“ጥሩ ውጤት እያመጣንና እየተሻሻልን ነው፤ እንዳለን አጠቃላይ ብቃት ግን የሚመጥነን ውጤት እያስመዘገብን አይደለንም” ሳላአምላክ ተገኝ /ባህርዳር ከተማ/

ባህርዳር ከተማ ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉን አዳማ ከተማን በፍፁም ዓለሙ ብቸኛ እና ምርጥ ግብ 1-0 በማሸነፍ በሜዳው የነበረውን ቆይታ በጥሩ ውጤት አጠናቋል።ባህርዳር ከተማ በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የእስካሁን ተሳትፎ ለሻምፒዮንነት ከሚፎካከሩት እና እድላቸውም ካልተመናመኑት ቡድኖች መካከል አንዱ ሲሆን ከዚህ ክለብ ጋር በተያያዘ እና ስለ ራሱም የግል ተሳትፎው ለቡድኑ ጥሩ እንቅስቃሴን እያሳዩ ካሉት ተጨዋቾች መካከል ሳላአምላክ ተገኝ /አማራውን/ የሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ አነጋግሮት ተጨዋቹ የሚከተለውን ምላሽ ሊሰጠው ችሏል።

ሀትሪክ፦ በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ አዳማ ከተማን በማሸነፍ የባህርዳር ቆይታችሁን በስኬት አጠናቃችኋል፤ ጨዋታው ምን መልክ ነበረው? በድሉስ ምን አይነት ስሜት ተሰማህ?

ሳላአምላክ፦ ከአዳማ ጋር ያደረግነው የሜዳችን ላይ ጨዋታ በጣም አሪፍ እና ጥሩ ነበር፤ የግጥሚያውን 3 ነጥብ እና በአጠቃላይም ባህርዳር ላይ በነበረን ቆይታ ከ12 ነጥብ 10ሩን ስላሳካን በጣም ተደስተናል። ወደ ጨዋታው ሳመራ ተደጋጋሚ ግብ የማስቆጠር ዕድሎችን በተጋጣሚያችን ላይ በመፍጠር እኛ የተሻልን ነበርን፤ ከእነዛ ውስጥም አንዱን ወደ ግብነት በመቀየርም ጨዋታውን አሸንፈን ወጥተናል።

ሀትሪክ፦ ስለ ተጋጣሚያችሁ አዳማ ከተማስ ምን አልክ?

ሳላአምላክ፦ አዳማ ጥሩ ቡድን ነው። ያን ዕለት ግን በመከላከል ላይ ያመዘነን እንቅስቃሴ ሊከተል ችሏል፤ እኛም ያን ስላወቅን ኳሱን ይዘንና ቶሎ ቶሎም ወደ እነሱ የግብ ክልል በመግባት ጎል ለማስቆጠር ስንጥር ነበር። ያም ተሳክቶልን አንድ ግብን በፍፁም ዓለሙ አማካኝነት ልናስቆጥር ችለናል። ከዚህ ግብ በኋላም አንድ ግብ ማግባት ብቻ አስተማማኝ ስላልሆነ ምክንያቱም እንዳለፈው ከጅማ አባጅፋር ጋር ስንጫወት 2-1 ከመራን በኋላ በመጨረሻው ሰዓት ላይ ግብ ተቆጥሮብን አቻ ተለያይተናልና ያ ዳግም እንዳይፈጠር አሰልጣኛችን ፋሲል ተካልኝ ሌላ ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር እንዳለብን ቢነግረንም ያ ለእኛ ፈታኝ እና ራሳችን ላይ እንደውም ግብ እንዳይቆጠርብን ስጋት ሊሆንብንም ችሏል።

ሀትሪክ፦ ባህርዳር ከተማ እያሳካቸው ያሉት ተደጋጋሚ ድሎች ወደ ደረጃ ፉክክሩ ውስጥ እንዲጠጋ አስችሎታል፤ የእዚህ የውጤታማነት ሚስጥሩ ምንድን ነው?

ሳላአምላክ፦ ዋናው ያለን ህብረትና አንድነት ሁሌም የማይቀየር መሆኑ ነው። ከዛ ውጪም በእያንዳንዱ ጨዋታዎቻችን ላይም ምን ማድረግ እንዳለብንም እንነጋገራለንና ያ ጠቅሞናል። ሆኖም ግን በዚህ መልኩ እስካሁን እየተጓዝን ቢሆንም በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ላይ ያስመዘገብነው አጠቃላይ ውጤት ግን እኛን ፈፅሞ አይመጥነንም።

ሀትሪክ፦ የእስካሁኑ ውጤት እናንተን ካልገለፃችሁ የት ደረጃ ላይ ነበር መገኘት የነበረባችሁ ?

ሳላአምላክ፦ ባህርዳር እንደያዘው ጥሩ ቡድንና ጥንካሬው በዚህ ሰዓት ላይ 33 ነጥብን ይዞ ነበር ፋሲል ከነማን መከተል የነበረበት፤ ያ ሊሳካ አልቻለም። ሆኖም ግን በኋላም ላይ ቢሆን ቡድኑ ችግሩን ተረድቶና በጣላቸው ነጥቦችም ተቆጭቶ በመስራት ወደ አሸናፊነት ሞራሉም መመለሱ በጥሩነቱ ሊጠቀስ የሚችል ነው።

ሀትሪክ፦ አዳማን በረታችሁበት ግጥሚያ ጥሩ ለመንቀሳቀስ ችለሃል፤ ምርጡ ጨዋታህ ያ ነው?

ሳላአምላክ፦ ለእኔ አይደለም። እንደዛም ሆኖ ግን በእሱም ጨዋታ ላይ ጥሩ ልንቀሳቀስ ችያለው። የእኔ ምርጡ ጨዋታዬ የምለው እና ከሁሉም የሚበልጥብኝ ግን ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ስንጫወት ያደረግነው እና እኔም የድሉን ግብ ያስቆጠርኩበትን ፍልሚያ ነው።

ሀትሪክ፦ ባህርዳር ከተማ እያደረጋቸው ባሉት የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ በችሎታህ ከፍተኛ መሻሻል እያሳየህ ነው ልበል?

ሳላአምላክ፦ አልተሳሳትክም አዎን፤ ጥሩ መሻሻልን እያሳየው ነው። ከዚህ በፊት የግራ እና የቀኝ ፉልባክ ተጨዋች ሆኜ ነበር ቡድኔን የማገለግለው አሁን ግን የመስመር አጥቂ ሆኜ መጫወቴ ነው ለመሻሻሌ ምክንያት የሆነኝ ይሄ ቦታ ኢትዮጵያ ቡና እያለውም ከተተኪው ቡድን አንስቶ እስከዋናው ቡድን ደረጃ ድረስም የተጫወትኩበት ስፍራም ስለሆነ በጣም ተመችቶኝ ነው እየተጫወትኩበት ያለሁት።

 

ሀትሪክ፦ የባህርዳር ቆይታችሁ ተጠናቀቀ፤ ከ21 ቀን እረፍት በኋላ ደግሞ ወደ ድሬዳዋ ከተማ ታመራላችሁ። በእዛ የውድድር ጉዞአችሁ ምን ይገጥማችሁ ይሆን?

ሳላአምላክ፦ ከባህርዳር ቆይታችን በተሻለ ጥሩ የውድድር ጊዜን የምናሳልፍ ይመስለኛል። ምክንያቱም ቡድናችን በአሁን ሰዓት ላይ እየተሻሻለ እየመጣ ነው። የድሬዳዋው ውድድር ደግሞ ወደ ሻምፒዮና ተፎካካሪነት ለማምራት ፍንጭን የሚሰጥም ነገር አለውና ለዛም ነው ለውድድሩ በጣም ጠንክረን ስለምንመጣ መልካም ጊዜያቶች ይኖሩናል ያልኩት።

ሀትሪክ፦ የባህርዳር ከተማው ፍፁም ዓለሙ /ስስ/ ለቡድኑ ተደጋጋሚ ግቦችን እያስቆጠረ ይገኛል፤ ስለ እሱ ምን ማለት ይቻላል?

ሳላአምላክ፦ ይሄ የቡድናችን አጋር ጥሩ ብቃት ያለው ተጨዋች ነው። ጎል በማስቆጠርና የተመቻቹ ኳሶችን ለጓደኞቹ በማቀበልም እየጠቀመን ይገኛል።

ሀትሪክ፦ ባህርዳርን በያዘው የተጨዋቾች ስብስቡ በምን መልኩ ትገልፀዋለህ?

ሳላአምላክ፦ እንከን የማይወጣለት ጥሩ የተጨዋቾች ስብስብ ነው ያለን። ያን ተመልክቼም ነው ቡድናችን እስካሁን ባስመዘገበው አጠቃላዩ የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ውጤት የሚመጥነው አይደለምም ያልኩት።

ሀትሪክ፦ በባህርዳር የተጨዋችነት ቆይታ ቡድኑን ከዚህ በኋላስ የት ድረስ ትጠቅመዋለህ? በአካል ብቃቱስ ላይ ለውጥ አለህ ልበል?

ሳላአምላክ፦ አዎን! አሁን ላይ ከቡድኔ ልምምድ በተጨማሪ በግሌም በአካል ብቃት ልምምድ ላይ ጠንክሬ እየሰራሁ ስለሆነ በራሴ ላይ ከፍተኛ መሻሻልን እየተመለከትኩኝ ነው። ይህን ካልኩ በቀጣይ ጊዜ የቡድኑ ቆይታዬ ደግሞ አሁን ያገኘሁትንና በጣምም እየተደሰትኩበት ያለሁትን በቋሚ ተሰላፊነት ቡድኔን እየጠቀምኩ የምገኝበትን ብቃቴን ይበልጥ አሻሽዬ በማስጓዝ ቡድኔን ለስኬት ለማብቃት ከፍተኛ ጥረትን አደርጋለሁ።

ሀትሪክ፦ የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ በ12 የነጥብ ልዩነት እናንተን ከመብለጡ አንፃር ከዋንጫው ፉክክር ወጥታችኋል?

ሳላአምላክ፦ በርካታ ጨዋታዎች ከመቅረታቸው አኳያ እኛ እንደዛ ብለን አናስብም። የእኛ ሀሳብ ከፊት ፊት ያሉብንን ጨዋታዎች እያሸነፍን በመጓዝ ወደፊት የሚሆነውን ነገር ማየት ነው። ምክንያቱም አንደኝነትን ስታስብም ነው ሁለተኝነትንም ልታገኝ የምትችለውና ከፉክክሩ ገና አልወጣንም።
ሀትሪክ፦ ሳላአምላክ ከብቃቱ ውስጥ ምንን ማሻሻል ይፈልጋል?
ሳላአምላክ፦ ግብ ጋር የመድረስ ብቃቱ ስላለኝ ተደጋጋሚ ጎሎችን ማስቆጠር ይኖርብኛል።

ሀትሪክ፦ ወደ ትዳር ህይወትም ገብተሃልና እስኪ አንድ አንድ ነገር በለን?

ሳላአምላክ፦ አዎን፤ ትዳርን መስርቼ በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው እየኖርኩ ያለሁት። ባለቤቴም ኪያ ታፈሰ ትባላለች። የአምስት ዓመቷ አሚን እና ገና ሁለት ወር የሆናት ክርስቲያን የሚባሉ ሴት ልጆችም አለን። ባለቤቴን በተመለከተ ኢትዮጵያ ቡና ከነበርኩበት ጊዜ ጀምሮ አብራኝ ያለች ነች። ጥሩም የትዳር አጋሬ ናት በጣምም ነው የምታስብልኝ። ከእግር ኳስ ተጨዋችነቴ ጀርባም የእሷ ከፍተኛ ድጋፍም ነው ለዚህ ያደረሰኝና በጣም ላመሰግናት እፈልጋለሁ።

ሀትሪክ፦ እናጠቃል….?

ሳላአምላክ፦ በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኔ አሁን የመጣሁበትን መንገድ በዚህ ደረጃ ላይ ብቻ እንዲቆም አልፈልግም። የእኔ እልም ፈጣሪ ይርዳኝ እንጂ ለሀገሬ ብሄራዊ ቡድን ተመርጬ እስከመጫወትና እስከማገልገል ብሎም ደግሞ እንደ እነ ሽመልስ በቀለ ከሀገር ወጥቶም በፕሮፌሽናል ደረጃ ላይ መጫወትም ነውና ያን ዕድል ለማግኘት ተግቼ እሰራለሁ።
በኳስ ተጨዋችነቴ እስከዛሬ ከጎኔ ሆናችሁ ለምታበረታቱኝ ቤተሰቦቼ፣ የቡድን አጋሮቼን፣ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን፣ ባለቤቴንና ለሌሎች አካላቶችም ምስጋናዬ ላቅ ያለ ነው።

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website