ነገሌ አርሲ እና አዳማ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል
በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ12ኛ ሳምንት የሁለተኛ ዕለት የአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታዎች ነገሌ አርሲ እና አዳማ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል።
በቀዳሚነት ከ07:00 ጀምሮ በተደረገው ጨዋታ ነገሌ አርሲ ድሬዳዋ ከተማን 3 ለ 0 አሸንፏል።
በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴ በታየበት የጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ዕድሎችን ፈጥረዋል።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታውም የመጀመሪያው ግብ የተገኘው በአስረኛው ደቂቃ ላይ በነገሌ አርሲ በኩል ነበር።
አስደናቂ የውድድር ዘመን እያሳለፈ የሚገኘው ከቤ ብዙነህ ከሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ የቀነሰለትን ኳስ ሐቢብ ከማል ግብ አድርጎታል።

ከግቡ በኋላ ድሬዳዋ ከተማዎች ከራሳቸው የሜዳ ክፍል በመነሳት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢጥሩም የነገሌ አርሲው የግብ ዘብ እድሪሱ አብዱላሂን የፈተኑ አልነበሩም።
የሚነጥቋቸውን ኳሶች በፈጣን ሽግግር ወደ ድሬዳዋ ከተማ ሳጥን የሚያደርሱት ነገሌ አርሲዎች በ26ኛው እና በ33ኛው ደቂቃዎች ላይ በከቤ ብዙነህ አማካይነት ጠንካራ የግብ ሙከራዎችን አድርገው የነበረ ቢሆንም አብይ ካሳዬ ግብ ከመሆን አድኗቸዋል።
በቀጣዮቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች ላይ መሐመድኑር ናስር እና አቤል ነጋሽ ጥሩ አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም ኳሱን ከመረብ ውስጥ መቀላቀል አልቻሉም።
በሁለተኛው አጋማሽ የድሬዳዋ ከተማ ጫና ተጠናክሮ ሲቀጥል ነገሌ አርሲዎች በጥብቅ መከላከል ግባቸውን ሲጠብቁ በፈጣን እና ረጃጅም ኳሶች ደግሞ ዕድሎች ፈጥረዋል።
አጋማሹ በጀመረ በሰከንዶች ውስጥ አቤል ነጋሽ በግቡ ትይዩ በቅርብ ርቀት ያገኘውን ኳስ ከግቡ አግዳሚ በላይ ልኮታል።
በ64ኛው ደቂቃ ላይም አቤል ነጋሽ በተመሳሳይ ከሳጥን ውስጥ ግብ የማስቆጠር ዕድልን ቢያገኝም እድሪሱ አብዱላሂ አድኖበታል።
በረጃጅም ኳሶች የድሬዳዋ ከተማ ተከላካዮች ጀርባ ላይ ያለውን ቦታ ለመጠቀም ሲጥሩ የቆዩት ነገሌ አርሲዎች በ78ኛው ደቂቃ ላይ የናትናኤል ሰለሞን ድንቅ አጨራረስ በታየበት ግብ መሪነተቻውን ወደ 2 ለ 0 ከፍ አድርገዋል።
የጨዋታው መጠናቀቂያ የፊሽካ ድምፅ በሚጠበቅበት ጊዜም የድሬዳዋ ከተማ ተከላካዮች ስህተትን ተጠቅሞ አለኝታ ማርቆስ የነገሌ አርሲን 3ኛ ግብ አስቆጥሮ ነገሌ አርሲን የ3 ለ 0 አሸናፊ አድርጓል።
ውጤቱንም ተከትሎ ቡድኑ ነጥቡን 19 ማድረስ ሲችል ድሬዳዋ ከተማ በነበረው 16 ነጥብ ለመቆየት ተገዷል።
በ13ኛው ሳምንት ነገሌ አርሲ ከመቻል እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ ከባህርዳር ከተማ ይጫወታሉ።
ከ10:00 ጀምሮ በተደረገው ጨዋታ ደግሞ አዳማ ከተማ ምድረ ገነት ሽረን 1 ለ 0 ረቷል።
በሁለቱም በኩል ቀድሞ የጨዋታውን ግብ ለማስቆጠር ጥረቶች በታዩበት ጨዋታው በተለይም የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ግቦች የሚስተናገዱበት ይመስል ነበር።
በጨዋታ እንቅስቃሴ አዳማ ከተማዎች በአንፃራዊነት የተሻሉ ዕድሎች መፍጠር የቻሉ ሲሆን በምድረ ገነት ሽረ በኩል በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ በመሆን የማጥቃት ሂደታቸው ይቋረጥ ነበር።
የጨዋታው የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ በ12ኛው ደቂቃ ላይ የተደረገ ሲሆን ሳዲቅ ኑሩ ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ ሪችሞንድ አይ መልሶታል።
በአዳማ ከተማ በኩል አህመድ ሁሴን ከነቢል ኑሪ የደረሰውን ድንቅ ኳስ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ያመከነበት እና የአቡበከር ሳኒ መነሻውን ከማዕዘን ምት ያደረገ ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ በሪችሞንድ አይ የተመለሰበት ኳሶች ተጠቃሽ ናቸው።
በምድረ ገነት ሽረ በኩል በአጋማሹ የመጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ በሽመክት ጉግሳ አማካይነት ያደረጉት ሙከራ እና ዳንኤል ዳርጌ በረጅም የተላከለትን ኳስ አላዛር ማርቆስ ከግቡ ወጥቶ እንዳይጠቀም ያደረገበት አጋጣሚዎች ተጠቃሽ ናቸው።
በሁለተኛው አጋማሽ በድጋሚ በፈጣን እንቅስቃሴ ጨዋታው ሲቀጥል ጠንካራ የግብ ሙከራዎችን ለመመልከት ግን ደቂቃዎች መጠበቅ የግድ ብሎ ነበር።
በ56ኛው ደቂቃ ላይ ቢንያም አይተን ከአብድልከሪም መሐመድ የደረሰውን ኳስ ለአህመድ ሀሱን በጥሩ መልኮ ቀንሶለት የነበረ ቢሆንም ጠንካራ ያልሆነው የአህመድ የግብ ሙከራ በሪችሞንድ አይ በቀላሉ ተይዟል።
ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ የዳንኤል ዳርጌ ብልጠት በታየበት የማጥቃት ሂደት ራሱ ዳንኤል ዳርጌ ኳሱን መልሶ አግኝቶ ያደረገው ጠንካራ ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል።
ጠንካራ ካሉ የግብ ሙከራዎች የተራራቀው ጨዋታው 85ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግብ አስተናግዷል።
የአዳማ ከተማ ቁልፍ ተጫዋች የሆነው ቢንያም አይተን በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ ከቡድን አጋሩ የደረሰውን ኳስ ገፍቶ ወደ ሳጥን በመግባት ቡድኑም አሸናፊ ያደረገ ግብ አስቆጥሯል።
በውድድር ዓመቱ 5ኛ ድሉን ያሳካው አዳማ ከተማ የዛሬ ድሉን ተከትሎ ነጥቡን 20 ያደረሰ ሲሆን ምድረ ገነት ሽረ በነበረው 14 ነጥቦች ላይ ለመቆየት ተገዷል።
በ13ኛው ሳምንት አዳማ ከተማ ከፋሲል ከነማ ምድረ ገነት ሽረ ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ጨዋታዎቻቸውን ያደርጋሉ።


