የሊጉ የሁለተኛ ቀን መርሀግብር አዲስ አበባ እና ሀዋሳ ላይ ቀጥለው ወላይታ ድቻ ፣ አዳማ ከተማ እና ነገሌ አርሲ ወሳኝ ድልን አሳክተዋል።
ወላይታ ድቻ 2-1 ወልዋሎ ዓ/ዩኒቨርስቲ
አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ በነበረ የዕለቱ ብቸኛ ጨዋታ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን የቀጠረው ወላይታ ድቻ በጊዜያዊ አሰልጣኙ አምጣቸው ሐይሌ እየተመራ የሊጉን የመጀመሪያ ድል ወደ ካዝናው ከቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ቅርቃር ውስጥ የሚገኙትን ቡድኖች ያገናኘው መርሀግብር ተመጣጣኝ ፉክክርን እያሳየን 45ኛው ደቂቃ ላይ ወልዋሎዎች ከጋናዊው አጥቂ ኮንኮኒ ሀፊዝ ያገኘውን ኳስ ፍቃዱ መኮንን ወደ ጎልነት ለውጦ ቡድኑን መሪ ቢያደርግም በጭማሪው የዕረፍት መገባደጃ ሰዓት 45+4 ላይ ተከላካዩ ውብሸት ክፍሌ ከመረብ አዋህዶ ቡድኑን 1ለ1 አድርጓል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል በደካማ እንቅስቃሴዎች መታጀብ ቢችልም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ግን ከድል የታረቁት ወላይታ ድቻዎች ሆነዋል። 88ኛው ደቂቃ አማካዩ ኪዳኔ አሰፋ ከቅጣት አሻምቶ በግብ ዘቡ ሙታክብዋ ጆኤል የተመለሰች ኳስን ወጣቱ ቅዱስ ቂርቆስ አስቆጥሮ ቡድኑን አሸናፊ አድርጓል።
- ማሰታውቂያ -

አዳማ ከተማ 1-0 ባህር ዳር ከተማ
በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም አዳማ ከተማን ከባህርዳር ከተማ ባገናኘው ጨዋታ አዳማ የአመቱን ሁለተኛ ግብ እንዲያስመዘግብ አስችሎታል። እጅግ ደካማ ፉክክር በነበረው የሁለቱም ቡድኖች ጨዋታ ባህርዳሮች በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ለመንቀሳቀስ ጥረት ቢያደርጉም በአጋማሹ ጉዳት አስናግዶ ከወጣው እዮብ ማቲያስ በስተቀር ትኩረት የሚስብ ነገርን በጨዋታው መመልከት አልቻልንም።
ከዕረፍት መልስ በመጠኑም ቢሆን ቅያሪዎችን ቡድኖቹ በማድረግ ወደ ሜዳ ቢመለሱም የማጥቃት ደመ ነብሳቸው ግን በእጅጉ የደበዘዘ ነበር። ጨዋታው ቀጥሎ 75ኛው ደቂቃ ላይ እንደደረሰ ቢኒያም ዐይተን ከማዕዘን አሻምቶ ዳዋ ሆቴሳ ጨርፎ የሰጠውን ኳስ አቡበከር ሳኒ ከመረብ አዋህዶ አዳማን 1ለ0 ባለ ድል ማድረግ ችሏል።

ኢትዮጵያ መድን 0-1 ነገሌ አርሲ
ጥሩ ፉክክር የነበረው እና በርካታ ተመልካቾችም የታደሙበት የኢትዮጵያ መድን እና ነገሌ አርሲ መርሀግብር ጠንካራ እና ፋታ የለሽ እንቅስቃሴዎች ያስመለከተን ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ በንፅፅር የተሻለውን ጊዜ ነገሌ አርሲዎች ማሳለፍ የቻሉ ቢመስልም የመጨረሻው ሜዳ ላይ ከነበራቸው ደካማ ውሳኔ አኳያ ጎል እና መረብን ማገናኘት ሳይቾሉ ቀርተዋል።
ተመጣጣኝ እና እልህ አስጨራሽ ፉክክርን ተላብሶ ከዕረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ ቡድኖች የተጫዋች ቅያሪን በማድረግ ጭሞር በአዲስ ጉልበት አንዳች ነገርን ለማግኘት በብርቱ ቢታገሉም ቅያሪያቸው ፍሬ ያፈራላቸው ግን የአሰልጣኝ ቱሉ ደስታው ነገሌ አርሲዎች ናቸው። 61ኛው ደቂቃ ከግብ ጠባቂው እድሪሱ አብላሂ በረጅሙ የደረሰውን ኳስ የመድን ተከላካዮች መዘናጋት ታክሎበት ምስጋና ፣ ገብረመስቀል እና ዳዊት ነካክተዋት በመጨረሻም ተቀይሮ የገባው ምስጋና መላኩ ጥሩ ቀን እያሳለፈ በነበረው ፋሲል ገብረሚካኤል መረብ ላይ በማዋሀድ በመጨረሻም ነገሌ አርሲ 1ለ0 አሸንፏል።



