የሎዛ አበራ አዲስ ዓለም

 

በእርግጥ ይሄንን ታሪካዊ ቀን አብዝታ ትጠብቀው ነበር፤ ምንም እንኳን አለምንና ሀገራችንን ያስጨነቀው የኮሮና ቫይረስ የልቧን እንዳታደርግ እንቅፋት ቢሆንባትም የቀለበት ስነ-ሥርዓቷን በቤተክርስቲያን ሕግና ሥርዓት ከማድረግ የማገድ አቅም አልነበረውም፣ አዎን በኢትዮጵያ እግር ኳስ የነገሰችው፣ በማልታ ሊግ ያንፀባረቀችው፣ የማልታ ሊግ የአመቱ ኮከብ ተጨዋችነት ክብርን በሀገራችን እግር ኳስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጎናፀፈችው ሎዛ አበራ የህይወቷን ሌላኛውን ምዕራፍ አንድ ብላ ጀምራለች፡፡
“ብዙም ያልተጋነነ እግዚአብሔር የከበረበት የቀለበት ሥነ-ስርዓት ነው ያደረግነው” የምትለው ሎዛ አበራ ባለፈው እሁድ ከአቶ ዮሐንስ ፍቃደ ጋር በትዳር አብሮ ለመኖር ቀለበት ማሰሯን ይፋ አድርጋለች፡፡ በዚህም “ሰው አባትና እናቱን ይተዋል በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” የሚለው ቅዱስ ቃሉ በእነርሱ ላይ ተፈፅሟል፡፡
የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክሲኪዩቲቭና ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ በቀለበት ስነ-ሥርዓቱ ምክንያት ፋታ የሌላትን ሎዛ አበራን “እንኳን ደስ አለሽ፤ መልካም ጋብቻ” የሚል ቃል አስቀድሞ ከጀግናዋና ከታሪካዊ ሰሪ0ዋ የእግር ኳስ ኮከብ ግን ደግሞ ከአዲሷ ሙሽራ ጋር ከዚህ በታች ያለውን ቆይታ አድርጓል፡፡

ሀትሪክ፡- …ሎዛዬ እንኳን ደስ አለሽ…እንኳን ለዚህች ታሪካዊ ቀንም በሠላም አደረሰሽ…?

ሎዛ፡- …እንኳን አብሮ ደስ አለን…፤…ስለመልካም ምኞትህም በጣም አመሰግናለሁ…፡፡

ሀትሪክ፡- …የማልታ የአመቱ ኮከብ ተጨዋች ክብርን…አሁን ደግሞ ለወግ ለማዕረግ በቃሽ…ተዳርሽ… እነዚህን ታላቅ ስኬቶች ከማግኘትሽ አንፃር አመቱ የሎዛ ነው ማለት ይቻላል…?

ሎዛ፡- …እንደዛ ቢባልም ስህተት ያለው አይመስለኝም…ምክንያቱም ከሀገር ውጪ ባለ ሊግ ተሳትፌ የአመቱ ኮከብ ተጨዋችነት ክብርን ማግኘት ለእኔም ለሀገሬም ትልቅ ስኬት ነው፤ሽልማቱ ለእኔ የተሰጠ ቢሆንም የተጠራው የእኔም የሀገሬም ስም በመሆኑ በጣም ተደስቻለሁ፤ከዚህ በተጨማሪ ትልቁ ህልሜ የነበረው በወግ በማዕረግ ተድሬ የራሴን አዲስ ህይወት…የመጀመሪያ የህይወት ምዕራፌን አንድ ብዬ የምጀምረበትና የምመራበትን እድል ያገኘሁበት በመሆኑ አዲሱን አመት ገና ከመጀመሪያው የእኔ አመት ነው ብዬ ባስብ ስህተት አይመስለኝም፡፡

ሀትሪክ፡- …ግን እኮ ተሰናባች አመት 2012ትም…በተለይ በሙያሽ የአንቺ አመትም ነበር…?

ሎዛ፡- …በግሌ…በእግር ኳስ ስኬቴ ካየኸው…አዎን ትክክል ነህ…በመጀመሪያው የፕሮፌሽናል ህይወቴ ደማቅ ታሪክ አፅፌ የራሴንም የሀገሬንም ስም ከፍ አድርጌ ያስጠራሁበት አመት ነው፤ብዙ ጎሎችን… ብዙ ክብሮችንም…ያገኘሁበት አመትም ነበር…፡፡

ሀትሪክ፡- …የቀለበት ፕሮግራምሽ ምን ያህል የደመቀ ነበር…?

ሎዛ፡- …እውነት ለመናገር ያን ያህል የተካበደ ነገር አላደረግንም…ሠርግ ሣይሆን የቀለበት ስነ-ስርዓት ነው ያደረግነው…ስነ-ሥርዓቱም የተከናወነው በቤተክርስቲያን ህግና ደንብ መሠረት በቃል ኪዳን ነው የተጋባነው፤ጠቅለል ሳደረግው ደስ የሚልና ቀለል ያለ…ግን እግዚብሔር ከፍ ብሎ የከበረበት…የቀለበት ስነ-ሥርዓት ነበር ያደረግነው፤በዚህም በጣም ተደስቻለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- …ባለቤትሽ የትዳር አጋርሽ ምን አይነት ሰው ነው ብልሽ ምን አይነት መልስ ትሰጨኛለሽ…?…ሎዛ በትክክል መስፈርቷን የሚያሟላ ውሃ አጣጪዋን ነው ያገኘችው…?

ሎዛ፡- …(ሣቅ)…ከሚገባው በላይ መስፈርቴን የሚያሟላ ምርጥ ባል ነው ያገኘሁት…(አሁንም ሳቅ)… ባለቤቴ ዮሐንስ ፍቃዱ በጣም መልካም ሰው ነው…በሙያዬ በብዙ ነገር ሲረዳኝ ቆይቷል…አሁንም እየረዳኝ ነው…ጨዋታዬንም ይከታተላል…አፈላጊውን ምክር ይሰጠኛል…አብሮኝ ትሬይኒንግ ይሰራል… በብዙ ነገር እውነተኛ አጋር የሆነኝ ሰው ነው፤ከዚህ ውጪ መልካም የሚባል ስብዕና ያለው አዛኝም ሰው ነው…የሚያውቀውን ብቻ ሣይሆን የማያውቀውንም ሰው በመረዳት የሚታወቅ ሰው ነው፡፡ ባለን ነገር ተግባብተን ነው እስከዛሬ የኖርነው…በህይወታችን ስለምንተሳሰብ…በሙያችንም ስለምንተጋገዝ አምላክ የፍላጎቴን አይቶ የሰጠኝ ሰው ነው ማለት እችላለሁ…/ሳቅ/

ሀትሪክ፡- …የቀለበት ስነ-ሥርዓት ቢሆንም ሚዜዎችሽ እነማን ነበሩ…?…ከተጨዋቾች ካሉ ብዬ ነው…?

ሎዛ፡- …ሚዜ…አንድ አንድ ነው ያደረግነው…በባለቤቴ በኩል በጣም የሚወደውን ጓደኛው ነበር፤በእኔ በኩል ግን እንዳልከው ተጨዋች ነበረች ሚዜዬ …የኢትዮጵያ ብ/ቡድን ግብ ጠባቂ የነበረችው ታሪኳ በርገና ነበረች ሚዜዬ፡፡

ሀትሪክ፡- …የቀለበት ስነ-ሥርዓትሽን…ወደ ትዳር አለም ጎራ ማለትሽን አስመልክቶ የደረሰሽ ያልጠበክሽው የደስታ መግለጫ መልዕክት አለ… ?

ሎዛ፡- …እስኪገረመኝ ድረስ…ብዙ ሰው…ከትንሽ እስከ ትልቅ…ሁሉም ማለት እችላለሁ…በተለያየ መንገድ የደስታ ስሜቱን ገልጾልኛል…እኔ ደስታው የእኔና የቤተሰቤ ብቻ ነበር የመሰለኝ…ግን ሁሉም በደስታዬ አብረውኝ ስለተደሰቱ ይበልጥ የተለየ ስሜት እንዲሰማኝ አድርጓልና…ሁሉንም ከልቤ አመሰግናለሁ…፡፡

ሀትሪክ፡- …በእግር ኳስ ከነገሽበት…ሌላ አዲስ ታሪክ ካፃፍሽበት ከወደ ማልታስ “እንኳን ደስ አለሽ” በሚል “ሀሎ ሎዛ” ብሎ ደስታውን ለመግለፅ የቀደመስ አለ?

ሎዛ፡- ….የብ/ቡድናችን አሰልጣኝና ተጨዋቾች ስሜታቸውን በተለያየ መንገድ ገልፀውልኛል…የደስታዬ ተካፋይ መሆናቸውን ጭምር ገልፀውልኛል፤በሜሰንጀር አውርተውናል፤ከዚህ ውጪ ፖስት በተደረጉት ፎቶዎቼ ላይ Congratulation’s(እንኳን ደስ አለሽ)፣መልካም የትዳር ጊዜ ብለው…ተመኝተውልኛል… ይሄኛውም ያልጠበኩትና ትልቅ የደስታ ስሜትን የፈጠረልኝ አጋጣሚ ነው…፡፡

ሀትሪክ፡- …ትዳር ይበልጥ የሚደምቀው…ጎጆም ይበልጥ የሚሞቀው በልጅ ነው ይባላል…ምናልባት ጥያቄው የፈጠነ ቢሆንብሽም…ሎዛ በቀጣይ ስንት ልጅ የመውለድ እቅድ አላት…?

ሎዛ፡- …ዛሬ ላይ ሆኜ ይሄን ያህል ልጅ ቢኖረኝ ብዬ በቁጥር ገድቤ አልነግርህም…ይሄንን የመወሰን ስልጣኑም የእኛ ነው ብዬ አላስብም፤እንደ እኔ እምነት ልጅ የእግዚብሔር ስጦታ ነው፤እግዚብሔር በህይወታችን ይሁን ያለውን…የሚፈቅድውን ነው የምንቀበለው…እኔ አሁን ልልህ የምችለው ይሄንን ነው፤እግዚብሔር በፈቀደልኝ…በቻልን ጊዜ ልጅ ይኖረናል፡፡

ሀትሪክ፡- …የላሜንገላ ሽርሽርሽ ማልታ ወይስ…?

ሎዛ፡- …(ሣቅ)… ኧረ ገና አልወሰንም….ማልታም ይሁን እዚህ ብለን…በዚህ ጉዳይ ገና ያወራነው ነገር የለም…ምክንያቱም…ጊዜው በዚህ ደረጃ እንድታስብ የሚያደረግ አይደለም…፡፡

ሀትሪክ፡- …የአንቺን የቀለበት ማድረግም ወደ ጋብቻው አለም ጎራ ማለትን የታዘቡ በሁለት ጎራ ተከፍለዋል…አንደኛው ወገን ሎዛ እንኳን አገባች ሲል…ሌላኛው ደግሞ ገና በእግር ኳስ ብቅ እያለች እያበራች በመጣችበት ሰዓት ቸኩላ ወደ ትዳር ገብታለች…በማለት አስተያየት የሚሰጡ አሉ…እውነት ሎዛ ቸኩላ ነው ያገባችው…?

ሎዛ፡- …እውነት ለመናገር የሰዎችን ሃሳብ አከብራለሁ…ከፍቅራቸው የተነሣ በሁለት አይነት ስሜት ውስጥ መውደቃቸውንም እረዳለሁ፤ይሄ ይሁን ያለው አምላካችን ነው፤በመቀጠልም የእኔ ውሣኔ ነው፤ ምክንያቱም ሁሉም ሰው የራሱን ህይወት ነው የሚኖረው…ለእኔ በጋብቻ ታስሮ አዲስ የህይወት ምዕራፍን ለመክፈት ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው ብዬ አምኜበት ገብቼበታለሁ፤ይሄም በመሆኑ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከፈቀዳችው…ከሚያደርግላቸው መልካም ነገሮች አንዱ በተቀደሰ ጋብቻ ተሳስሮ መኖርን በመሆኑ እኔ ለጋብቻ አልዘገየሁም በጣምም አልፈጠንኩም፡፡

ሀትሪክ፡- የሰው ስጋት ሎዛ ገና በእግር ኳስ ከፍ እያለች ያለበት ሰዓት ነው…በዚህ ሰዓት ወደ ትዳር መግባቷ የእግር ኳስ ህይወቷ እድገት ላይ አሎታዊ ጎን ይኖረው ይሆን? ከሚል ስጋት በመነጨ ነው፤ ማግባትሽ በእግር ኳስ ህይወትሽ ላይ የሚያሳድረው ነገር ይኖራል ብለሽ ትሰጊያለሽ?

ሎዛ፡- …በፍፁም አልሰጋም…እንደዚህ አይነቱን አስተያየትም አልቀበልም፤እንደውም አንድ እውነት ልንገርህ ወደ ትዳር አለም በመግባቴ የበለጠ ጠንካራ…በፕሮግራም የምመራ ሰው እንድሆን ነው የሚያደርገኝ፤እኔ የተሻለችዋ ሎዛ ይበልጥ ልትፈጠር እንደምትችል ነው የማስበው፡፡ እግር ኳስ በጣም የምወደው፣በጣም የማከብረው፣ብዙ የደከምኩበትና የለፋሁበት ሙያዬ ነው…በፍፁም ይሄንን የምወደውን…ብዙ ርቀት ለመሄድ የማልምበትን ሙያዬን ለመጉዳት ሣይሆን ይበልጥ ለማሳደግም ነው ወደዚህ ነገር የገባሁት፤አግብተው በጣም ስኬታማ የሆኑ ተጨዋቾች እንዳሉም መዘንጋት የለብንም፡፡ ይሄ ደግሞ ህይወት ነው…እኔም ሰው እንደመሆኔ…ሌላኛውን የህይወት ምዕራፌን መጀመር አለብኝ፡፡ በምችለው አቅም በትዳሬም ስኬታማ ሆኜ ህይወቴን መምራት ነው የምፈልገው፤በሙያዬም በጣም ጠንካራ ሆኜ መጓዝን ነው የማስበው፡፡

