“በጥሩ ሞራል ላይ እንገኛለን፤ ከእግዚአብሔ ጋር ኮትዲቯርን ረተን እናልፋለን ብዬ አምናለሁ” አሰልጣኝ ውበቱ አባተ (የዋልያዎቹ አሰልጣኝ)

“መላው ኢትዮጵያዊያንን በአንድነት የሚያስተሳስር ድል በመመዝገቡ ተደስቻለሁ”

“በጥሩ ሞራል ላይ እንገኛለን፤ ከእግዚአብሔ ጋር ኮትዲቯርን ረተን እናልፋለን ብዬ አምናለሁ”
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ (የዋልያዎቹ አሰልጣኝ)

ከትላንት ወዲያ ምሽት የተካሄደው ጨዋታ ኮትዲቫር ኒጀርን 3-0 በመርታት በ10 ነጥብ ሲመሩ  ማዳጋስካርን 4ለ0 የረቱት ዋሊያዎቹ በ5 ጨዋታ 9 ነጥብና 6 ግብ ይዘው የአፍሪካ ዋንጫ ምድብ አስራ አንድን በሁለተኛ ደረጃን መያዝ ችለዋል ፡፡ መላው ህብረተሰብ በሀገሩ የተካሄውን የብሔራዊ ቡድኑን ጨዋታ ማየት ባይችልም ባለማየቱ የተሰማው ሀዘን ግን በተገኘው አስደሳች ድል ተሸፍኗል፡፡ አማኑኤል ገ/ሚካኤል፣ ጌታነህ ከበደ፣ አቡበከር ናስርና ሽመልስ በቀለ ከመረብ ባሳረፏቸው አራት ግቦች ዋሊያዎቹ ማዳጋስከርን 4ለ0 ረትተው ለማክሰኞው አጓጊያ ፍልሚያ ተዘጋጅተዋል። ዋሊያዎቹ ባለፉት 3 ጨዋታዎች 11 ግብ አስቆጥረው የተቆጠረ አንድም ግብ አለመኖሩ አሰልጣኙ የተከላካይ መስመራቸው ላይ እየሰሩ ያሉት ስራ እየሰመረ መምጣቱን ያሳያል፡፡ አሰልጣኙ በክለቡ ተጠባባቂ የነበረውን ተክለማርያም ሻንቆ /ጎሜዝን/ በቋሚነት ተጠቅመው መረባቸው ሳይደፈር መውጣቱ ቁማሩን እንዲያሸንፉ ረድቷቸዋል፡፡ ጨዋታውን የመሩት የካሜሮን አርቢትሮች ጨዋታውን በጥሩ ሁኔታ መምራታቸው ደግሞ አስመስግኗቸዋል፡፡ 58 የልዑካን ቡድን ይዘው ባህርዳር ጃካራንዳ ሆቴል ያረፉት ማዳጋስካሮች ከሽንፈቱ በፊት የነበሩበትን መሪነት ለዋሊያዎቹ ለማስረከብ ተገደዋል፡፡ የዚህ ድል ዋነኛ መሪ የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ ስለተመዘገበው ድል፣ ስለነበረባቸው ትግልና ስላገኙት ድጋፍ፣ የድሉ መታሰቢያነት የማን እንደሆነ፣ ድሉ ስለፈጠረው አንድነት፣ በሞት ስለተለዩት አሠልጣኝ ስብስቤ ይባስና ሌሎች ጉዳዮች ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሀትሪክ፡- እንኳን ደስ አላችሁ? አረፋችሁ አይደል?

ውበቱ፡- /ሳቅ/እንኳን አብሮ ደስ አለን፡፡ ጥሩ ውጤት ነው የተመዘገበው እረፍቱማ ገና ነው /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- 4ለ0 ማዳጋስካርን ረታችሁ.. እንደ ማላዊ ጨዋታ ልምምድ አደርጋችሁት?
ውበቱ፡- የምን ልምምድ ትልቅ ጨዋታ ነበር የሚጠበቅን ጨዋታ ነው ያደረግነውም ያሸነፍነውም፡፡

ሀትሪክ፡- ውጤቱ ሰፍቷል… ጠበከው እንዴ?

ውበቱ፡- እግርኳስ የሚታየው የመጨረሻው ውጤቱ ነው…መታየት ያለበት ግን ከዚያ በፊት የነበረው ቡድን የመስራት ሂደትም መታየት አለበት ጎን ለጎን ቡድን እየገነባን ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- ጨዋታው ሲያልቅ አማተብክ.. እፎይ ነው?

