ነገሌ አርሲ ማስገረሙን ሲቀጥል ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል
የሳምንቱ የመክፈቻ ቀን መርሀግብር መሪው ሲዳማ ቡና ነጥብ ሲጥል የከቤ ብዙነህ ምትሀት ለነገሌ አርሲ ወሳኝ ድል አስገኝቷል የወልዋል እና አዳማ ጨዋታ ደግሞ 1ለ1 ተጠናቋል።
ምድረገነት ሽረ 0-1 ነገሌ አርሲ
በፌድራል ዋና ዳኛ አባይነህ ሙላት መሪነት በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በተለመደው እንቅስቃሴ ከቆሙበት የቀጠሉት ነገሌ አርሲዎች መሐል ለመሐል እና በሽግግር ከግራ ከቤ ብዙነህ በመጠቀም በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ ባለው እንቅስቃሴ የበላይነቱን በመውሰድ 12ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ማስቆጠር ችለዋል። ከቀኝ በረጅሙ አማካዩ ዳዊት ተፈራ የተቆጣጠራትን ኳስ በጥሩ ዕይታ ወደ ግራ ያቀበለውን ኳስ የሊጉ አዲሱ ክስተት ከቤ ብዙነህ በጥሩ አጨራረስ እየነዳ ገብቶ ወደ ጎልነት ለውጦ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። ከጎሏም በኋላ ከቤ ከግራ አሻምቶ ምስጋናው መላኩ በግንባር ገጭቶ የግቡ አግዳሚ ብረት አግዶበታል። ከሰሞነኛ አቀራረባቸው መጠነኛ መውረድ የታነባቸው ስሑል ሽረዎች ጥቂት የማጥቃት ተነሳሽነትን ቢያሳዩም በተጋጣሚያቸው የመከላከል አቅም ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።
- ማሰታውቂያ -
በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ መሻሻልን ይዘው ወደ ሜዳ የገቡት ምድረገነት ሽረዎች በይበልጥ ለሳጥኑ በመጠጋት በአጥቂው አቤል ማሙሽ አማካኝነት ጥቃት ሰንዝረዋል ፣ በተለይ የግብ ዘቡ እድሪሱ አብዱላሂ የግብ ክልሉን ለቆ ወጥቶ ወደ ጎል ሞክሮ ለጥቂት የወጣችበት አጋጣሚ ከተሞከሩት ሻል ያለችው ነበረች። በመልሶ ማጥቃት ከቤን ማዕከል በማድረግ ነገር ግን ለኋላ ክፍላቸው ጥንቃቄን መርጠው የተጫወቱት ነገሌ አርሲዎች በከቤ ብዙነህ አማካኝነት ተጨማሪ ጎል ሊሆኑ የሚችሉ ዕድሎችን ቢያገኙም መቆጠር ሳይችል በመጨረሻም ጨዋታው 1ለ0 በሆነ ውጤት ተቋጭቷል። በአሰልጣኝ ቱሉ ደስታ የሚመሩት እና ባደጉበት አመት ማስገራማቸው የቀጠሉት ነገሌዎች አራተኛ ተከታታይ ድላቸውን ወደ ካዝናቸው በመክተት በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ላይ በሀያ አምስት ነጥቦች መቀመጥ ችለዋል።
ወልዋሎ ዓ/ዩኒቨርስቲ 1-1 አዳማ ከተማ
ሌላኛው በአዲስ አበባ ስታዲየም የተደረገው ሁለተኛው መርሀግብር በበርካታ ጥፋቶች ታጅቦ በቀዳሚው አጋማሽ ወልዋሎዎች እንደነበራቸው ብልጫ 21ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥረዋል። ሳዲቅ ዳሪ በሳጥኑ ጠርዝ ዳዊት ገብሩ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የቅጣት ምት ኪሩቤል ወንድሙ መቶ ናትናኤል ተፈራ መረብ ላይ በማሳረፍ ቢጫዎቹን ቀዳሚ አድርጓል። በአጋማሹ የተዳከመ እንቅስቃሴን ያሳዩት አዳማዎች በተጋጣሚያቸው እየተመሩ አጋማሹ ተገባዷል።
ከዕረፍት መልስ ተመጣጣኝ የሚመስል ብዙ ሙከራዎችን ያላሳየን አጋማሽ በፈጣን ሽግግር ወልዋሎ በጥልቀት በመጫወት አዳማ ሜዳ ላይ የነበራቸው ቅርፅ ሲሆን 74ኛው ደቂቃ ላይ አዳማዎች አቻ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል። ከግራ የሳጥኑ ክፍል ፍቃዱ መኮንን ቢኒያም ዐይተን ላይ በሰራው ጥፋት የዕለቱ ዳኛ ሔኖክ አክሊሉ የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ቢኒያም አክሎ በመጨረሻም ጨዋታው 1ለ1 ተጠናቋል።
ሲዳማ ቡና 0-0 አርባምንጭ ከተማ
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ በተቃራኒው ተቀምጠው የሚገኙት ሲዳማ ቡና እና አርባምንጭ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ እንዲሁ በጥቅል በጠሩ የግብ ዕድሎች መድመቅ የቻለ አልነበረም። በመጀመሪያው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች 8ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ታደሠ በቄንጠኛ ሙከራን አድርገው እድሪሱ አብዱላሂ የያዘበት እና 44ኛው ደቂቃ ላይ ዮሴፍ ዮሐንስ ከሳጥን ውጪ ኢላማዋን መጠበቅ ያልቻለች ሙከራን ከማድረጉ ውጪ አጋማሹ የተለየ ነገር አላስመለከተንም ነበር።
ከዕረፍት ተመልሶ በተመሳሳይ አቀራረብ የቀጠለው የቡድኖቹ ጨዋታ ፍቅረየሱስ ለሲዳማ እንዲሁም አርባምንጮች መጠነኛ መሻሻልን ባሳዩበት የመጨረሳዎቹ ሀያ ደቂቃዎች በፍቅር ግዛቸው ከይገዙ ያገኘውን ነፃ ኳስ በዮሴፍ የተነጠቀበት እና በመጨረሻ ደቂቃ ያለቀለት ዕድል በድጋሚ አዞዎቹ አግኝተው ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው 0ለ0 ለመጠናቀቅ ተገዷል።


