“ዘንድሮ ጉዳት ጭምር ከሜዳ አርቆኝ ለቡድኔ በምፈልገው ደረጃ አልተጫወትኩም ነበር፤ አሁን ላይ ግን ኢትዮጵያ ቡናን ለመጥቀም በሚያስችለኝ ጥሩ አቋም ላይ ነው የምገኘው”ሚኪያስ መኮንን /ኢትዮጵያ ቡና/

በመሸሻ ወልዴ

የኢትዮጵያ ቡናው ሚኪያስ መኮንን የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ላይ ስለነበራቸው የእስካሁኑ የውድድር ተሳትፎና ስለምርጡ ትዝታ እንደዚሁም ደግሞ በድሬዳዋና በሐዋሳ ከተማ ስለሚኖራቸው ቀጣይ የሊጉ ጉዞና ስለ ራሱ ከጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ጥያቄ ቀርቦለት ምላሽን ሰጥቷል።

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ እያደረጉት ስላለው የውድድር ተሳትፎ

“በእስካሁኑ ጉዞአችን በአብዛኛው ጥሩ ዓመትን ነው እያሳለፍን የምንገኘው። እንደዛም ሆኖ ግን በራሳችን ስህተት ከወላይታ ዲቻ፣ ከወልቂጤ ከተማ እና ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ባደረግናቸው ጨዋታዎች ላይ ማሸነፍ የነበሩብንን ግጥሚያዎች አንዳንዶቹ ቡድኖች ጥሩ ሳይሆኑ ቀርተው ነጥቦችን የጣልንበት ግጥሚያዎች ነበሩና ለዛ ላጣነው ውጤት ራሳችንን ነው የምንወቅሰው”።

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ከመቋረጡ በፊት ባህርዳር ላይ የነበራችሁ የውድድር ቆይታ ለየት ይል ነበር?

“አዎን እንደ ቡድን ጥሩ ቆይታ ነበረን። የመጫወቻ ሜዳውም ኳስን ተቆጣጥረ ለመጫወት በደንብ ያስችልም ነበር። ካደረግናቸው ጨዋታዎች ውስጥም ያሸነፍንበት ቁጥሩም ከፍ ይልም ነበር። አንድ ጨዋታን ብቻ አቻ ስንለያይ አንድ ጨዋታን ደግሞ ልንሸነፍ ችለናል”።

በባህርዳር ስለነበረው ምርጡ ትዝታ

“ምርጡ ትዝታዬ ከዚህ በፊት በጀልባ በመሄድ ገዳማትንና ቤተክርስቲያንን የማየት እድሉ አልነበረኝም። ባህርዳር በነበረን ቆይታ ግን ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ እነዚህን በተለይ የማሪያም ቤተክርስቲያንን ላይ እና ከዛ ውጪም ብዙ ነገሮችንም በመመልከት ለመዝናናትም ችያለሁ”።

ፋሲል ከነማ በመመራት ላይ የሚገኘውን ሊግ ቀልብሰው የደረጃ ሰንጠረዡን ይመሩ እንደሆነና ሻምፒዮና ስለመሆን እድላቸው

“በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በዚህ ሰዓት ላይ ካለን ጥሩ ብቃት እና እንደ ቡድንም ጥሩ ከመጫወታችን አንፃር የሊጉ መሪ ብንሆን ኖሮ በጣም ደስ ይለን ነበር። የውድድሩ ሻምፒዮና የመሆን እድላችንም በጣም ከፍ ይል ነበር። ግን መሪ ለመሆን አልቻልንም። ቢሆንም ግን በቁጥር ስሌት አሁንም ውድድሩ ገና በርካታ ጨዋታዎች ከፊታችን ያሉት ከመሆኑ አንፃር መሪ የምንሆንበትና ሻምፒዮና የምንሆንበት እድላችንም ስላልተሟጠጠ በቀጣይ ጨዋታዎቻችን ውጤቱን ለማጥበብ እና የሚመጣውን ውጤትም ለመቀበል ዝግጁም ነንና ያንን እየተጠባበቅን ነው”።

ለኢትዮጵያ ቡና በተከታታይ ግጥሚያዎች ላይ ተሰልፎ ስላለመጫወቱ፤ ብቃቱ እንደ ቀድሞ አለመሆኑና በቅርብ ጊዜ ውስጥ ደግሞ ለቡድኑ ተሰልፎ ስለመጫወቱ

