“ኢትዮጵያ ቡናን ለሚያህል ታላቅ ቡድን በእዚህ ፍጥነት እጫወታለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር” ዊሊያም ሰለሞን /ኢትዮጵያ ቡና/

 

በሐረር ከተማ ተወልዶ ያደገው ዊሊያም ሰለሞን በታዳጊነት ዕድሜው ለኢትዮጵያ ወጣቶች አካዳሚ ቡድን ለመሰልጠንና ለመጫወት ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ የትውልድ ሀገሩ ላይ ስለ ኢትዮጵያ ቡና ከሚሰማው ነገር በመነሳት የክለቡ ደጋፊ ለመሆን እንደቻለ እና ዛሬ ላይ ደግሞ ፈፅሞ ባልጠበቀው መልኩ የእዚሁ ትልቅ ቡድን ተጨዋች ሆኖ የክለቡን መለያ በማጥለቅ ሊጫወት በመቻሉ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማው ለሀትሪክ ስፖርት ድረ ገፅ አስተያዩቱን ሰጥቷል።

ኢትዮጵያ ቡናን በዝውውር መስኮቱ ከመከላከያ ክለብ በመምጣት የተቀላቀለው እና በቤትኪንግ የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታ ላይም ተቀይሮም ሆነ በቋሚ ተሰላፊነት በመግባት የተጫወተው እና ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴንም ያሳየው ዊሊያም 58 ኪሎ ግራም የሚመዝን ሲሆን 1ሜትር ከ61 ሜትርም ይረዝማል። ይህን ተጨዋች ከኳስ ጅማሬው አንስቶ አሁን ኢትዮጵያ ቡናን እስከተቀላቀለበት እና ለቡድኑም ተሰልፎ ለመጫወት እስከቻለበት ጊዜ ድረስ ባሉት ጉዳዮች ዙሪያ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አናግሮት የሰጠው ምላሽ የሚከተለውን ይመስላል።

ስለ ኳስ ጅማሬው

“የኳስ ጅማሬዬ ተወልጄ ባደግኩበት ሐረር ከተማ ፖሊስ ሜዳ ላይ ነው፤ እዛም ነው ከህፃንነት ዕድሜዬ አንስቶ የምወደውን ኳስ ለመጫወት የቻልኩት”።

ኳስን መጫወት ሲጀምር ቤተሰብ ጋር ስለነበረው አመለካከት

“እነሱ ኳስ መጫወቴን ይደግፉት ነበር። ከዛ በተጨማሪ ትምህርቴንም እንድማርም ጭምር ያበረታቱኝ ነበርና የእነሱ ድጋፍና እገዛ ከፍ ያለ ነበር”።

ከዊልያም ውጪ በሌላም ስም ስለመጠራቱ

“አዎን። ሐረር ላይ አበጋዝ ብለው የሚጠሩኝ አሉ።”

በታዳጊነት ዕድሜው ኳስን መጫወት ሲጀምር አድንቆት ስላደገው ተጨዋች

“ይሄ ተጨዋች አቤል እንዳለ ይባላል። ለደደቢት ተጫውቶ ካሳለፈ በኋላ በአሁን ሰዓት ላይ ደግሞ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በመጫወት ላይ ይገኛል። እሱን ነው የኳስ ተምሳሌቴ አድርጌ ያደግኩት። አቤል በሐረር ከተማ ውስጥም የሰፈሬ ልጅ ነው። በአካባቢያችን በኳሱም አሉ ከሚባሉት ተጨዋቾች መካከልም አንዱ ነው።

