ሲዳማ ቡና በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠሩ ጎሎች ሸገርን 2ለ0 በመርታት ወደ ሊጉ መሪነት ሲመለስ ሀድያ ሆሳዕና ተከታታይ ሦስተኛ ድሉን ሀዋሳ ላይ አስመዝግቧል።
ሀድያ ሆሳዕና 1-0 ሀዋሳ ከተማ
ሀዋሳ ከተማዎች ከወትሮ እንቅስቃሴያቸው ትዕግስትን መርጠው ለመጫወት ጥረት ባደረጉበት የመጀመሪያው አጋማሽ ከፍ ባለ የሽግግር እንቅስቃሴ መጫወትን መርጠው በታዩት ሀድያ ሆሳዕናዎች የሙከራ ብልጫው ተወስዶባቸው ያስተዋልን ሲሆን በዚህም የጨዋታ መንገድ ጎልን 22ኛው ደቂቃ ላይ መመልከት ችለናል። ሄኖክ አርፊጮ ከግራ የራሳቸው ሜዳ በረጅሙ በቀኝ የሜዳው ክፍል ያሻገራትን ኳስ የሀዋሳውን ተከላካይ ብሩክ ታደለን ጀርባውን ገጭታ የተመለሰች ኳስን እዮብ አለማየሁ ከኤልያስ አህመድ ጋር ተቃብሎ ያቀበለውን ኳስ ጫላ ተሺታ ወደ ጎልነት ለውጦ ነብሮቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከጎሏ መቆጠር በኋላ በሀድያ ሆሳዕና በኩል በተደረገ ሌላ ሙከራ ሄኖክ አርፊጮ ከቅጣት አሻምቶ ናትናኤል ሻጋሞ በራሱ ላይ በግንባር ገጭቶ ለማስቆጠር የተቃረበበት አጋጣሚ በአጋማሹ ሌላኛው በጥራት የተሞላች ሙከራ ሆናለች።
ከዕረፍት መልስ መጠነኛ መሻሻልን ይዘው ሀዋሳዎች መመለስ በቻሉበት አጋማሽ የመጨረሻው ሜዳ ላይ ግን አሁንም የግብ ዕድሎችን መፍጠር ላይ ደካሞች ነበሩ። ሀድያ ሆሳዕናዎች በአንድ ለአንድ ግኖኙነት በተመስገን ብርሀኑ ጥቃት ሰንዝረው ሰይድ ሀብታሙ ካዳናት በኋላ ሀዋሳዎች አብነት ደምሴ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ የግብ ዘቡ ያሬድ በቀለ ያዳናት እና ቢኒያም በላይ ከማዕዘን አሻምቶ ያሬድ ከያዛት ሌላ ሙከራ በኋላ ጨዋታው በመጀመሪያ አጋማሽ የሀድያ ሆሳዕና ብቸኛ ጎል 1ለ0 ተቋጭቷል።
- ማሰታውቂያ -
ሲዳማ ቡና 2-0 ሸገር ከተማ
ፌድራል ዋና ዳኛ ዳንኤል ግርማይ በመሩት የምሽቱ መርሀግብር ሲዳማ ቡናዎች በይበልጥ ለሳጥኑ በመጠጋት በድግግሞሽ ጥቃት ለመሰንዘር ጥረት ማድረግ የቻሉበት ቢሆንም ጥቅጥቅ ባለ መከላከል ጎሎች እንዳይቆጠርባቸው ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ሸገር ከተማዎች በተጋጣሚያቸው ብልጫ ቢወሰድባቸው ጎል ሳይቆጠርባቸው ጨዋታ ተገባዷል።
ከዕረፍት በተመለሰው ጨዋታ ሲዳማ ቡናዎች ከመስመር በሚነሱ ማጥቃቶቻቸው ከቆሙበት እንቅስቃሴ መቀጠል የቻሉ ሲሆን በተለይ ፍቅረየሱስ እና መስፍን በሚያደርጓቸው ተደጋጋሚ የመጨረሻው ሜዳ የአንድ ለአንድ የበላይነት የሸገር ከተማ የተጫዋቾች ግላዊ ስህተት ታክሎባቸው ግብ ወደ ማስቆጠሩ መጥተዋል። 52ኛው ላይ ከሔኖክ አዱኛ እግር ስር መስፍን ታፈሠ የነጠቀውን ኳስ ወደ ሳጥን መሬት ለመሬት ሲያሻግር ብለስ ናጎ በሁለት እጎሩ መሐል ሾልካ የደረሰችውን ኳስ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ከመረብ አሳርፎ ሲዳማ ቡናን ቀዳሚ አድርጓል።
ተመስገን ከቅጣት በሚገርም ዕይታ ሞክሮ ባህሩ ያዳነበት እና ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ካመለጠችው ዕድል በኋላ 79ኛው ደቂቃ ላይ የሸገሩ ተከላካይ በተሳሳተ መንገድ ያቀበለውን ኳስ ተመስገን በጅሮንድ በአግባቡ ሰጥቶት መስፍን ታፈሠ በድንቅ አጨራረስ ጎል በማድረግ ሲዳማ ቡናን 2ለ0 አሸናፊ ሆኖ ወደ ሊጉ መሪነት እንዲመለስ አስችሏል።


