በቢትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ5ኛው ሳምንት ጨዋታ ፋሲል ከነማ እና ባህር ዳር ከተማ ዛሬ ብርቱ ፉክክርን አድርገው 2-2 በሆነ የአቻ ውጤት ሊለያዩ ችለዋል።
በኢንተርናሽናል አልቢትር በላይ ታደሰ የተመራው የሁለቱ ቡድኖች ተጠባቂ ጨዋታ የተለያዩ ትህይንቶችን አስተናግዶም የተጠናቀቀ ሲሆን በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የፋሲል ከተማው አጥቂ ሙጂብ ቃሲም ክለቡ ለመሪነት የበቃበትን የፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሮ ለመምራት ቢችሉም በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ የባህር ዳር ከተማው አጥቂ ወሰን አሊ በሁለት ቢጫ ካርድ በቀይ ካርድ ከወጣ በኋላ በሁለተኛው አጋማሽ ሌላኛው የቡድኑ አጥቂ ባዬ ገዛኸኝ ባስቆጠረው ግብ ባህር ዳሮች ግጥሚያውን አቻ አድርገውት እና መልሰውም ደግሞ በምንይሉ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ 2-1 ሊመሩ ቢችሉም ወደ አሸናፊነቱ እያመሩ በነበረበት ሰዓት የፍፁም ቅጣት ምቱን ያስቆጠረው ምንይሉ በፋሲል ከነማው ተጨዋች ሽመክት ጉግሳ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ በቀይ ካርድ በመውጣት ቡድኑ በ9 ልጅ እንዲጫወት በመገደዱ በስተመጨረሻ ፋሲሎች የሁለተኛው አጋማሽ ላይ ተቀይሮ በገባው በናትናኤል ገብረጊዮርጊስ አማካኝነት የአቻነት ግብን አስቆጥረው ጨዋታው በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ ከእረፍት በኋላ ለባህር ዳር ከተማ ክለብ ተቀይሮ በመግባት ቡድኑን ለመሪነት ያበቃውን ግብ በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሮ ማሊያ በማውለቁ ቢጫ የተመለከተው እና ሌላ በሰራው ጥፋትም በሁለት ቢጫ ካርድ በቀይ ካርድ የወጣውን ምንይሉ ወንድሙን በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አናግሮት ምላሽን ሰጥቶታል።
ሀትሪክ፦ ከፋሲል ከነማ ባደረጋችሁት ጨዋታ ተቀይረህ ገብተህ ቡድንህ ለመሪነት የበቃበትን ግብ ማስቆጠር ችለህ ነበር፤ ያም ሆኖ ግን በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጣህና ቡድንህ ላይ በተቆጠረው ግብ አቻ ተለያያችሁ። በእዚህ ዙሪያ ምን ትላለህ?
ምንይሉ፦ ከፋሲል ከነማ ጋር ባደረግነው የዛሬው ጨዋታ ቡድናችን እየተመራ በነበረበት ሰዓት ለቡድኔ ተቀይሬ ገብቼ የተሻለ ነገርን ለመስራት እና ቡድናችንም ለመሪነት የበቃበትን ግብ ለማስቆጠር ችዬ ነበር። ያም ሆኖ ግን በፍፁም ቅጣት ምት ለመሪነት ያበቃችንን ግብ ሳስቆጥር ከእኔ በማይጠበቅ ስህተት ማልያ በማውለቅ ቢጫ ካርድ በማየቴና ሌላም ጥፋት ሰርቼ በቀይ ካርድ ከሜዳ በመውጣቴ ቡድኔ አሸናፊ መሆን የሚችልበትን ዕድል አሳጥቼዋለሁ። በዛም በጣም አዝኛለሁ። ለእዚህም ቡድኔን አሰልጣኞቼን የቡድኔን ተጨዋቾች እና ደጋፊዎቻችንን ይቅርታ እጠይቃለሁ።
ሀትሪክ፦ ማሊያ ማውለቅ ቢጫ ካርድ እንደሚያሰጥ ይታወቃል። ካወለቁ በኋላ ደግሞ ሌላ ከበድ ያለ ጥፋት ከተሰራ ወይ በሁለት ቢጫ ካርድ አለያም ደግሞ በቀጥታ ቀይ ካርድ መውጣት የግድ ይላልና አንተም በዛሬው ጨዋታ አንዱን ፈፀምክ…..