የእግር ኳስን ተጫውቶ ስለመጣበት መንገድ

“መጀመሪያ ተወልጄ ባደግኩበት ሐረር ውስጥ ነው በታዳጊነት ዕድሜዬ በ2006 እና 2007 ላይ የተጫወትኩት። ከዛም ወደ ኢትዮጵያ ወጣቶች አካዳሚ ገባውና ለሁለት ዓመታት ቆየው። በመቀጠል ደግሞ የመከላከያ u-20 ቡድንን በ2011 ለመቀላቀል ቻልኩና ከሐዋሳ ከተማ ጋር ባደረግነው ጨዋታ ጥሩ መንቀሳቀሴን ተከትሎ በአንድ ጨዋታ በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ አማካኝነት ወደ ዋናው ቡድን የማደግ ዕድሉን አገኘውና ቡድኑ በወረደበት ዓመት ላይ የመሰለፍ እድሉን አላገኘውም ነበር። አምና በነበረን የከፍተኛ ሊግ ቆይታ ደግሞ በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው አማካኝነት ለመከላከያ ዋናው ቡድን በበቂ ሁኔታ የመሰለፍ እድሉን አግኝቼ ከተጫወትኩ በኋላ ዘንድሮ ኢትዮጵያ ቡናን ተቀላቀልኩ”።

ወደ ኢትዮጵያ ቡና እንዴት እንዳመራ

“ኢትዮጵያ ቡናዎች እኔን ወደ ክለባቸው እንድመጣ ማናገርና ፍላጎታቸውን ማሳየት የጀመሩት ባሳለፍነው ዓመት ግማሽ ላይ ነበር። ያኔ እኔ ያደግኩበትን ክለብ መጥቀምና ችሎታዬን ማሳደግ እፈልግ ስለነበር እንደዚሁም ደግሞ ውልም ስለነበረብኝ ይሄ አልተሳካም። በኋላ ላይ ኮቪድ ገብቶም ስለነበር በድጋሚ በክረምቱ ወራት ላይ አናገሩኝና የእኔ ዝውውር በስተመጨረሻም ተሳካ”።

ወደ ኢትዮጵያ ቡና የተዛወርከው እና ከመከላከያ ጋር የተለያየከው በአሰልጣኝ ዩሃንስ ሳህሌ ስላልተፈለግክ ነው?

“እውነታውማ ይሄ አይደለም። አሰልጣኝ ዩሃንስማ እኔን በጣም ይፈልገኛል። ከዛ ውጪም ወደ ቡድኑ ሲመጣ እኔን ጨምሮ ወደ ዋናው ቡድን አምና አድገን በነበርነው አራት ልጆች ላይ ሌሎችንም ጨምሮ ቡድኑን መስራት እንደሚፈልግም ነበር የነገረን። እኔን በተለይ በጣም ያበረታታኝና /አፕርሸትም/ ያደርገኝ ነበር። በጋራ ጥሩ ነገር እንሰራለንም ብሎኝ እና ደሞዜ ተጨምሮልኝ ከቡድኑ ጋር እንድቀጥልም ይፈልግ ነበር። ከእሱ ውጪ ከረዳቱ አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ ጋርም አውርተን እሱም ስለእኔ ጥሩ ነገር ነበረው። ይሄ ሆኖ ሳለ ግን የእኔን እድገት በማይፈልግ እና ቡድኑ ውስጥ ባለ አንድ ሰው ምክንያት ነው መናገር በማልፈልጋቸው ብዙ ጉዳዮች ከክለቡ ጋር ለመለያየትና ቡናንም ለመቀላቀል የቻልኩት”።

ወደ ኢትዮጵያ ቡና ሲገባ እና መለያውን አድርጎ ሲጫወት ስለተሰማው ስሜት

“ለቡድኑ መጫወት እፈልግ ነበር። ይህ እልሜ ከበፊት ጀምሮም አብሮኝ የነበረም ስለሆነ ወደ ቡድኑ ስገባና ማሊያውንም አጥልቄ ስጫወት የተለየ ደስታ ነበር የተሰማኝ”።

ወደ ኢትዮጵያ ቡና በፍጥነት እንዲህ እገባለው ብለህ ጠብቀህ ነበር?

“በፍፁም። ኢትዮጵያ ቡናን ለሚያህል ታላቅ ቡድን በእዚህ ፍጥነት ገብቼ እጫወታለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። ይሄ እድለኛነቴን ነው የሚያሳየው”።

የኢትዮጵያ ቡና ካምፕን ስትቀላቀል ቡድኑን በአንዴ ተላመድክ? አቀባበላቸውስ ምን ይመስል ነበር?

