በአዲስ አበባ እና አዳማ በተደረጉ አራት ጨዋታዎች መቻል ከተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ሲመለስ ቅዱስ ጊዮርጊስ በጎል ፌሽታ ደምቆ ተጋጣሚውን ረቷል። መሪው ሲዳማ ነጥብ ሲጥል ቡናማዎቹ እና ሐይቆቹ ነጥብ ተጋርተዋል።
አርባምንጭ ከተማ 0-2 መቻል
የመቻሎች የበላይነት ገዝፎ ከጅምሮ ገዝፎ በታየበት ጨዋታ አርባምንጮች ከይገዙ ቦጋለ የርቀት ሙከራ በስተቀር በተጋጣሚያቸው ጥቃቶችን ደጋግመው አስተናግደው። በጥልቅ እንቅስቃሴዎች በቸርነት ጉግሳ ሁለት ፣ በአለምብርሀን ይግዛው እና አብዱልከሪም ወርቁ አማካኝነት ያለቀላቸውን ሙከራዎች መቻሎች ፈጥረው የነበረ ቢሆንም በቶጓዊው የግብ ዘብ እድሪሱ ኦጎዶጆ ብርቱ ጥረቶች አዞዎቹ ጎል እንዳይቆጠርባቸው ሆኗል።
ከዕረፍት መልስ ፈጣን በሆኑ ሽግግሮች ወደ ውስጥ ተስቦ በመጫወት አንዳች ነገርን ለመፍጠር ጥረት ማድረጋቸውን የቀጠሉት ጦረኞቹ እንደነበራቸው የእንቅስቃሴ ብልጫ 68ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አግኝተዋል። 68ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ደምቆ መታየት የቻለው አለምብርሀን ይግዛው ወደ ሳጥን ኳስን ይዞ ሲገባ በተከላካዩ አካሉ አትሞ ጥፋት ስለተሰራበት የዕለቱ ዋና ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ምት ቸርነት ጉግሳ ከመረብ አዋህዶ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። ጨዋታው ቀጥሎ ሊጠናቀቅ በተሰጠው ጭማሪ አምስት ደቂቃዎች ውስጥ 90+1 ደቂቃ ላይ አለምብርሀን ይግዛው በጥሩ ዕይታ ያመቻቸለትን ኳስ ተቀይሮ የገባው ዩጋንዳዊው አጥቂ ቻርለስ ሙሴጌ እድሪሱ መረብ ላይ አስቀምጧታል። ጨዋታው ሊገባደድ ሲቃረብ በሌላ አጋጣሚ የአብስራ ተስፋዬ ከአለምብርሀን የተቀበለውን ኳስ መጠቀም ሳይችል በመጨረሻም ጨዋታው መቻልን ከሦስት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ወደ ድል መልሷል።
- ማሰታውቂያ -
ቅዱስ ጊዮርጊስ 4-0 ድሬዳዋ ከተማ
ተመጣጣኝ የሚመስል አጀማመርን ማየት ብንችልም በሂደት ግን የቅዱስ ጊዮርጊሶች የበላይነትን መታየት በቻለበት ጨዋታ 16ኛው ደቂቃ ላይ ነበር ጎል መቆጠር የቻለው። የድሬዳዋው ተከላካይ የአብስራ ሙሉጌታ የተሳሳተውን ኳስ ያገኘው ተገኑ ተሾመ ጥሩ በሆነ መልኩ ሲያቀብለው ወጣቱ አማካይ ሀብታሙ ጉልላት ከቀኝ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ጎሉን መረቡ ላይ አዋህዷል። በጎሉ መመራታቸው ድንጋጤ ውስጥ የከተታቸው ብርቱካናማዎቹ ይባስ ብለው 22ኛው ደቂቃ ላይ አማካዩ ሔኖክ ሀሰን የአብስራ ጎሳዬ ላይ በሰራው ጥፋት የዕለቱ ዋና ዳኛ ሙሉቀን ያረጋል በቀጥታ ቀይ ሊያሰናብቱት ችለዋል። 35ኛው ደቂቃ ላይ ቶሎሳ ንጉሴ ከቀኝ ወደ ውሰጥ ሲያሻማ አብዱሰላም የሱፍ ኳስን በእጅ በመንካቱ በዕለቱ ሁለተኛ ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው ዕገዛ የተገኘን የፍፁም ቅጣት ምት አቤል ያለው አስቆጥሯታል።
ከዕረፍት መልስ ከቆሙበት የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 49ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ አቤል ያገኘውን ኳስ ከፍ በማድረግ ሲሰጠው ፍፁም ጥላሁን በግንባር ገጭቶ የአብዩ ካሳዬ መረብ ላይ ሦስተኛዋን ጎል አገናኝቷል። በጎልም ሆነ በተጫዋች የቁጥር ብልጫ ተወስዶባቸው ጨዋታውን የቀጠሉት ድሬዳዋ ከተማዎች 88ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ያለው የተሰነጠቀለትን ኳስ አህመድ ረሺድን በፍጥነት ቀድሞ አስደናቂ ጎል በማስቆጠር ጨዋታው በመጨረሻም በፈረሰኞቹ 4ለ0 በሆነ አሸናፊነት ተቋጭቷል።
ኢትዮጵያ ቡና 1-1 ሀዋሳ ከተማ
ጥሩ ፉክክርን ከጅምሩ ያስመለከተን ጨዋታ ሻባን መሐመድ ለኢትዮጵያ ቡና ሽመልስ በቀለ እና አብነት ደምሴ ለሀዋሳ ጠጣር የሆኑ ሙከራዎችን ቢያደርጉም በተሻለ የማጥቃት ደመ ነብስ የተሞሉት ቡናማዎቹ 38ኛው ደቂቃ ናይጄሪያዊው አማካይ ዲቫይን ዋቹኩዋ ከወጣቱ ናትናኤል ፍሬው ያገኛትን ኳስ ወደ ጎልነት በድንቅ አጨራረስ አስቆጥሮ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።
ከዕረፍት መልስ ኢትዮጵያ ቡናዎች የበላይ ሆነው በቀረቡበት አጋማሽ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሰንዝረው ሌላ የግብ ዕድል ያመለጣቸው ሲሆን ጨዋታው ተጠናቆ በተሰጠው የጭማሪ ደቂቃ ላይ 90+3 ላይ ከእጅ ውርወራ መነሻዋን አድርጋ ጌታነህ ከበደ ከተባረከ ሄፋሞ የተቀበለውን ኳስ የቡናማዎቹ የመከላከል ስህተት ታክሎ ሀዋሳን አቻ በማድረግ 1ለ1 ጨዋታው ተቋጭቷል።
አዳማ ከተማ 2-2 ሲዳማ ቡና
አጀማመራቸው ተቀራራቢ ቢመስልም ወደ ግራ በማዘንበል መስፍን ታፈሠን ለመጠቀም አልመው የተጫወቱት ሲዳማ ቡናዎች 16ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን አሻምቶ ብርሀኑ በቀለ በግንባር ጨርፎለት መስፍን ታፈሠ ተንሸራቶ ቀዳሚዋን ጎል አስቆጥሯል። በእንቅስቃሴ ብልጫ ባይወሰድባቸውም በተቃራኒው ጎል አካባቢ ሲደርሱ ደካማ ሆነው የታዩት አዳማዎች 44ኛው ደቂቃ ፍቅረየሱስ ከደግፌ ያገኘውን ኳስ በጥሩ ዕይታ ሰጥቶት ሳጥን ውስጥ ኳሷን ያገኘው መስፍን ታፈሠ ለራሱም ሆነ ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አድርጓታል። ቢኒያም አይተን ከአንድ ደቂቃ በኋላ ጥሩ አጋጣሚን ለአዳማ ፈጥሮ የግብ ዘቡን በቀላሉ አሳቅፎታል።
ከዕረፍት መልስ 55ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች በሰሩት ስህተት አቡበከር ሳኒ አዳማን ወደ ጨዋታ የመለሰች ጎል አስቆጥሯል። ጨዋታው ከፍ ባለ ተነሳሽነት ቀጥሎ ሊጠናቀቅ በተሰጠው ጭማሪ 90+1 ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻማን ኳስ ሙጂብ ቃሲም በእግር ኳስ ህይወቱ መነሻ የነበረው አሳዳጊ ክለቡ መረብ ላይ አሳርፎ አዳማን አቻ አድርጓል። ተጫዋቹም ጎሏን አስቆጥሮ ደስታውን ሲገልፅ በቀደመ ክለቡ ደጋፊዎች ተቃውሞን አስተናግዷል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ በሁለት ደቂቃ ልዩነት ውስጥ ቢኒያም አይተን ለአዳማ ብርሀኑ በቀለ ለሲዳማ ካደረጓቸው እና ብረት በተመሳሳይ ከመለሳቸው ሙከራዎች በኋላ ጨዋታው ተጠናቋል።


