በአራተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን መርሀ-ግብር ኢትዮጵያ መድን እና ሸገር ከተማ የመጀመሪያ ድላቸውን ሲያሳኩ ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ሦስተኛውን የዓመቱ ድሉን አስመዝግቧል።
ሀድያ ሆሳዕና 1-2 ኢትዮጵያ መድን
ከቀትር መልስ ከአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎቹን ጨርሶ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ጨዋታውን ያደረገው ኢትዮጵያ መድን የሊጉን የመጀመሪያ ድል በስኬት ቋጭቷል። ተመጣጣኝ አጀማመር የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በተሻለ እንቅስቃሴ ሁሉቱም መጫወት መርጠው ቢታዩም ኳስ እና መረብን በማገናኘቱ ግን መድኖች የበላይ ነበሩ። 28ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር ያሬድ ካሳዬ ያሻማለትን ኳሶ ረመዳን የሱፍ ገጭቶ የግብ ዘቡ ያሬድ ካሳዬ በአግባቡ መቆጣጠር ያልቻላትን ኳስ ዩጋንዳዊው አጥቂ አለን ካይዋ ወደ ጎልነት በመለወጥ ቡድኑን መሪ አድርጓል።
ጎልን ካስተናገዱ በኋላ በይበልጥ ፈጣን ሽግግርን ሲጠቀሙ የተስዋሉት ሀድያ ሆሳዕናዎች ወደ ጨዋታ የመለሳቸውን ግብ በአጋማሹ ጭማሪ ደቂቃ 45+1 ላይ አስቆጥረዋል። በመልሶ ማጥቃት ከብሩክ በየነ በአግባቡ መሬት ለመሬት የተሰጠውን ኳስ ፈጣኑ የመስመር አጥቂ ተመስገን ብርሀኑ ፋሲል ገብረሚካኤል መረብ ላይ አሳርፎ ቡድኑን ወደ አቻነት አምጥቷል።
- ማሰታውቂያ -
ከዕረፍት መልስ ከመጀመሪያዎ አኳያ ወረድ ያሉ ፉክክሮች በተንፀባረቁበት አጋማሽ ቡድኖች ከመረጡት የጨዋታ እንቅስቃሴ በቀር የተለየ የማጥቃት ሁነትን ማስመልከት ባይችሉም መድኖች ግን የአሸናፊነት ጎልን ማግኘት ችለዋል። መደበኛው የጨዋታ ደቂቃ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ብቻ ሲቀረው አማኑኤል ኤርቦ ወደ ሳጥን ያሻማትን ኳስ ለማውጣት ጥረት ሲያደርግ የነበረው ዳግም ንጉሴ በራሱ መረብ ላይ በማስቆጠር ጨዋታው በመጨረሻም በኢትዮጵያ መድን 2ለ1 አሸናፊ ተገባዷል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ 0-1 ሸገር ከተማ
የአዲስ አበባ ስታዲየም ሁለተኛው ጨዋታ አስር ሰዓት ሲል ጊዮርጊስ እና ሸገር ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ሸገር ከተማ የሊጉን የመጀመሪያ ድል ያገኘበትን ውጤት አስመዝግቧል። ሜዳ ላይ ቡድኖች መርጠው ለመጫወት ከሞከሯቸው እንቅስቃሴዎች ውጪ ብዙም የጠሩ አጋጣሚዎች ባልነበሩት ጨዋታ ከመጀመሪያው አጋማሽ ይልቅ ሁለተኛው አጋማሽ በተሻለ መነቃቃቶችን ያሳየን ቢመስልም በግብ ሙከራዎች መድመቅ ላይ ግን አሁንም ደካማ ነበር።
ይሁን እንጂ ከዕረፍት መልስ ፈጣን አጀማመር የነበራቸው ሸገር ከተማዎች 47ኛው ደቂቃ ሔኖክ አዱኛ ከቅጣት ያሻገረልን ኳስ ከከፍተኛ ሊጉ ቡድኑን ያሳደገው ያሬድ መኮንን ዘደ ጎልነት ለውጦ ቡድኑን መሪ አድርጓል። መሪነታቸው ካወቁ በኋላ በቢኒያም ፍቅሬ እና አቤል ያለው በሚመራው የአጥቂ ክፍል በድግግሞሽ ፈረሰኞቹ ሲያጠቁ ቢታይም የተለየ ነገርን ማድረግ ሳይችሉ የሊጉን የመጀመሪያ ሽንፈት ሸገሮች በበኩላቸው የመጀመሪያ ድላቸው አስመዝግበውበት ተቋጭቷል።
መቐለ 70 እንደርታ 1-3 ሀዋሳ ከተማ
በጨዋታው የመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች አጀማመራቸውን ፈጠን ባሉ ቅብብሎች በማድረግ በእንቅስቃሴ ብልጫን ለመያዝ ጥረት ያደረጉት ሀዋሳዎች ጎል ያስቆጠሩት ገና በጊዜ ነበር። 8ኛው ደቂቃ ያሬድ ብሩክ ወደ ግራ ካደላ ቦታ ወደ ጎል ሞክሮ ግብ ጠባቂው ሶፎኒያስ ሠይፈ የተፋትን ኳስ ልማደኛው አጥቂ ጌታነህ ከበደ በቀላሉ መረቡ ላይ አሳርፎ ሐይቆቹን ቀዳሚ አድርጓል። በወጣቱ የመስመር ተከላካይ የአብስራ ደግፌ ሁለት ሙከራዎችን ካደረጉ በኋላ በእንቅስቃሴ በተጋጣሚያቸው ለመበለጥ የተገደደው የአሰልጣኝ ተመስገን ዳናው ሀዋሳ ከተማ 24ኛው ደቂቃ ላይ ሱለይማን ሀሚድ ግሩም የቅጣት ምት ጎል አክሎ መቐለን ወደ 1ለ1 ማሸጋገር ችሏል። ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸው ጎል ካገኙ በኋላ በይበልጥ ጨዋታውን መቆጣጠር የቻሉት እና በኪቲካ ጀማ እና ፍፁም አለሙ አማካኝነት መሪ ሊያደርጋቸው የሚችላቸውን አጋጣሚዎችን መቐለዎች ማግኘት ቢችሉም ወደ ግብነት መለወጥ ሳይችሉ ቀርዋል።
ከዕረፍት መልስ የተጫዋቾችን ቅያሪ በማድረግ ወደ ሜዳ የተመለሱት ሀዋሳዎች በድጋሚ መሪ ሆነዋል። 47ኛው ደቂቃ ላይ ቢኒያም በላይ ከዘረሰናይ ብርሀነ የነጠቀውን ኳስ ወደ ሳጥን ሲያሻግር ያሬድ ብሩክ ለቡድኑ ሁለተኛ ለራሱ የውድድር ዘመኑ ሦስተኛውን ጎል አስቆጥሯል። ጨዋታው ቀጥሎ መቐለዎች በእንቅስቃሴ የበላይነቱን ቢወስዱም ሱለይማን ሀሚድ እና አሸናፊ ሀፍቱ ካደረጓቸው ቀላል ሙከራዎች ውጪ የመጨረሻው ሜዳ ላይ ኮስታራ መሆን አለመቻላቸውን ተከትሎ በ84ኛው ደቂቃ የመቐለው ተከላካይ ፍሬዘር ካሳ ከዕለቱ ዋና ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ ጋር በፈጠረው ሰጣገባ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ተወግዷል። በተቃራኒው ጨዋታው ሊገባደድ 89ኛው ደቂቃ ተጨማሪ ጎልን ለማስተናገድ ተገደዋል። ጌታነህ ከበደ ከሳጥኑ ጠርዝ አካባቢ የተገኘን የቅጣት ምት አክርሮ መቶ መረቡ ላይ አስቀምጦ ለራሱ ሁለተኛ የውድድር ዘመኑ አራተኛ ጎሉ አድርጎ በ90+3ኛው የሀዋሳ ከተማው ተከላካይ በረከት ሳሙኤል በሰራው ጥፋት በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ወጥቷል። ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 3ለ1 ድል አድራጊነት ተጠናቋል።