ውበቱ፡- ማማተብኮ ማመስገን ነው ከ3 ጨዋታ በኋላኮ ደስታህን አታውቀውም የነበርክበት ነገር አታስብም ከውጤቱ በላይ ስራውን ነው የማየው የምሞክረው ነገርን የሚመስል ነገር ልጆቹ ላይ ማየት..በእንቅስቃሴው የሚሄድበት መንገድ ነው የሚያሳስብህ እኛ የምንጫወትበት ሂደት ነው የምመለከተው.. ያን ሳይ ነው የምደሰተው የበለጠ የተሻለ ነገር እንድሰራ ነው የሚያደርገኝ… ይሄ ውጤት ከነ ብዙ ክፍተታችን ከነ ብዙ ስህተታችን ጥሩ የሚባል ነው የታዩብን ጥቃቅን ስህተቶችን ደግሞ እያሻሻልን ስንሄድ ደግሞ የተሻለ ነገር እንሰራለን፡ እንዲህ ነው የሚሰማኝ… ከጭንቀት ጋር አላያያዝኩትም ነገር ግን ሁልጊዜም ድሉ ያስፈልገናል እንደ ሀገርም ውጤቱ ያስደስታል አንድ ስፖርት ቤተሰብ ደግሞ ትልቅ መልዕክት ነው ውጤቱ የተለመደ አይደለም ረጅም አመታት ከግብ ማስቆጠር ጋር የተያያዙ ከፍተኛ ክፍተቶች ነበሩብን ያ ነገር ትንሽ ሲሻሻል በማየቴ ተደስቻለሁ ጨዋታው ግን ብዙም የሚያስጨንቀን አይደለም፡፡

ሀትሪክ፡- በደረጃ የሚበልጡንን መርታት ምን ስሜት ይሰጣል?

ውበቱ፡- በወዳጅነት የገጠምነው ማላዊ ይሁን በነጥብ ጨዋታ የረታነው ማዳጋስካር እነርሱ በሚጫወቱበት መንገድ ብንጫወት ኖሮ የግጥሚያው ውጤት እንደዚህ እንደማይሆን ይገባናል ጨዋታውን ተቆጣጥረን ያሸነፍንበት መንገድ ነው የነርሱን አቋም ደካማ ያስመሰለባቸው እንጂ ሁለቱም በደረጃ ይበልጡናል ማላዊ 123ኛ ማዳጋስካርም ወደ 97 አካባቢ ናቸው እኛ ካለንበት 146ኛ አንፃር ያሸነፍነው የሚበልጡንን መሆኑ ያስደስታል ከድሉ በላይ ግን ድሉን ያገኘንበት መንገድ ነው ዋናው… የሚያናድደው ከዚያ መንገድ ሲያፈነግጡ ነው ያ ነው ስሜታዊ የሚያደርገው ከዚያ ውጪ ማሸነፋችን ደስ ብሎኛል ያውም የሚበልጡንን መሆኑ ደግሞ ለቀጣዩ ጨዋታ የሚያበረታታን ነው፡፡

ሀትሪክ፡- አራቱን ግቦች ያስቆጠሩት የተለያዩ ተጨዋቾች መሆናቸውስ ምን ትርጉም ይሰጣል?

ውበቱ፡- የተለያዩ ተጨዋቾች ግቦችን ማስቆጠራቸው የቡድኑን የጎል ማግባት አማራጭ ያሳፋል ይሄ ደግሞ ተጨዋቾቹም የራስ መተማመናቸውን እንዲጨምር ያደርጋቸዋል ከግቡ በላይ ግቡ የተቆጠረበት መንገድ ለእኛ ትልቁ ነገር… በዚ ላይ ስንሰራ ስለነበር ግቦቹ የቆጠሩበት መንገድ አስደስቶናል ለተጨዋቾቹም የራስ መተማመን ጥሩ ይመስለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- የግብ ጠባቂው አቋም ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖች አሉ፤… እርስዎስ ምን ይላሉ?

