የጨዋታ ዘገባ | አፄዎቹ ፈረሰኞቹን በመርታት አመቱን በድል ጀምረዋል

 

ፋሲል ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን በሙጂብ ቃሲም ብቸኛ ግብ 1-0 አሸንፏል።

የ2013 የኢትዮጵያ ፕሪምየርሊግ ዛሬ ጥዋት 4:00 ስአት ላይ በሰበታ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ጅማሮውን አድርጎ 9:00 ላይም ቀጥሎ አፄዎችን እና ፈረሰኞቹን አገናኝቷል። በሁለቱም በኩል የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ በመስመር አጋድለው ተንቀሳቅሰዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ የነበራቸው ፋሲል ከተማዎች ሽመክት ጉግሳ ባቀበለው ኳስ በሙጂብ ቃሲም ጥቃት መሰንዘራቸውን ጀምረዋል። ፈረሰኞቹ በበኩላቸው ይህ ነው የሚባል አስደንጋጭ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።

 

44ኛው ደቂቃ ላይ አፄዎቹ ሱራፌል ዳኛቸው ከቅጣትምት ሲያሻማ ፓትሪክ ማታሲ በአግባቡ ሳይቆጣጠራት ቀርቶ በቅርብ ርቀት የነበረው ሙጂብ ቃሲም በቀላሉ ግብ በማስቆጠር ተጠናቆ ቀዳሚ በማድረግ የአመቱን የመጀመሪያ ግብ ማስቆጠር ችሏል። የመጀመሪያው አጋማሽ በዝች ብቸኛ ግብ ተጠናቆ በፋሲል ከተማ 1-0 መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል ።

በሁለተኛው አጋማሽ አፄዎቹ ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት ሲታትሩ ቢስተዋሉም ደቂቃዎች እየገፉ ሲመጡ ግን የያዙትን ውጤት ለማስጠበቅ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወትን ለመከተል ተገደዋል።

 

በአንፃሩ ፈረሰኞቹ አዲስ ግደይ በተሰለፈበት የግራ መስመር አጋድለው ተጫውተዋል። በዚህም ማታሲ በቀላሉ የተቆጣጠራትን ኳስ በእጅ ለቡድን አጋሩ ለማቀበል ሲሞክር ለበዛብህ መላዮ አቀብሎት ማታሲ ከግቡ ወጣ ብሎ ስለነበር ግቧን ለማስቆጠር ሲጣደፍ ሳይጠቀምባት ቀርቷል።

ጨዋታው ወደ መገባደዱ ሲጠጋ ፈረሰኞቹ ተጭነው በመጫወት አቻ ለመሆን ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቶ በአፄዎቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። አፄዎቹ የውድድር አመቱን በድል ሲጀምሩ ፈረሰኞቹ አመቱን በሽንፈት ለመጀመር ተገደዋል።

Hatricksport website Editor

Facebook

ሚሊዮን ኃይሌ

Hatricksport website Editor