ሁለት መልኮች በነበረው ጨዋታ መቐለ 70 እንደርታ በመጨረሻ ደቂቃ ጎል ከወላይታ ድቻ ጋር 2ለ2 ሲለያይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ነገሌ አርሲ ያለ ጎል አጠናቀዋል።
በፌድራል ዋና ዳኛ ሙሉቀን ያረጋል መሪነት አስር ሰዓት ሲል የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ሰላሳ ደቂቃዎች በንፅፅር ከጥልቅ አጨዋወት ማጥቃትን መርጠው መጫወት የቻሉት መቐለዎች በይበልጥ ወደ ሳጥኑ በተጠጉበት ሂደት 28ኛው ደቂቃ ላይ በፍፁም ቅጣት ምት መሪ ሆነዋል። በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል ከግራ ሳጥኑ ጠርዝ ቦና ዓሊ ኳስን ገፍቶ ለመግባት ጥረት ሲያደርግ ለማስጣል ሙከራ ባደረገው እና ከወትሮ ሚናው በመከላከል ቦታ ላይ በነበረው ሙሉቀን አዲሱ በመጠለፉ ራሱ ቦና የተገኘውን አጋጣሚ ወደ ጎልነት ለውጦ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከጎሏ መቆጠር በኋላ ወደ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የገባው ጨዋታ በመልሶ ማጥቃት ካርሎስ ዳምጠው የጦና ንቦቹን ወደ ጨዋታ የምትመልስ ግልፅ ዕድልን ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ከዕረፍት መልስ በጊዜያዊ አሰልጣኙ ቴዎድሮስ ቀነኒ የሚመሩት ወላይታ ድቻዎች የተጫዋቾች ቅያሪን በማድረስ ከተመለሱ በኋላ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ጨዋታውን ወደ ራሳቸው ቁጥጥር አድርገው ቢገቡም 54ኛው ደቂቃ ጎል አስተናግደዋል። በፈጣን ሽግግር ከፍፁም አለሙ ያገኘውን ኳስ ኪቲካ ጀማ በድንቅ አጨራረስ ለመቐለ ሁለተኛዋን ኳስ ከመረብ አሳርፏል። ጎሎች ተቆጥሮባቸው 2ለ0 ለመመራት የተገደዱት ድቻዎች የተጨማሪ ተጫዋቾች ለውጥን በማድረግ ከፍ ባለ ፈጣን መልሶ ማጥቃት የመጨረሻዎቹን ሰላሳ ደቂቃዎች ተጭነው በመጫወት 70ኛው ደቂቃ በምንተስኖት ተስፋዬ ግብ ወደ 2ለ1 ተሸጋግረዋል።
- ማሰታውቂያ -

ጎል ማስቆጠራቸው ያነቃቸው ድቻዎች ጎል ማስናገዳቸው ያፈዘዛቸው መቐለዎች በተወሰደባቸው ተደጋጋሚ ብልጫ በጭማሪው አምስት ደቂቃዎች ውስጥ 90+3 ላይ ካርሎስ ዳምጠው ወደ ጎል የመታውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ሱለይማን ሀሚድ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ካርሎስ በቀላሉ አስቆጥሮ በመጨረሻም ጨዋታው 2ለ2 ሊጠናቀቅ ችሏል።
አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ በነበረው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ነገሌ አርሲ ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል። በመጀመሪያው አጋማሽ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሁለተኛው አጋማሽ ነገሌ አርሲዎች በበኩላቸው በሁለተኛው አጋማሽ ለጎል የቀረበ ሙከራን ያደረጉበትን እንቅስቃሴ ብናስተውልም ጨዋታው ጎል ሳይቆጠርበት ያለ ጎል ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ11 ነጥብ ተከታዮቹ እስኪጫወቱ የሊግ መሪ መሆን ሲችል ነገሌ አርሲ በበኩሉ እስከ አሁን ሦስት ነጥብን ማግኘት ተስኖታል።