ሀትሪክ፡- …ከማልታ ክለብ ጋር የነበረሽን ኮንትራት ነገስሽ አጠናቀሻል፤ሎዛን ከሙሽርነቱ በኋላ የት ነው የምናገኛት?ማልታ ወይስ?

ሎዛ፡- …እሱን የሚያውቀው እግዚአብሔር ነው፤ዛሬ ላይ ሆኜ እንደዚህ ነው ብዬ አልናገርም….ሲሆን አብረን ብናየው አይሻልም…?

ሀትሪክ፡- …እኔንም አንባቢዎቼን በማክበር…በጣም የተጠባበ ጊዜሽን በመሰዋት ለቃለ-ምልልስ ሁሌም ለምታደርጊልኝ ትብብር እያመሰገንኩ ከመለያየታችን በፊት የመጨረሻ ቃል ካለሽ…?

ሎዛ፡- ከሁሉም በላይ እግዚአብሔርን ማመስገን እፈልጋለሁ…የፈጠረኝ አምላክ በህይወቴ ይሄንን ስላሳካልኝም፣ለዚህ ስላበቃኝም ከልቤ ነው የማመሰግነው፤ ቤተሰቦቻንን በተለይ እናትና አባቶቻችን እህት፣ወንድም፣አክስት፣አጎት ሁሉም ዘመዶቻችን በዚህ ታሪካዊ ቀን እጅግ እጅግ በጣም ደስተኞች ነበሩ፣እናትና አባቶቻችን በህይወት ኖረው የእኛን መልካም የሚባል ፕሮግራም ለማየት ስለበቁ የእነርሱን ደስታ በዚህ መልኩ ከማየት በላይ ምንም የሚያስደስት ነገር የለምና በጣም ደስ ብሎኛል፤ እነሱን ሠላም ነገር ያማረ እንደሆን ላደረጉት ነገር እኔም ከልብ አመሰግናለሁ፤ በዚህ ፕሮግራም ላይ የተገኙትን በጣም የምወደው ወንድሜን አስውቦ በጣም ቆንጆ ያደረገኝን “ሄኒ አፍሮን” በጣም ነው የማመሰግነው…በብዙ ነገር የረዳኝ የቅርብ ጓደኛዬም ነው እሱን በጣም አመሰግነዋለሁ…ከእሱ ውጪ አዲካን ፕሮግራማችን ያማረ እንዲሆን ላደረጋችሁልን ነገር እንዲሁ ምስጋና ይደረሳችሁ…ከዚህ ሌላ ፕሮግራሙ ለታሪክ እንደቀመጥ ላደረገው ዞላ ፎቶን እንዲሁም አቢ ዲኮርን በጣም ነው የማመሰግነው…እግዚብሔር ይስጥልኝ፤አንተም መድረኩን ስለሰጠኸኝ ምስጋና ይገባሀልና በጣም አመሰግናለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- …ሎዛዬ እኔም በጣም አመሰግናለሁ…ጋብቻችሁ ያማረ፣የደመቀና የተሳካ እንዲሆን ምኞቴ ነው…

ሎዛ፡- ….(እድነት አኳረጠችኝና) .. ውይ… ውይ…. በጣም ይቅርታ… አንድ ነገር ይቀረኛል…

ሀትሪክ፡-…ምን…?

ሎዛ፡- …ይቅርታ መጠየቅ ይቀረኛል…አለምንና ሀገራችንን ባስጨነቀው በዚህ ወረርሽኝ (ኮቪድ19) ምክንያት ቤተሰቦቻችንን አድናቂዎቻችንንና ወዳጆቻችን መጥራት ባለመቻላችን ቅር ያላችሁ የተቀየማችሁን ካላችሁ በልዑል እግዚአብሔር ስም ይቅርታ እጠይቃለሁ፤ሁላችሁንም ብንጠራ ደስ ይለን ነበር፤በበሽታው ምክንያትና ይሄንንም ተከትሎ ቤተክርስቲያንም ገድብ ስላለት ሁላችሁንም በደስታችን ቀን እንድትገኙ መጥራት አለመቻላችንን አውቃችሁ ይቅርታችሁን እንደትስጡን እጠይቃለሁ፤በድጋሚም አመሰግናለሁ፡፡

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.