“በእኔ እምነት ኢት. ቡና የፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮን የመሆን አቅም አለው” ወንድሜነህ ደረጄ /ኢትዮጵያ ቡና/

 

በኮቪድ ላለፉት 7 ወራቶች ከልምምድና ከውድድር ርቆ የቆየበት አጋጣሚ…

“በእዚህ መልኩ ረዘም ላለ ጊዜ ስርቅ የአሁኑ የመጀመሪያዬ ነው፤ በኳስ ህይወቴም እንዲህ ያለ ቆይታም አጋጥሞኝ አያውቅም፤ያ ከመሆኑ የተነሳም በወቅቶቹ ደስ የሚልም ደስ የማይልም ስሜቶችን ነው ሳስተናግድም የነበረው፡፡ በቆይታዬ ደስ የሚለው ነገር ከቤተሰቦቼ ጋር ሆኜ ከእዚህ በፊት ለረጅም ጊዜያት አብሮ የመቆየትና የመጨዋወት እንደዚሁም ደግሞ ብዙ ቁም ነገሮችንም የማውራት አጋጣሚው የለም ነበርና ያን በሚገባ ላሳካው ችያለሁ፤ ሌላው ደግሞ ከኳስ መራቅ በጣም ከባድ እና አስቸጋሪም ሁኔታ ነው የሚያጋጥምህና ልምምዴን በግል በመስራት ራሴን ለአዲሱ የውድድር ዘመን ላዘጋጅበት በቅቻለው፤ ደስ የማይለው ነገር ደግሞ ኮቪድ በጣም ከምንወደው እና ስራችን ከሆነው እግር ኳስ ያራቀን አጋጣሚ ነበርና ያን ነው ለመጥቀስ የምፈልገው”፡፡

ወደ ልምምድና ውድድር መመለሱ…

“ይሄ መሆን መቻሉ ደስ የሚል አጋጣሚ እና ከፍተኛ እርካታንም ያገኘሁበት ነው፤ እንደመታደልም ሆኖ ለብሔራዊ ቡድን ተመርጬ ስለነበርም ነው አስቀድሜ ወደ ልምምድም ወደ ውድድርም በቅድሚያ ከተመለሱት ተጨዋቾች መካከል አንዱ ልሆንም የቻልኩት፤ ከኮቪድ አንፃር አስፈላጊውን ጥንቃቄ አድርጌ ወደ ሜዳ ስመለስም ሆነ አሁን ላይ ደግሞ ለክለቤ የዘንድሮውን የፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታዬን ላደርግ መሆኑ ከፍተኛ ደስታንም ነው በድጋሚ በውስጤ የፈጠረብኝ”፡፡

በ2013 የሚቀርበው ኢትዮጵያ ቡናና የአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ቡና እንዴት እንደተገነባ…

“ኢትዮጵያ ቡና ለዘንድሮው የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው በሜዳ ላይ የሚቀርበው ካለፈው ዓመት አቋሙ በመነሳት ነው፤ ዓምና የነበሩብን ጥቃቅን ችግሮች ነበሩ፤ እነዛን እያሻሻልን ነው፤ ይሄ በመሆኑም ዘንድሮ ጥሩና ውጤታማ ቡድንን ይዘን እንቀርባለን፤ በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ የሚገነባው ይኸው ቡድን ለውድድር ሲቀርብም የሚገነባው ቡድን በ2012 ላይ ካሳየው እና ተስፋ ሰጪ ከሆነውም እንቅስቃሴ በመነሳት ያን የማስቀጠል ስራን ነው የምንሰራው፤ ዓምና በእንቅስቃሴ ደረጃ የገባን ነገር ነበር፤ በእዛ ላይ ሌሎች ሊገቡን የሚገቡ ተጨማሪ ስራዎችን እየሰራንም ነው የምንገኘው፤ ያሉን ተጨዋቾች እና ቡድናችንንም በአዲስ መልክ የተቀላቀሉት ልጆችም በአሰልጣኛችን የሚሰጠውን ታክቲክ ተላምደውና ከእኛም ጋር ተግባብተውም በመስራት ላይ ይገኛሉና ቡድናችን በሚገባ ነው የተገነባው”፡፡

አዲስ ስለተቀላቀሉት እና ቡድኑን ስለለቀቁት ተጨዋቾች ጥቅምና ጉዳት

“ኢትዮጵያ ቡናን በዝውውር መስኮቱ የተቀላቀሉት አዳዲስ ተጨዋቾች የክለቡን የጨዋታ እንቅሰቃሴ /ታክቲክ/ በመላመድ በኩል እያሳዩት ያለው ፍጥነት እና ጥረት ሊደነቅ የሚገባው ነው፤ ወደ ቡድናችን የመጡት እነዚህ ተጨዋቾችም ቶሎም ነው በአጨዋወት ደረጃ ሊዋሀዱን እና ሊግባቡንም የቻሉት፤ ክለቡን ሲቀላቀሉ ምንም ነገር አልከበዳቸውም፤ ተጨዋቾቹ በጣም የሚጠቅሙንና የለቀቁብንን የሚተኩም ናቸው፤ ከቡድኑ የለቀቁብን ደግሞ ስኳዳችንን ከማስፋትና አሰልጣኙም ምን እንደሚፈልግ ከማወቅና ቡድኑን ከመላመድ አንፃር ቢኖሩልን ኖሮ ጥሩ ይሆን ነበር፤ መውጣታቸው ትንሽም ቢሆን ይጎዳናል፤ እንደዛም ሆኖ ግን የተጨዋች መሄድ እና መምጣት ያለና የሚኖር ስለሆነም ባለን የተጨዋቾች ስብስብ የእዚህ ዓመትን የሊግ ውድድር ለማድረግ ተዘጋጅተናል”፡፡

ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ መባሉና ውድድሩ በስፖንሰር ታጅቦ ገንዘብ ስለ ማምጣቱ…

“ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተሰጠው የአሁኑ የውድድር ስያሜ በጣም ደስ የሚል መጠሪያ ያለው ሲሆን ከእዛም ውጪ ሊጉ በስፖንሰር ታጅቦም ገንዘብን ሊያስገኝ መሆኑም ለሀገራችን እግር ኳስ እድገት የሚያስገኘው ከፍተኛ ጠቀሜታም አለ፤ በእዚህ መልኩ ውድድሩ ሲካሄድ ከሚገባው ገቢ በታዳጊ ወጣቶች ላይ ብዙ ነገሮችንም እንድንሰራም ያደርገናልና ያን በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል፤ የኢትዮጵያ ሊግ ከእዚህ ቀደም ወጪን እንጂ ገቢን የሚያስገባ አልነበረም፤ ይሄ ጉዳይን ብዙዎች እያወሩበትም መነጋገሪያ ሲያደርጉትም ከርመዋል፤ አሁን ላይ ግን ሊጉ ገቢን ሊያስገኝ ዝግጁ ሆኗልና ከእዚህ በኋላ ፌዴሬሽናችንም ከወቀሳ ይድናል፤ ይሄ አካሄድ አንድ እርምጃም ወደፊት እንደሄድንም ስለሚቆጠር ወደፊት ሊቀጥልም ይገባል”፡፡

በዲ.ኤስ.ቲቪ /በሱፐር ስፖርት/ የዘንድሮው የሊግ ውድድር መተላለፉ…

“የሀገራችን የሊግ ውድድር በዲ.ኤስ.ቲቪ መተላለፍ መቻሉ ለተጨዋቾቻችንም ሆነ ለሊጋችን በጣም ጥሩ እድልን ነው ይዞልን የመጣው፤ እነዚህ ግጥሚያዎቻችንን በዓለም ዙሪያ ሲታዩም ተጨዋቾቻችን ለብዙ ዘመናት ሲያልሙት የነበረውን ወደ ውጪ ሀገር ወጥቶ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት የመጫወት እድልን ያስገኝልናልና ያ አስደሳች ነገር ነው፤ ከዛ ውጪ የሊጉ ውድድር ጥራትም ይኖረዋልና ይሄን ያገኘነውን መልካም እድል በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል”፡፡

በበርካታ ደጋፊዎች ታጅበህ ነው የተጫወትከው፤ አሁን ግን ያለ ደጋፊ መጫወት ምን ስሜት ይፈጥራል…?

“እንደ ኢትዮጵያ ቡና ላሉና በበርካታ ደጋፊዎች ፊት ታጅበው ለሚጫወቱ ቡድኖች የእዚህ ዓመት ውድድርን ያለ ደጋፊዎቻችን መጫወት መቻል በጣም ከባድ ነው፤ ለውጤታችን ከፍተኛ ተፅህኖንም ነው የሚፈጥርብን፤ ምክንያቱም የቡና ደጋፊ ሁሌም ቢሆን ሜዳ ሲገባ እኛን በመጥቀሙ በኩል እንደ 12ኛ ተጨዋቻችን የምንቆጥራቸውም ናቸውና፤ ዘንድሮ ያለ እነሱ መጫወታችን በጣም ነው የሚጎዳን፡፡ ይሄ የሆነው በኮቪድ ወረርሽኝ ከጤና አንፃር ስለሆነም ይኸውን ውድድራችን እነሱ ከጎናችን እንደሆኑ አስበን ልንጫወትና በሜዳም ላይ ጥሩ ነገርን ለማሳየት ተዘጋጅተናል”፡፡

ዓምና በ2ኛው ዙር የተሻለ ነገር አሳይታችኋል፤ ዘንድሮስ…?

“ያለፈው ዓመት ውድድራችንን ስንጀምር ውጤታችን ጥሩ አልነበረም፤ ድክመትም ነበረብን፤ ከዛም በሁለተኛው ዙር ጅማሬያችን ላይ በተቻለን መጠን እየተሻሻልን መጥተን ነበር፤ ዘንድሮ ደግሞ ከዓምናው ብዙ የተማርነውና የተሳሳትነውንም ነገሮች በሚገባ ያወቅንበት ሁኔታ ስላለ ስህተቶቻችንን አንደግማቸውም፤ ከውድድሩ ጅማሬ አንስቶም በሜዳ ላይ ጥሩ ነገርን ለማሳየት እየተዘጋጀንም ነው የምንገኘው”፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ቡና ህልማችሁ ምንድን ነው? በግልና እንደ ቡድን…?

