላይታ ድቻዎች በይበልጥ ከፍ ባሉ ፈጣን የሽግግር አጨዋወት የተሻሉ መሆን በቻሉበት የመጀመሪያው አጋማሽ በተጋጣሚያቸው ላይ ብልጫዎች ወስደው ቢታዩም በጠሩ ሙከራዎች ግን አጋማሽ መድመቅ ሳይችል ቀርቷል።
ከዕረፍት መልስ በመጠኑም ቢሆንም ጥሩ ፉክክርን ባየንበት አጋማሽ የጦና ንቦቹ በዮናታን ኤልያስ ነገሌ አርሲዎች በከቤ ብዙነህ የቅጣት ሙከራን አድርገው የግቡን የግራ ቋሚ ብረትን ለትማ ከተመለሰችዋ ኳስ በኋላ ከወትሮ እንቅስቃሴያቸው ደከም ብለው የታዩት ሰጎኖቹ ጎል አስቆጥረዋል። 83ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት አማካዩ ዳዊት ተፈራ ያሻማውን ኳስ ቁመታሙ ተከላካይ ሮሆቦት ሰለሎ በግንባር ገጭቶ የሰጠውን ገብረመስቀል ዱባለ ከመረብ አሳርፏታል። ጨዋታው ቀጥሎ መደበኛው ደቂቃ ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ 90+4 ላይ የነገሌው የቀኝ መስመር ተከላካይ ቦና ቦካ በሳጥን ውስጥ ኳስን በእጅ በመንካቱ የዕለቱ ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ምት ካርሎስ ዳምጠው እድሪሱ አብዱላሂ መረብ ላይ በማሳረፍ ጨዋታው በመጨረሻም 1ለ1 ተጠናቋል።
- ማሰታውቂያ -
ኢትዮ ኤሌክትሪክ 2-1 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ፈጣን የሆነ አጀማመርን ማድረግ የቻሉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ጎል ያስቆጠሩት ገና በጊዜ ነበር። 5ኛው ደቂቃ ላይ በሻሸመኔ ቆይታቸው በ2016 በተመሳሳይ መልኩ አሸናፊ ጥሩነህ አቀብሎ በጥሩ አጨራረስ ጎል አስቆጥሮ የነበረው እዮብ ገብረማርያም ዛሬም ያንኑ ያስታወሰች ጎል መረቡ ላይ በማሳረፍ ኤሌክትሪክን መሪ አድርጓል። የመጀመሪያዎቹን አስራ አምስት ደቂቃዎች በተጋጣሚያቸው ለመበለጥ ቢገደዱም በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ግን ተሽለው የታዩት ንግድ ባንኮች በተለይ በቅርቡ በሴካፋ ከ17 አመት በታች ቆይታን ባደረገው ሁዘይፋ ሻፊ ጥሩ የማቀበል ዕይታ በዩጋንዳዊው አጥቂ ሳይመን ፒተር ሙከራን ቢያደርጉም የግብ ዘቡ የሱፍ ሞሮ አምክኗታል።
ሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ጨዋታው አስደንጋጭ አጋጣሚን አሳይቶናል። የወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ ውስጥ በአሰልጣኝነት የሚያገለግለው አሰልጣኝ ኩመራ በቀለ የመጀመሪያ ልጅ የሆነው ኢብሳ ኩመራ ከመሬቱ ጋር ተጋጭቶ ምላሱ በመታጠፉ ሜዳ ላይ ከተደረገለት ህክምና በኋላ ለተጨማሪ ህክምና ወደ ሆስፒታል አምርቷል።
ለተጨማሪ ጎል ዕድል እንዳላቸው ሜዳ ላይ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ አንፃር ያሳዩን ኤሌክትሪኮች ቢመስሉም 66ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን አዲስ ግደይ አሻምቶ ከጉዳት መልስ ከሰሞኑ ቡድኑን እያገለገለ የሚገኘው አማካዩ ቢኒያም ካሳሁን ቆንጆ ጎል አድርጓት ጨዋታው 1ለ1 ሆኗል። ለመሸናነፍ ብርቱ ጥረቶች እየታዩበት የቀጠለው ጨዋታ 73ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ያሬድ የማነ ያሻማለትን ኳስ ከከፍተኛ ሊጉ መጥቶ ጥሩ አመትን እያሳለፈ የሚገኘው ሀሰን ሁሴን በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ጨዋታው በኢትዮ ኤሌክትሪክ 2ለ1 አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ ሆኗል።
ሸገር ከተማ 0-0 ፋሲል ከነማ
ግልፅ የሆኑ የግብ ዕድሎች ባልተፈጠሩበት በይበልጥ የኳስ ቅብብሎችን ብቻ ማየት የቻልንበት የመጀመሪያው አጋማሽ ጥራት ባላቸው ሙከራዎች የታጀበ መሆን ሳይችል ቀርቷል።
ከዕረፍት መልስ ብዙ መሻሻሎችን ይዞ መመለስ የቻለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 53ኛው ደቂቃ አወዛጋቢ ውሳኔን በዕለቱ ዋና ዳኛ ዳንኤል ይታገሱ አማካኝነት አስተውለናል። ቡልቻ ሹራ ከሳጥኑ የግራ ቦታ ኳስን ከፍ አድርጎ ለማለፍ ጥረት ሲያደርግ የአፄዎቹ ተከላካይ ዋሳዋ ጂኦፎሪ በእጅ ነክቷል በሚል የፍፁም ቅጣት ምት ቢሰጡም በዕለቱ አንደኛ ረዳት ዳኛ በሆኑት ፋሲካ የኋላሸት ውሳኔ ወደ ቅጣት ምት የተሸጋገረችዋን ኳስ ሔኖክ አዱኛ ቢመታትም የግብ ዘቡ ሞይስ ፓዎቴ ጥሩ ቅልጥፍና መክሸፍ ችላለች። በሌላ የሸገር ሙከራ ወጣቱ ቢኒያም መሐሪ አደገኛ ጥቃትን ሰንዝሮ ሞይስ ፓዎቴ ከመለሳት በኋላ 70ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲሉ አማካይ አቤኔዘር ዮሐንስ ቢኒያም መሐሪ ላይ በሰራው አደገኛ ጥፋት በአራተኛ ዳኛው ኤፍሬም ደበሌ ጥቆማ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከወጣ በኋላ የቀሩት ቀጣዮቹ ደቂቃዎች ጎሎች ሳያሳየን 0ለ0 ተቋጭቷል።
ሀድያ ሆሳዕና 3-1 ምድረ ገነት ሽረ
በቀኑ ከታዩት ጨዋታዎች ሁሉ በሁሉም ረገድ ከፊት ሊጠራ የሚችለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ሀያ ደቂቃዎች ሽረዎች ተሽለው መቅረባቸውን አስመልክተውናል። ዳንኤል ዳርጌ ባደረጋት ጥቃት ቀዳሚዎቹ ሞካሪዎች ሽረዎች ቢሆኑም እዮብ አለማየሁ ለሀድያ ሆሳዕና ሙከራን አድርጎ የግብ ዘቡ ሪችሞንድ አዩ ያመከነበት ጠጣሯ አጋጣሚ የነበረች ሲሆን 12ኛው ደቂቃ ላይ ግን ሽረዎች መሪ ሆነዋል። ከግራ የሜዳው ክፍል ተካልኝ ደጀኔ ለማሻማት በሚመስል መልኩ ወደ ጎል የላካት ኳስ የግብ ዘቡ አውሱ እንድሪውሱ ቦታውን ለቆ በመውጣቱ ኳሷ መረብ ላይ አርፋለች። በፈጣን መልሶ ማጥቃት ምላሽን ለመስጠት የታተሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች 45ኛው ደቂቃ በሳጥን ውስጥ ፀጋአብ ዮሐንስ እዮብ አለማየሁ ላይ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ብሩክ በየነ አቻ በማድረግ ጨዋታው ተጋምሷል።
እጅግ ከፍተኛ የመሸናነፍ ፉክክርን ባስተዋልንበት እና ተመስገን ብርሀኑ ተቀይሮ ገብቶ ልዩነት መፍጠር በቻለበት ሁለተኛው አጋማሽ ሀድያ ሆሳዕናዎች 50ኛው ደቂቃ ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል። ተመስገን ብርሀኑ በአግባቡ ያቀበለውን ኳስ በቅርቡ ወላጅ አባቱን በሞት ያጣው ኤልያስ አህመድ ወደ ግብነት ለውጧታል። ተመጣጣኝ በሚመስል ከፍ ያለ እንቅስቃሴን እያስተዋልን የሽረዎችን መጠነኛ ብልጫን ያየንበት ቀጣዮቹ ደቂቃዎች 58ኛው ደቂቃ ዳንኤል ዳርጌ ከግራ አሻምቶ ሽመክት ጉግሳ በግንባር ገጭቶ የግብ ዘቡ አውሱ እንዲሪውሱ በጥሩ ብቃት አውጥቶበታል። ተመስገን ብርሀኑን በገጠመው ጉዳት ቀይረው ለማስወጣት የተገደዱት ነብሮቹ 90+3 ላይ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ሱራፌል ተመስገን ግሩም የሆነች ጎልን አስቆጥሮ ጨዋታው በመጨረሻም 3ለ1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።


