ሲዳማ ቡና ፣ ፋሲል ከነማ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ ቡና ባለ ድል ሆነዋል።
መቻል 1-2 ሲዳማ ቡና
ፈጣን አጀማመርን ያደረጉት መቻሎች ጎል ማስቆጠር የቻሉት ገና በጊዜ ነበር። 1ኛው ደቂቃ ላይ ከእጅ ውርወራ የመጣለትን ኳስ ኮሊን ኮፊ ከመረብ አሳርፎ የአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረትን ቡድን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። የመጀመሪያዎቹን አስራ አምስት ደቂቃዎች ወደ ራሳቸው ኳስን በይበልጥ በመሳብ ብልጫን መውሰድ ቢችሉም ቀስ በቀስ በሲዳማ ቡና ጫናን ማስተናገድ የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች ያሬድ ባዬ ባስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ምት ወደ አቻነች ተሸጋግረዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ተደጋጋሚ ሙከራዎች እና ፋታ የለሽ ማጥቃቶችን ያስተዋልንበት የሁለቱ ቡድኖች መርሀግብር መደበኛው ደቂቃ ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ 90+4 ላይ ከጨዋታ ውጪ በምትመስል መልኩ ያሬድ ባዬ ከቅጣት ምት ሬድዋን ናስር ያሻገረለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር 2ለ1 ሲዳማ ቡናን አሸናፊ በማድረግ የሊጉ መሪ መሆን እንዲችል አድርጓል።
- ማሰታውቂያ -

ሀዋሳ ከተማ 0-1 ፋሲል ከነማ
በመጀመሪያው አጋማሽ በሙከራዎች ረገድ መጠነኛ ቢሆንም የአፄዎቹ የበላይነት የተንፀባረቀበት መሆን ቢችልም በጎል ግን መታጀብ አልቻለም።
በሁለተኛው አጋማሽ ሀዋሳዎች በኳስ ቁጥጥሩ መሻሻልን ማሳየት ቢችሉም ማጥቃት ላይ ስልነት የሚታይባቸው ፋሲሎች ናትናኤል ገብረጊዮርጊስን በጉዳት ካጡ በኋላ በይበልጥ ግብ ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት ተሳክቶ 77ኛው ደቂቃ ላይ ቃልኪዳን ዘላለም ከምኞች ደበበ ጋር በፈጠረው ጥሩ ቅንጅት ፋሲል ከነማን 1ለ0 ድል እንዲቀናው አድርጓል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ 1-0 ቅዱስ ጊዮርጊስ
ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያገናኘው የመዲናይቱ ክለቦች ግንኙነት ተመጣጣኝ የሚመስል ነገር ግን በንፅፅር የኤሌክትሪክን ብልጫ ያሳየን ቢመስልም በሙከራ መታጀብ ግን ሳይችል ቀርቷል።
ከዕረፍት መልስ ለሀያ ደቂቃዎች ያህል ወደ መስመር ባደላ ማጥቃት መንቀሳቀስን መርጠው መታየት የቻሉት ኤሌክትሪኮች በተጋጣሚያቸው የቅብብል ስህተት ጎልን አስቆጥረዋል። 59ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ኋላ ወደ ሳጥን የተመለሰን ኳስ ኬኒያዊው የፈረሰኞቹ ግብ ጠባቂ ሻሂክሎ ፋርክ በአግባቡ ማራቅ ባለመቻሉ ኳሷን ፈጥኖ ያገኘው ሀሰን ሁሴን መረቡ ላይ በቀላሉ በማስቀመጥ ኤሌክትሪክን 1ለ0 አሸናፊ መሆን እንዲችል አስችሏል።
ሸገር ከተማ 1-2 ኢትዮጵያ ቡና
ሸገርን ከተማን ከኢትዮጵያ ቡና ባገናኘው የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ሸገሮች እንደነበራቸው የአጀማመር ብልጫ 3ኛው ደቂቃ ጎል አስቆጥረዋል። ከቀኝ መስመር አቅጣጫ አሚር አብዶ ያሻገረለትን ኳስ በከፍተኛ ሊጉ የቡድኑ ባለውለታ የነበረው ጀቤሳ ሜኤሳ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር አዲስ አዳጊዎቹን ቀዳሚ አድርገዋል። ጎል ካስተናገዱ በኋላ በይበልጥ በአንድ ሁለት ቅብብል ምላሽ ለመስጠት የዳዱት ቡናማዎቹ 36ኛው ደቂቃ ላይ ሚኪያስ በዳሶ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታውን ኳስ በተጫዋቾች ተጨርፋ እግሩ ላይ የደረሰለት ራምኬል ጀምስ 1ለ1 ማድረግ የቻለች ጎልን ከመረብ ደባልቋታል።
ከዕረፍት ተመልሶ ጨዋታው ሲቀጥል ሸገሮች ጥሩ መልክን ያሳዩ ቢመስልም 59ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅሩ አለማየሁ በሜዳው የግራ ክፍል በሰራው ጥፋት በዕለቱ ረዳት ዳኛ ወይንሸት አበራ ጥቆማ በሁለት ቢጫ በቀይ ከተሰናበተ በኋላ የተጫዋች ቅያሪን ቡናማዎቹ በማድረግ የተጫዋች የቁጥር ብልጫን ጭምር ወስደው ጎል አግኝተዋል። 79ኛው ደቂቃ ላይ ራምኬል ጀምስ ላይ ሦስት የሚደርሱ የሸገር ተጫዋቾች በሰሩበት ጥፋት በዕለቱ ዳኛ አብርሃም ኮይራ አማካኝነት የተሰጠን የፍፁም ቅጣት ምት አቡበከር አዳሙ አስቆጥሮ ኢትዮጵያ ቡና 2ለ1 ድል ማድረግ እንዲችል ረድቷል።