“ዘንድሮ ለቡድኔ በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ተሰልፌ ያልተጫወትኩት 4ኛ ሳምንት ላይ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር የነበረን ጨዋታ ላይ ተጎድቼ ስለነበር ነው። ጉዳት ደግሞ በእግር ኳስ ላይ የሚያጋጥም አይነት ስለሆነ ያ ከሜዳ አርቆኝ የነበረው ሁኔታ ለቡድኔ በምፈልገው መልኩ እንዳልጫወት አድርጎኝ ነበር። ከእኔ ብቃት ጋር በተያያዘ የእውነት ነው ተሰልፌ የመጫወት እድልንም ባገኘሁባቸው ጨዋታዎች ቀድሞ ደርሶብኝ የነበረው ጉዳት ጭምር እንደበፊቱ በምፈልገው መልኩ እንድጫወት አላደረገኝም ነበር። ይሄ እንኳን አይደለም እኔን የዓለም የኳስ ክዋክብቱን እነ ሊዮኔል ሜሲንም የሚያጋጥማቸው ጊዜም አለ። ደግሞም በቋሚነት መሰለፍ ብቻ ጥሩ ተጨዋች መሆንም አይደለምና በዚህ ሰዓት ግን በሁሉም መልኩ ሙሉ ለሙሉ በመልካም ጤንነት ላይ የምገኝበት ወቅት ላይ ስለሆንኩኝ ክለቤን በጥሩ መልኩ አገለግለዋለውኝ”።

በድሬዳዋ ከተማ ስለሚኖራቸው ተሳትፎ

“እንደ ቡድን ከጓደኞቼ ጋር ጥሩ በመጫወት ክለባችን ውጤታማ እንደሚሆን አስባለሁ።
ይህ የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታችንም ወደ ዋንጫው ለምናደርገው ጉዞም ወሳኝ ስለሆነ በርካታ ነጥቦች ሊኖረንም የግድ ነው የሚለው”።

ጎል ከማስቆጠር ጋር ስለመራራቅ

“በዚህ ዓመት ላይም አንድ ጎልን ነው ያስቆጠርኩት። የእውነትም ከጎል ማስቆጠሩ ጋር በተያያዘ ብዙ የሚቀሩኝ ነገሮችም አሉ። በጣም ስለምጓጓም ነው የግብ ሙከራ ለማድረግ ጥረትን እያደረግኩኝ ሁሉ ሳይሳካልኝ የቀረው። በቀጣዩ ጊዜ ግን ተደጋጋሚ የመጫወት እድሎችን ሳገኝ ይሄን ችግሬን መቅረፍ እፈልጋለሁኝ”።

በቤትኪንግ የፈተናቸው ክለብ

“ወልቂጤ ከተማ ነዋ! እነሱ ኳስን ተቆጣጥረው በመጫወት ጥሩ ነበሩ። ከብዙዎቹም እኛ ከገጠምናቸው ክለቦች የተሻሉም ነበሩና እነሱን ነው የምጠቅሰው”።

ስለ አቡበከር ናስር

“ብዙ ነገሮችን ስለ እሱ በተደጋጋሚ ጊዜ ተናግሬአለሁ። ለክለባችን ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ብዙ ነገሮችን እየሰራም ነው። ሀገርን ደግሞ ለአፍሪካ ዋንጫም ካሳለፉት የብሄራዊ ቡድናችን ተጨዋቾች መካከልም ይሄ ዉዱ ጓደኛዬ አንዱ በመሆኑም በጣም ደስ ብሎኛልና በዚህ አጋጣሚ እንኳን ደስ ያለህም እለዋለሁ። አቡኪ አሁን ምርጥ በሆነ ብቂት ላይ ነው የሚገኘው። ጥሩ አቅም ስላለውም የሀገሪቱን የግብ ሪከርድ የሚሰብረውም ነው የሚመስለኝ”።

በመጨረሻ

“በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎአችን አሁንም ለአሰልጣኛችን ካሳዬ አራጌ የጨዋታ ታክቲክ ታማኝ ሆነን በመቀጠል እስከ ፍፃሜው ጨዋታ ድረስ ጥሩ ውጤትን ለማምጣት ዝግጁ ነን። ኢትዮጵያ ቡና ዘንድሮ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት አሁንም እድሉ አላከተመም በዚህ ሙከራ ያደርጋል። ይሄ ባይሳካለት እንኳን ሊጉን በሁለተኛ ደረጃ ፈፅሞ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ደረጃ ለመወዳደርና ሀገርንም ወክሎ ለመጫወትም ይፈልጋልና ለዛም ጥረትን እያደረገ ነው የሚገኘው”።

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *