አዲስ አበባ ላይ የተደረጉት ጨዋታዎች ግብ ሳይቆጠርባቸው ተጠናቀዋል
በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ13ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ሲደረጉ አዲስ አበባ ላይ የተደረጉት ጨዋታዎች ያለ ግብ ተጠናቀዋል።
በቀዳሚነት ከቀን 07:00 ጀምሮ የተደረገው የአዳማ ከተማ እና የፋሲል ከነማ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ የአዳማ ከተማ የበላይነት የታየበት ነበር።
በአጋማሹ ከተጋጣሚያቸው በተሻለ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቻሉት አዳማ ከተማዎች ኳስ እና መረብ ማገናኘት የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።
- ማሰታውቂያ -
የመጀመሪያ ሙከራቸውን በ4ኛው ደቂቃ ላይ ያደረጉም ሲሆን ነቢል ኑረዲን ያደረገውን ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ሞይስ ፓወቲ ግብ ከመሆን አድኖታል።
በቀላሉ ወደ አዳማ ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ የተቸረጉት ፋሲል ከነማዎች በ22ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ አማኑኤል ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመታው ኳስ ቀዳሚ ሙከራቸውን አድርገዋል።
በዘንድሮው የውድድር ዘመን የፋሲል ከነማ ጉዞ ጉልህ ሚና በመወጣት ላይ ከሚገኙት ተጫዋቾች መካከል ቀዳሚ የሆነው በረከት ግዛው ባጋጠመው ጉዳት በ24ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል።
የስዩም ከበደው ቡድኑ የማጥቃት ብልጫውን ወስዶ በቀጠለባቸው ቀጣይ ደቂቃዎች ላይ በተለይም የቀኝ መስመር ተከላካዩ አብደልከሪም መሐመድ ወደ ሳጥን በሚያሻግራቸው ኳሶች ተደጋጋሚ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲጥሩ ተስተውሏል።
በ27ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን ከቢንያም አይተን የተቀበለውን ኳስ የፋሲል ከነማ ተከላካዮችን ሸውዶ በማለፍ ከሞይስ ፓወቲ ጋር ፊት ለፊት ቢገናኝም ኳስ እና መረብን ማገናኘት ሳይችል ቀርቷል።
በአጋማሹ ለዮሐንስ ሳህሌው ቡድን አስቆጪ በነበረው የግብ ሙከራ ያሬድ ብርሀኑ በረጅም የተላከለትን ኳስ ተቆጣጥሮ የግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስ መውጣትን ተከትሎ ከፍ አድርጎ ወደ ግብ የላከው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል።
በ44ኛው ደቂቃ ላይ ሀይደር ሸረፋ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ነቢል ኑረዲን በግንባር ወደ ግብ ልኮ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት እና በ45+1 ላይ ቢንያም አይተን ከግብ ጠባቂው ትይዩ ተገኝቶ ሳይጠቀምበት የቀሯቸው ኳሶች ለአዳማ ከተማዎች የአጋማሹ ሌሎች የግብ ዕድሎች የተፈጠሩባቸው አጋጣሚዎች ናቸው።
በሁለተኛው አጋማሽም የአዳማ ከተማ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲቀጥል በተለይም በግራ መስመር በኩል የፋሲል ከነማን የኋላ ክፍል ሰብረው ለመግባት ጥረቶችን አድርገዋል።
በፋሲል ከነማ በኩል በረጃጅም ኳሶች እና በሽግግር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ ለማጥቃት ያደረጓቸው ሙከራዎች በአጋማሹ ተስተውለዋል።
በሀዋሳ ከተማ ሳለ ከሳጥን ውጪ በሚያስቆጥራቸው ግቦች የሚታወቀው አቤኔዘር ዮሐንስ በ51ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ጠንካራ የግብ ሙከራ ለጥቂት ከግቡ አግዳሚ በላይ ወጥቷል።
በጨዋታው 69ኛ ደቂቃ ላይ የአዳማ ከተማው የመሀል ተከላካይ መናፍ አወል ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት ጨዋታውን አቋርጦ ወጥቷል።
በ71ኛው ደቂቃ ላይ ቃልኪዳን ዘላለም ከዳግም አወቀ የደረሰውን ግሩም ኳሶ ተጠቅሞ ግብ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ግብ ጠባቂው ቀድሞት ደርሶ ኳሱን አውጥቶታል።
በአዳማ ከተማ በኩል በአብዛኛው በግራ መስመር ያደላው የማጥቃት እንቅስቃሴ ይህ ነው ሊባል የሚችል ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራን ሳያስተናግድ ጨዋታው ተጠናቋል።
በ14ኛው ሳምንት ፋሲል ከነማ ከኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም አዳማ ከተማ ደግሞ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ይጫወታሉ።
ከ10:00 ጀምሮ የተደረገው እና ቀዝቀዝ ያለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በታየበት ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወልዋሎ አዲግራት ነጥብ ተጋርተዋል።
በቀዳሚው አጋማሽ ወልዋሎ አዲግራቶች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ወደ ሶስተኛው ዞን የሜዳ ክፍል መድረስ ቢችሉም ጠንካራ ሙከራዎችን ግን ማድረግ አልቻሉም።
በ34ኛው ደቂቃ ላይ ኮንኮኒ ሀፍዝ በሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ አክርሮ በመምታት ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣበት በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ በኩል የተመለከትነው ሙከራ ነበር።
በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ደግሞ በ42ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ የማነ ለግቡ ቅርብ ሆኖ ያገኘውን ኳስ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ እንኳን ማድረግ ሳይችልበት ቀርቷል።
በሁለተኛው አጋማሽ ወልዋሎ አዲግራቶች በማጥቃት እንቅስቃሴ ተሽለው ቢቀጥሉም ከ65ኛው ደቂቃ በኋላ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ተጭነው ለመጫወት ችለዋል።
በተመሳሳይ ጠንካራ የግብ ሙከራዎች እምብዛም ባልነበሩት አጋማሹ ተቀይሮ የገባው እዮብ ገብረማርያም ከሳጥን ውጪ ያደረገው የ71ኛው ደቂቃ ከባድ ሙከራ በሙታክብዋ ጆኤል ተይዟል።
በወልዋሎ አዲግራት በኩል በ90+4ኛው ደቂቃ ላይ ጌትነት ተስፋዬ ያገኘውን አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
በ14ኛው ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከድሬዳዋ ከተማ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ደግሞ ከአዳማ ከተማ ይጫወታሉ።