“ባለፈው የውድድር ዘመን እየተሻሻልን ከመምጣታችን አንፃር ዘንድሮ ምንም ጥያቄ አያስፈልግም ቡና የሊጉን ውድድር የሚጫወተው ጥሩ ተፎካካሪ ለመሆን ሳይሆን ለሻምፒዮናነት ነው፤ እንደ ቡድን ይህን ካልኩ በግል ደግሞ የሊግ ውድድራችን በዲ.ኤስ.ቲቪ የሚተላለፍ በመሆኑ ራሴን ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ብቁ ተጨዋች አድርጌ በማቅረብ ቡድኔን ለስኬት ለማብቃትና በፕሮፌሽናል ተጨዋችነትም ወደ ውጪ ወጥቶ መጫወትንም ከወዲሁ እያለምኩ ይገኛል”፡፡

ኢትዮጵያ ቡና የሊጉ ሻምፒዮን የመሆን አቅም አለው…?

“አዎን፤ ይህን ለማለት የደፈርኩትም ህልማችንን ለማሳካት የሚችል ጥሩ ቡድን ስላለን ነው፤ ለእዚህም ስኬት እንድንበቃ ዓምና በሜዳ ላይ የተመለከትናቸው ጥሩ ጎኖችም በጣም ይረዱናል፤ ከዛ ውጪም በውድድሩ ጅማሬ ላይ ነጥብን በመጣሉ ረገድ የተሸወድንባቸው ነገሮችንም በደንብ ስላወቅንም ይሄን ዘንድሮ የምንደግመው አይደለም፤ በእዚህ ዓመት ቡድናችን ተጋጣሚዎቹን በምን መልኩ በልጦ ማሸነፍ እንደሚኖርበት ካለፈው ትምህርትን የወሰደበት ሁኔታም አለና ይሄን ዓመት በስኬታማነት እንደምናጠናቅቅ ከወዲሁ አስባለሁና እንደ እኔ እምነት ኢት. ቡና የፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮን የመሆን አቅም አለው”፡፡

ከ16ቱ ቡድኖች 3ቱ የሉም፤ የእነሱ ያለመኖር በፉክክሩ ላይ የሚያመጣው ነገር…?

“የፕሪምየር ሊጉ ተወዳዳሪዎች የነበሩት መቐለ 70 እንደርታ፣ ወልዋሎ አዲግራትና ስዑል ሽረ ከዘንድሮው የሊግ ውድድር ውጪ በሆኑበት ሁኔታ ጨዋታዎቹ ሊጀመሩ መሆናቸው እንደ ሀገር ስፖርቱን የሚጎዳበት መልኩ ሰፊ ነው፤ ምክንያቱም የእነዚህ ቡድኖች መኖር የሊጉን ውድድር ጠንካራ እንዲሆንም ያደርገዋልና፤ በቡድኖቹ አለመኖር ሌላው ያመጣው ነገር ደግሞ በእነዚህ ቡድኖች ውስጥ የሚጫወቱት አብዛኛው ተጨዋቾች የአሁን ሰዓት ላይ ክለብ አልባም የሆኑበት እና ከያዙት ቤተሰብ እና ከራሳቸው አኳያም ህይወትን ለመምራት የተቸገሩበት ሁኔታም ስላለ የሁሉም ስፖርተኛ ምኞት የእነዚህ ተጨዋቾች ወደ ተለያዩ ክለቦች ገብተው እንዲጫወቱ ነው”፡፡

ከ13ቱ የሊጉ ተወዳዳሪዎች 3ቱ ላለመውረድ መጫወታቸው ነገሮችን ከባድ አያደርገውም…?

“እንደ ውድድር በጣም ነው እንጂ ከባድ የሚያደርገው፤ የሶስቱ ቡድኖች መውረድ ብቻ ሳይሆን ለሻምፒዮናነት መጫወት መቻሉም ከባድ ነገር ነው”፡፡

ካለፈው ዓመት አቋማቸው እና ከዘንድሮ ስብስባቸው አንፃር እነማን የዋንጫው ተፎካካሪ ይሆናሉ ብለህ ትገምታለህ…?

“በቅድሚያ እኛን ነው የዋንጫው ተፎካካሪ የማደርገው፤ በመቀጠል ደግሞ ፋሲል ከነማን ቅ/ጊዮርጊስንና ባህር ዳር ከተማን ነው በተፎካካሪነት የማስቀምጣቸው”፡፡

በአዲሱ ዓመት አንተስ ምንን ማሳካት ትፈልጋለህ…?

“ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የሊጉ ሻምፒዮና መሆን፣ የውድድር ዓመቱ ኮከብ ተጨዋች መባልና በሀገሪቱ ከሚገኙት ጠንካራ ተከላካዮች መካከል አንዱ የመሆንን እልም ማሳካት እፈልጋለውና ለዛም ራሴን እያዘጋጀው ነው”፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website