የአስረኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ሦስት ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ተፈፅመዋል።
ድሬዳዋ ከተማን ከአዳማ ከተማ ያገናኘው የአዲስ አበባ ስታዲየም ቀዳሚው መርሀግብር በአቻ ውጤት ተቋጭቷል። ድሬዳዋ ከተማዎች 27ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ጀሚል ያዕቆብ ያሻገረለትን ኳስ አማካዩ ያሬድ ታደሠ ከሳጥን ውጪ ያስቆጠራት ኳስ ቡድኑን መሪ ብታደርግም ከሦስት ደቂቃዎች መልስ ግን ብዙአየዎ ሰይፈ ሰጥቶት ጋናዊው አጥቂ ማይክል ኪፕሮፕ ወደ ጎል ሞክሮ የግብ ዘቡ አብዩ ካሳዬ ሲመልሳት ወጣቱ አጥቂ ነቢል ኑሪ ወደ ጎልነት ለውጦ ጨዋታው በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ጎሎችን ቡድኖቹን 1ለ1 አለያይቷል።

ከዚህ ቀጥሎ ሁለቱን የመዲናይቱ ክለቦች መቻል እና ኢትዮ ኤሌክትሪክን ያፋለመው ጨዋታ ያለ ጎል ሲጠናቀቅ በአዳማ ሳይንስ እና ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሊጉን መሪ ሲዳማ ቡናን ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አገናኝቶ የነበረው ጨዋታ በመጨረሻው ደቂቃ ፈረሰኞቹ ያገኟት ጎል በአቻ ውጤት እንዲፈፅሙ አድርጓቸዋል። ግለቱ ከፍ ብሎ በታየው እና ሲዳማ ቡናዎች በይበልጥ ለሳጥኑ ተጠግተው በተንቀሳቀሱበት መርሀግብር ተመስገን በጅሮንድ በመጀመሪያው አጋማሽ ከቅጣት ምት ወደ ሳጥን ያሻረውን ኳስ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ ፍፁም ጥላሁን በራሱ መረብ ላይ በግንባር ገጭቶ ሲያስቆጥር ጨዋታው በሲዳማ አሸናፊነት ተጠናቀቀ ተብሎ ሲጠበቅ 90ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን ሽግግር አማካዩ ሀብታሙ ጉልላት አስደናቂ ጎልን ዩጋንዳዊው ግብ ጠባቂ ኢማኑኤል ካል መረብ ላይ አስቀምጦ ጨዋታው በመጨረሻም 1ለ1 ተቋጭቷል።
- ማሰታውቂያ -
በዚህ ሳምንት የጀመረው የአስረኛ ሳምንት መርሐግብሮች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አርባምንጭን ወላይታ ድቻ ሸገርን በተመሳሳይ 3ለ1 ሲረቱ ሀድያ ሆሳዕና መቐለን 2ለ1 ፋሲል ከነማ ነገሌ አርሲን 1ለ0 ሲረቱ ምድረገነት ሽረ ከባህርዳር ያለ ጎል ወልዋሎ ከኢትዮጵያ ቡና 1ለ1 መፈፀማቸው ይታወሳል። በሳምንቱም አርባምንጭ እና መቐለ አሰልጣኞቻቸውን ሲያሰናብቱ ሊጉም የዳኝነት ክፍተትን በጉልህ አስመልክቶን ተገባዷል።