“ወደ ቡድኑ ስመጣ ምርጥ አቀባበል ነበር ያደረጉልኝ። በተለይ ደግሞ አቡበከር ናስርና እያሱ ታምሩ ክለቡን ቶሎ እንድላመድ ያደረጉት ጥረትም ደስ የሚልም ነበርና በአጠቃላይ የቡናን ተጨዋቾች አመሰግናቸዋለሁ”።

በኢትዮጵያ ቡና ቆይታህ ምን ነገሮችን ታልማለህ? የጨዋታ ጅማሬህስ…

“ወደ ቡድኑ በገባሁበት አጭር ጊዜ ውስጥ ከወዲሁ አበረታች የሚባል እንቅስቃሴን ለማሳየት ብችልም ገና ብዙ የሚጠበቅብኝ ተጨዋች ነኝ። በቡና ቆይታዬም ቡድኑን ከእዚህ በላይ አገልግዬና ሻምፒዮና ሆኜም ታሪክ መስራትም እፈልጋለሁ”።

ስለ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ

“እሱን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደተመለከትኩት ከምንም ነገር በላይ አባት ጓደኛ እና ለሁሉም ተጨዋች እኩል አይነት አመለካከት ያለው እና ያመነበትን ነገር በማሰብ የሚሰራ ምርጥ ባለሙያ ነው። ከዛ በተጨማሪ እንደ ሌሎች አሰልጣኞች የመኩራራት ባህሪም አይታይበትምና ይሄን በጣም ወድጄለታው”።

ስለ ኢትዮጵያ ቡና ወቅታዊ አቋም እና ቡድኑ የት ድረስ እንደሚጓዝ

“ጥሩ ላይ ነው ያለነው። ተነሳሽነታችን እና ፍላጎታችንም በጣም የሚገርም ነው። ከሌሎች ቡድኖች አንፃርም ብዙዎቹ የአየር ላይ ኳስን ስለሚጠቀሙ በተጠና እና በተቀናጀ መልኩ የሚጫወት ቡድንን ከእኛ በላይ ያየሁበት ክለብ ስለሌለም የዘንድሮ የሊግ ዋንጫውን ለማንሳት ይከብደናል ብዬ አላስብምና እስከ ፍፃሜው ድረስ ነው የምንጓዘው”።

የእግር ኳስ እድገትህ ፈጣን ነው ማለት እንችላለን?

“አዎን። ከሐረር አንስቶ የእኔ እዚህ ደረጃ ላይ በፍጥነት መድረስ የሚታሰብ አይደለም። ሐረር በነበርኩበት ሰዓት ክለብ ያላገኙ ልጆች ብዙ ናቸው እኔ ግን በእዚህ የወጣትነት እድሜዬ ያውም ቡናን ወደሚያክል ክለብ መግባቴን ሳስብ ፈጣሪዬን አመሰግነዋለሁ”።

በመጨረሻ

“የእግር ኳስ ተጨዋችነት ጅማሪዬ እና ጉዞዮ በሀገር ውስጥ ተጨዋችነት ብቻ ተገድቦ እንዲቆም አልፈልግም። ወደ አውሮፓ ወጥቶ መጫወትን እፈልጋለሁ። ከዛ በፊትም በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ከሚመራው ቡድን ቡናም ጋር ዋንጫን ማንሳት እና ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንም መጫወትን እፈልጋለሁ እና ለዛ ጠንክሬ እሰራለሁ። ከዛ ውጪ መናገር የምፈልገው ለእዚህ ደረጃ እንድበቃ ያደረጉኝን ቤተሰቦቼን የልጅነት አሰልጣኜን እስክንድርን እና እስከዛሬ ብዙ ነገርን ያደረገልኝን አቤል እንዳለን በፈጣሪ ስም ከልብ አመሰግናቸዋለሁ”።

Hatricksport website editor

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Hatricksport website editor