ምንይሉ፦ ልክ ነህ። ይህ እንግዲህ እግር ኳስ ነው። ቡድናችን ለመሪነት እንዲበቃ ያደረገችውን ግብ ሳስቆጥር በጎዶሎ ልጅ ሆነን እንጫወት ስለነበር እና ሶስት ነጥብንም እናገኛለን ብዬም ስላሰብኩ በደስታ ስሜቴን መቆጣጠር ስላልቻልኩ ነበር ማሊያ አውልቄ የመጀመሪያውን የማስጠንቀቂያ ካርድ የተመለከትኩት። ከዛ በኋላም ሌላ ፋውል መስራት አልነበረብኝምና እኔ ግን ሰርቼ በቀይ ካርድ ወጣሁ። ለእዚህ ራሴን እወቅሰዋለሁኝ።
ሀትሪክ፦ የሁለታችሁ ጨዋታ ምን መልክ ነበረው? ስለተጋጣሚያችሁ ፋሲል ከነማስ ምን ትላለህ?
ምንይሉ፦ የዛሬው ጨዋታ እስከመጨረሻው ሰዓት ድረስ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት እና የእኛም ቡድን በጎዶሎ ልጅ ተጫውቶ የተሻለም የነበረበት ነው። ከዛ ውጪም
በዳኝነት ስህተቶች አልፎ አልፎ ግጥሚያው ወደመበላሸት ሊያመራ የሚችልበት እድል ሊኖረው ቢችልም ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ውጤቱንም አሜን ብለን ተቀብለናል።
ፋሲል ከነማን በተመለከተ ጥሩ እና ኳስ ይዞ የሚጫወት ቡድን ነው። በዛሬው ጨዋታ ግን እኛ የተሻልን ነበርን።
ሀትሪክ፦ የአቻ ውጤቱ ለሁለታችንም በቂ /ፌር/ ነው እያልክ ነው….?
ምንይሉ፦ አይደለም። በጨዋታው ብዙ ከመልፋታችን አኳያ ውጤቱማ ለእኛ አይገባንም። ጨዋታውን ማሸነፍም እንችል ነበር። ምክንያቱም የአቻነቱ ግብ የተቆጠረብን እና ነጥቡን የተጋራነው ባለቀ ሰዓት ላይ ነውና አንድአንዴ በኳስ እንዲህ ያለ ነገር ያጋጥማል።
ሀትሪክ፦ የቡድናችሁን ወቅታዊ አቋም በምን መልኩ ትገልፀዋለህ?
ምንይሉ፦ ጥሩ ቡድን እና ጥሩ አሰልጣኝ አለን። ከጨዋታ ወደ ጨዋታ የተሻለ ነገርንም እያሳየን ነው። በሊጉ አሉ ከሚባሉት ቡድኖች ውስጥም ከፍተኛ የተጨዋቾች ስብስብን የያዝንምም ነንና ይሄን በመልካም ሁኔታ ነው የምገልጸው።
ሀትሪክ፦ ባህር ዳር ከተማ በቤትኪንጉ የት ድረስ ይጓዛል?
ምንይሉ፦ ያለ ምንም ጥርጥር እስከ ዋንጫው ድረስ ነዋ! ለእዛም የሚፈትነም ቡድን አለን ብዬም አላስብም። ምክንያቱም የሚፈትነንን ቡድን በዛሬው ዕለት በጎዶሎ ልጅ ተጫውተን ስላየነው ዋንጫ የማናነሳበት ምንም ምክንያት የለም።
አስተያየት ይስጡ