ውበቱ፡- ግብ ጠባቂ እንደ ሌሎቹ ተጨዋቾቹ መታየት የለበትም የራስ መተማመኑን ለማምጣት ጨዋታዎች የግድ ያስፈልጉታል በክለቡ ከጨዋታ የራቀ ተጨዋች ነው ሲሰራ የነበረው ነገር ከዚህ ጋር የሚገናኝ ነው እንጂ የብቃት ጉዳይ አይደለም በሂደትም ወደ ብቃት እንደሚመለስ ርግጠኛ ነኝ ለኔ ግን ዛሬ ያሳየው አቋም ከበቂ በላይ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- አዲስ አበባ፣ ጅማና ባህርዳር የነበረው ልምምድ በውጤቱ ትልቅ አስተዋፅኦ ነበረው ማለት ይቻላል?

ውበቱ፡- አንድ ቀን ብቻ አይደለም የሶስቱ ከተሞችም የልምምድ ጊዜያት ብቻም አይደለም ከመጀመሪያው የአሰልጣኝነት ቅጥር ጀምሮ ቡደኑን እንዴት አድርገን እናዋቅር፣ ኮቺንግ ስታፍ ምን ይምሰል ? ምን አይነት ኮቺንግ ስታፍ ያስፈልጋል? ምንአይነት ቡድን ነው የሚያስፈልገን? ምን አይነት ልጆችን ነው መስብስብ ያለብን፣ ምን አይነት ፕሮፋል ያላቸውን በየ ቦታው እንምረጥ? ምን አይነት መንገድ እንከተል አጨዋወታችን ምን ይመስል? ተጨዋቾቹን እንዴት አድርገንን ልንመራ ይገባል?የኒጀርን ጨዋታ እንዴት ልንወጣ እንችላለን የሚል ሰፊ ነገር ላይ ተነጋግረን ከሄድንበት በኋላ መንገዱስ ልክ ነበር ወይስ ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ ወደ 107 ገጽ ሪፖርት ለፌዴሬሽኑ አስገብተናል። በዚያ ላይ በቀጣይስ ምን እንሰራ የሚልም ነገርም አለ በጅማ፣ በአዲስ አበባ እና በባህርዳር የተዘጋጀነው ዝግጅት የሪፖርቱ አንድ አካል ነው ለማዳጋስካርና ለኮትዲቫር ጨዋታ ብቻ ሣይሆን በቀጣይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከመገንባት አንፃር በዚህ መንገድ ቢሄድ ጥሩ ነው ያልነውን ሃሳብ አካተንበታል ይሄ ደግሞ ከ17 እ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድንን የሚመለከት ነው… በአጠቃላይ ቡድኑ የሂደት ውጤት ነው የሚል ሃሣብ አካተንበታል፡፡

ሀትሪክ፡- የሊጉ ጥንካሬ ለብሔራዊ ቡድኑ ጥንካሬ መሰረት ሆኗል ማለት የምንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል?

ውበቱ፡- ሊጉ ላይማ ሁሌ በየአመቱ ፉክክር አለ ፉክክር የሌለበት አመት የለም ለምሣሌ ወደ አሰልጣኝነት ከገባሁበት ጊዜ ጀምሮ ፉክክር አለ አሁንም አለ በየቡድኑ ለኛ ፍላጎት አጨዋወትና ቡድን ግንባታ የሚሆኑ ከመምረጥ አንፃር ፕሪሚየር ሊጉ በዲ.ኤስ.ቲቪ በመተላለፉ ለየት ያለ አድቫንቴጅ ሰጥቶናል በቅርብ ያላቸውን አቅምም እንድንመለከት አድርጎናል ፉክክሩ ሁሌም አለ ነገር ግን ለብሔራዊ ቡድን ግንባታ ወሳኝ ሚና አላቸው ከምል ይልቅ በፉክክሩ ተጠቅመናል ብል ይቀለኛል ከዚያ ውጪ የብሔራዊ ቡድኑ አጨዋዋት ተረድተውና ተገንዘበው በዚያው ላይ እንዲፀኑ ማድረጋችን ጠቅሞናል ለምሣሌ ቅዱስ ጊዮርጊስን ብናይ ፉክክሩን ለአመታት ለብቻው ሲመራው ቆይቷል ከ2 ወይም ከ3 አመት ውጪ ማለት ነው ያን ያህል ልዩነት ቢኖርም ግን ፉክክሩ በየአመቱ አለ ለብሔራዊ ቡድኑ ይጠቅማል አይጠቅምም የሚለው ሃሣብ እንዳለ ሆኖ ማለቴ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ምርጥ የምትለው ልዩነት ፈጣሪ ተጨዋች ስም ልትጠራልኝ ትችላለህ?

ውበቱ፡- የሁሉም አስተዋፅኦ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል ሁሉም እንደ ቡድን ትልቅ ብቃታቸውን እንዲውም ያለ የሌላ ኃይላቸውን ተጠቅመው እንድናሸንፍ አድርገዋል የጌታነህ ከበደ የቅጣት ምት ግብ ምርጥ ናት ከግቧ በላይ ከኋላ መስመር የቡድን እንቅስቃሴና ተሰርቶ የመጣበት መንገድ ደስ ይላል ያ የቡድን ስራው ምርጥ እንደሆነ ያሳያልና የቡድን ድል ብንለው ይቀላል/ሳቅ/

ሀትሪክ፡- ፌዴሬሽኑስ ተገቢ ድጋፍ አድርጓል ማለት ይቻላል?

ውበቱ፡- የተለየ ነገር የለውም… ቡድኑን በተመለከተ የሚጠየቀውን ድጋፍ አድርጓል… በጥሩ ሁኔታ ቡድኑን ሲከታተል ነበር ይሄም ደስ የሚል ድጋፍ ነው ከዚያ ውጪ ክለቦቹ ተጨዋቾችን ከመልቀቅና ካለመልቀቅ ጋር በተያየዘ ይደርስ የነበረው ችግር ይታወቃል ያ ተቀርፎ ሁሉም ድጋፍ በማድረጋቸው ደስ ብሎናል ከዚያ ውጪ የተለያዩ አካላት ቡድኑን ደግፈዋል ይሄም ትልቅ ውጤት አምጥቷል ባይ ነኝ …ከዚያ ውጪ መንግስት ብሔራዊ ቡድኑን በደንብ መደገፍና ማገዝ አለበት በርግጥ መንግሥት የሚችለው ድጋፍ እያደረገ ነው ከዚህ በተሻለ ቅርበት ኖሮት ቢከተተል ደስ ይለኛል ብሔራዊ ቡድኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ውክልና ስላለው በደንብ መደገፍ አለበት ብዬ አስባለው

ሀትሪክ፡- የድሉን መታሰቢያነት ለማን ሰጠህ?

ውበቱ፡- ይሄኮ የኢትዮጵያዊያን ድል ነው የሁሉም ዜጋ ደስታ ነው ለይቼ ለእገሌ የምለው ነገር የለኝም የተመዘገበው ድል ለመላው ኢትዮጵያዊየን መታሰቢያነት ይሁንልን፡፡
ሀትሪክ፡- የመጀመሪያ ስልክ ደውሎ እንኳን ደስ አለህ ያለህ ሰው ማነው?

ውበቱ፡- /ሳቅ/ በፍፁም አላውኩም በርግጥም በዚህ ደረጃ የያዝኩት ነገር የለም ስልኬ ዝግ ስለነበር ማን ቀድሞ ስልክ እንደደወለ አላወኩም፡፡

ሀትሪክ፡- ቤተሰብ ጋር የነበረው ጭንቀት ቀለል አለ ማለት ይችላል?

ውበቱ፡- /ሳቅ በሳቅ/ ታዲያ እንኳን ቤተሰብ የሚያውቀኝ ሁሉ ይጨነቃል የቅርብ ሰው ጓደኛ የሙያ ባልደረቦች የሰፈር ሰዎች፣ አብሮ አደግህ.. ለቤተሰብ ቅርብ የሆነ ሁሉ መጨነቁ አይቀርም ጨዋታው ሀገርን የሚወክል እንደመሆኑ ብዙዎች ተጨንቀውበታል ከነኚሀ ሁሉ ወደ ቤተሰብ ስትመጣ ጭንቀቱ ፍርሃቱ ስጋቱ የበለጠ ይሆናል። እንኳን 110 ሚሊዮን ህዝብ የሚወክል ብሔራዊ ቡድን ይዤ ቀርቶ ክለብ እያሰለጠንኩ ቤተሰብ ሃሣብ ውስጥ መግባቱ አይቀርም አሁን ግን ቀለል ብሏቸው ደውዬ ሁሉ አናግሬያቸው ተዝናንተዋል ቤተሰብ ትልቅ እረፍት ላይ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- እግር ኳስ የኢትዮጵያዊያን ፍቅር አግኝቷል የናንተ ማሸነፍ መላው ኢትዮጵያዊያንን በደስታ አስጨፍሯል የዚህ ደስታ ዋነኛ መሪ በመሆንህ ምን ተሰማህ?

ውበቱ፡- ዋው እንዴት ደስ እንደሚል.. እግር ኳስ ምንያህል አንድ ልብ እንደሚያደርግማ አይቻለሁ ይሄ ትልቅ ደስታ የሚፈጥር ውጤት ነው ጨዋታው ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ በዝግ መሆኑ በተወሰነ የህዝቡ ደስታ ላይ ያጨለመው ነገር አለ ተመልከት ድሉ 60 ሺህ ህዝብ በስታዲየም ታድሞ የተከታተለው ግጥሚያ ቢሆን ምን አይነት ደስታ እንደሚኖረው… ያ ቀርቶ ለመላው ህብረሰብ እንዲደርስ ሁሉም በቲቪ የመከታተል እድል ቢያገኝ ምን አይነት ደስታ እንደሚኖር… ህብረተሰቡ የተወሰነ የማየት እድል ከመኖር ውጪ ሁሉም ጨዋታውን ተከታትሏል ብዬ አላምንም ድሉ በደጋፊዎች ታጅቦ አለመካሄዱ እንጂ መላው ኢትዮጵያዊያንን በአንድነት የሚያስተሳስር ድል በመመዝገቡ ተደስቻለሁ በበርካታ ግብ የታጀበ ድል መሆኑ ደግሞ ያስደስታል፡፡ የእግር ኳስ ድል ትልቅ ጥቅም ይሄ ነው ለመላው ኢትዮጵያዊንን እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ኮትዲቯርን በተመለከተ ውስጥህ ምን ይልሃል? እናልፋለን… ? ሶስት ኮከቦቿ በተለያዩ ምክንያት ከግጥሚያው ውጪ መሆናቸው ደግሞ እድሉን እያሰፋውም?

ውበቱ፡- በግሌ ኮትዲቯሮች በበሽታ ተጎድተው እንድናሸንፍ አልፈልግም እግር ኳስ ነውና በጥሩ ሁኔታ ተጫውተን ማሸነፍ እንደምንችል አምናለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- በጉዳት ተጨዋች ማጣትኮ እግር ኳስ ላይ ያለ ነገር ነው… ለምን አልተመቸህም?

ውበቱ፡- በዚህ ደረጃ ማሸነፍን አልፈልግም ፌር ባልሆነ መንገድ የሚመጣ ውጤት ደግሞ አይመቸኝም ነገር ግን ጥሩ ሞራል ላይ እንገኛለን ተጨዋቾቼም የማሸነፍ አቅም አላቸው ከእግዚአብሄር ጋር ኮትዲቯርን ረተን እናልፋለን ብዬ አምናለሁ፡፡ በተረፈ የተጋጣሚያችን ጉዳትና ውጤት አይቼ ለማሸነፍ የምጓጓበት ምክንያት የለኝም ጥሩ ደረጃ ላይ በመገኘታችን በርትተን የመፋለምና የአፍሪካ ዋንጫ ተካፋይነታችንን የማረጋገጥ አቅም አለን፡፡

ሀትሪክ፡- የአሰልጣኝ ሰብስቤ ይባስ ዜና እረፍት ላይ የምትለው ነገር አለ?

ውበቱ:- በጣም ነው ያዘንኩት… በጣም ቅር ብሎኛል አሰልጣኝ ስብስቤን በደንብ አውቀዋለው በዚህ ደረጃ ለዕልፈት በመዳረጉ አዝኛለሁ ለቤተሰቡ ለጓደኞቹ ለወዳጆቹ መፅናናትን እመኛለሁ፤ የሚያሳዝን ዜና ሆኖብኛል፡፡

ሀትሪክ፡- የመጨረሻ ምስጋና …?

ውበቱ፡- በተገኘው ድል ተደስቻለሁ.. እንደሚታወቀው ተጨዋቾች ከሌሉ ክለቦችም እግር ኳስም አይኖርምና ለተገኘው ድል የቅድሚያ ምስጋና ለተጨዋቾቼ ይሁን…ከዚያ በመቀጠል አብረውኝ ለሚሰሩትና በደንብ እየረዱኝ ላሉ የአሰልጣኞች ቡድን አባላት፣ ተጨዋቾቻቸውን በምፈልገው ጊዜ ለቅቀው ተገቢ ዝግጅት እንድናደርግ የበኩላቸው ሚና ለተወጡት ክለቦች፣ በሶስት ከተማ በነበረው ዝግጅት ሙሉ ድጋፍ ላደረጉ ባለሙያዎችና ደጋፊዎች ለኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሙሉ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport