“በቅዱስ ጊዮርጊስ የድል እንጂ የሽንፈት ባህል አልተለመደም፤ ከክለቡ ጋር የማፅፋቸው ብዙ ታሪኮች ይኖሩኛል” ሀይደር ሸረፋ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

የቅ/ጊዮርጊሱ የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ሀይደር ሸረፋ ቡድናቸው ወደሚታወቅበት ውጤታማነቱ ተመልሶ በአጭር ጊዜ
ውስጥ የቀድሞ ስምና ዝናውን እንደሚረከብ እርግጠኝነቱን ለሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ ገልጿል፡፡
ቅ/ጊዮርጊስን ከመቀላቀሉ በፊት ለደደቢት፣ ለጅማ አባቡና እና ለመቐለ 70 እንደርታ ቡድኖች በፕሪምየር ሊግ ደረጃ
ተጫውቶ ያሳለፈው ስኬታማው እና ጠንካራው የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ሀይደር በሜዳ ላይ የኳስ ብቃቱ ብዙዎች
የሚያደንቁት ሲሆን በሊጉ ቆይታውም ጥሩ መንቀሳቀሱን ተከትሎ ለኢትዮጵያ ኦሎምፒክና የዋናው ቡድንም
በመመረጥ እስከመጫወት ደረጃ ላይም ደርሷል፤ ሀይደር በሊጉ ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ጥሩ ቆይታን በማድረግ

ዋንጫን ያነሳ ሲሆን በቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ተጨዋችነቱም ይህን ዋንጫ ጨምሮ በርካታ ተደራራቢ ድሎችንም ለመጎናፀፍ
የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግም እየተናገረ ይገኛል፡፡ ሀይደር ይህን አስመልክቶም “ለእኔ አሁን ላይ ከፍተኛ ስጋት
የሆነብኝ ኮሮና ነው፤ ይህ ወረርሽኝ ከአገራችን ይጥፋ እንጂ በዘንድሮ የውድድር ዘመን የሊጉ ውድድር ሲጀመር ለክለቡ
በቋሚ ተሰላፊነት በመጫወት ቡድኑን በጣም ለመጥቀም እና ከጓደኞቼም ጋር በመሆን ክለቡን ለተደራራቢ ድል
ለማብቃትም መዘጋጀቱን አክሎ ገልፆልናል፡፡
ቅ/ጊዮርጊስ ለዘንድሮው የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው እስካሁን አዲስ ግደይን ከሲዳማ ቡና እንደዚሁም ደግሞ ከነዓን
ማርክነህን ከአዳማ ከተማ ያስፈረመ ሲሆን የተጨዋቾቹ ወደ ቡድኑ መምጣት መቻልም ክለቡን ብቻ ሳይሆን እኛን
ነባር ተጨዋቾችንም ይበልጥ ያጠናክረናል ሲልም ተደምጧል፤ ከቅ/ጊዮርጊሱ ሀይደር ሸረፋ ጋር የሀትሪክ ስፖርት
ጋዜጣ አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ቆይታን አድርጎ ተጨዋቹ ምላሾቹን ሰጥቷል፤
ተከታተሉት፡፡

ሀትሪክ፡- ቅ/ጊዮርጊስን ባሳለፍነው ዓመት ተቀላቅለህ ለመጫወት ችለሃል፤ በክለቡ ውስጥ የነበረህን ቆይታህ ከዚህ
ቀደም ከተጫወትክባቸው ቡድኖችህ አንፃር እንዴት ተመለከትከው?

ሀይደር፡- ቅ/ጊዮርጊስን ማንም እንደሚያውቀው የትልቅ ታሪኮች ባለቤት ቡድንና በውጤታማነቱም የሚታወቅ ክለብ
ከመሆኑ አንፃር ለእዚህ ቡድን መጫወት መቻል ከሌላ ቡድኖች አኳያ ሲመዘን ሁሌም ጫናዎች /ቻሌንጆች/ አሉት፤
ምክንያቱም ይሄ ቡድን በበርካታዎች የሚደገፍና ሁሌም ደግሞ ውጤት እንድታመጣበትም የሚጠበቅብህ ክለብ ነውና
ወደዚህ ቡድን ገብቼ መጫወት ስጀምር በጊዜ ሂደት ክለቡን እየተላመድኩ መጥቼ ነበር ያም ሆኖ ግን ኮቪድ ወደ
አገራችን በመግባቱ የተነሳና የሊጉ ውድድርም በመሰረዙ ስለ ሙሉ ዓመት የቡድኑ ቆይታዬ ብዙም የምለው ነገር
አይኖረኝም፡፡

ሀትሪክ፡- ለቅ/ጊዮርጊስ በፕሪምየር ሊጉ እየሰጠክ የነበረውን ግልጋሎት ኮቪድ ውድድሩን ባያቋርጥ ኖሮ የተዋጣለት
ይሆን ነበር?

ሀይደር፡- ብዬ አስባለሁ፤ ያም ሆኖ ግን በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የሀገራችን የሊግ ውድድር ስለተቋረጠና ለክለቡ
መጫወትም የቻልኩት ለግማሽ ሲዝንም ስለነበርና ገና ቡድኑንም እየተላመድኩትም ስለነበር የእኔን አቅምና ለቡድኑ
የሰጠሁትን ግልጋሎት ለመለካት የሚቻልበት ሁኔታ ፈፅሞ የለም፡፡

ሀትሪክ፡- ቅ/ጊዮርጊስን ከእዚህ በኋላስ በምን መልኩ ልትጠቅመው ዝግጁ ሆነሃል?

ሀይደር፡- በብዙ መልኩ ምክንያቱም ይሄ ቡድን የሀገሪቱ ትልቁ ቡድን ነውና ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ስታወራ መጀመሪያ
የምትናገረው ስለዚህ ታሪካዊና ውጤታማ ቡድን ነው፤ ይሄ ክለብ በርካታ ደጋፊዎች ያሉት ስለሆነም ቡድኑን ውጤታማ
ለማድረግም አቅሜን ሳልሰስትም እጫወትለታለሁ፤ ከዛ ውጪ እኔ ወደዚህ ቡድን የመጣሁበት አንዱ ምክንያትም
ክለቡን ከበፊት አንስቶ አደንቀውና ገብቼም ልጫወትበት የምፈልገው ቡድን በመሆኑ ከእዚህ ማሸነፍን እንጂ መሸነፍን
ፈፅሞ ከማይወድ ቡድን ጋር ላስፅፋቸው የምፈልጋቸው ብዙ ታሪኮች አሉና እነዚህን እልሞቼን ለማሳካት ከፍተኛ
ጥረቶችን እያደረግኩኝ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ ግደይን እንደዚሁም ደግሞ ከነዓን ማርክነህን ሊያስፈርም ችሏል፤ ይህን ስታውቅ ምን
አልክ?

 

ሀይደር፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ጥሩ ጥሩ ችሎታ ያላቸውን
ተጨዋቾችን ለማስፈረም መቻሉ ጥቅሙ ለሁላችንም ነው፤ በተለይ ደግሞ የእነዚህ አብሬያቸው በብሔራዊ ቡድን
ደረጃም የተጫወትኳቸው ልጆች መምጣት መቻላቸው ቡድኑ የለመደውን ውጤትም እንዲያስጠብቅለትም ያደርገዋል፤
ከዛ ውጪም በቡድኑ ውስጥ የምንገኘውን ነባር ተጨዋቾችም ከእዚህ በፊት ከነበረን አቋም አንፃርም ይበልጥ
እንድንጠናከርም ያደርጉናልና የተጨዋቾቹ ወደ ክለባችን መምጣትን እኔም ሆንኩ ሌሎቹ የቡድናችን ተጨዋቾች
በመልካም ዜና ነው ልንቀበለው የቻልነው፡፡

ሀትሪክ፡- አዳዲስ ተጨዋቾች ብዙ ጊዜ ሲፈርሙ ነባር ተጨዋቾች ተሰልፎ ከመጫወት እና ካለመጫወት ጋር ተያይዞ
ስጋት ውስጥ የሚወድቁበት ሁኔታ አለ፤ አንተስ ላይ ይሄ ስጋት ተፈጥሯል?

ሀይደር፡- በፍፁም፤ የእነሱ መምጣት እኔን ስጋት ውስጥ አይከተኝም፤ እኔን አሁን ላይ የሚያሰጋኝ ነገር ቢኖር ኮሮና
ብቻ ነው፤ የተጨዋቾቹ መምጣትማ ከላይም እንደገለፅኩት ቡድናችንንም ሆነ እኛን ተጨዋቾች በጣም ይጠቅማልና
ይሄን ብቻ ነው ለማለት የምፈልገው፡፡

ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ዋንጫ ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ካቻምና አንስተሃል? ይሄ ድል ለአንተ በቂህ
ነው?
ሀይደር፡- አይደለም፤ ምክንያቱም በርካታ የሊጉ ዋንጫዎችን አሁን ከምጫወትበት ክለቤ ቅ/ጊዮርጊስ ጋርም
በተደጋጋሚ ጊዜ በቀጣይነት አነሳለውና ያኔም እነዚህን ድሎች ሳሳካ በቂዬ ነው ብዬ ልናገር እችላለው፡፡

ሀትሪክ፡- ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር የመጀመሪያ የሊግ ዋንጫህን ካቻምና ማንሳት ችለሃል፤ የተለየ ደስታ ነበር
የተፈጠረብህ?

ሀይደር፡- አዎን፤ ምክንያቱም የእግር ኳስ ተጨዋች ስትሆን የመጀመሪያ ዓላማ ሊሆን የሚገባው ከምትጫወትበት
ክለብ ጋር ትልቁን ዋንጫ ማንሳት መቻል ነው፤ ይሄን ዋንጫ አገኘ ማለት ደግሞ ለቤተሰቦችህ እና ለአድናቂዎችህ
የምትናገረው ታሪክም ይኖርሃልና ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ያገኘሁት ዋንጫ ወደ ትልቁ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስም
እንድገባና በኳስ ህይወቴም ወደ ተሻለ ደረጃም እንድንደረደርም ምክንያት የሆነኝ ስለሆነ ትልቁ ደስታዬ ነው፤
በቀጣይነትም ከቅ/ጊዮርጊስ ቡድን ጋር ውጤት የማገኝባቸው ጊዜያቶች ስለሚኖሩ ሌሎች የደስታ ጊዜያቶች ይኖሩኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ገብተህ መጫወት ከጀመርክበት ጊዜ አንስቶ ያጋጠመህ ለየት ያለ ነገር አለ?

ሀይደር፡- ከሌሎች ቡድኖች አኳያ ከሆነ አዎን፤ ይሄ ቡድን ሁሌም ልታወራለት የምትችለው ብዙ ታሪክ አለው፤ የበርካታ
ደጋፊዎች ባለቤት ቡድን ነው፤ ትላልቅ የሚባሉ ተጨዋቾችም ያለፉበት ነው፤ ከዛ ውጪም ስለ ቡድኑ ትልቅነት እና
ውጤታማነትም የአደባባይም ታሪክ ነውና ይሄንን በቡድኑ ቆይታዬ ላውቅ ችያለው፡፡

ሀትሪክ፡- ቅ/ጊዮርጊስ የሊግ ዋንጫን ካጣ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል፤ በኮቪድ የተቋረጠው የዓምናው የውድድር
ዓመት ሲጨመር ደግሞ ወደ ሶስተኛ ዓመት እየመጣ ነውና ይሄ መሆን መቻሉ በቡድኑ ውስጥ ምን ነገርን ፈጥሯል?

ሀይደር፡- ቅ/ጊዮርጊስ ብዙ ዋንጫዎችን የለመደ እና ማሸነፍንም ባህሉ ያደረገ ክለብ ከመሆኑ አኳያ ባለፉት
ዓመታቶች እነዚህን የለመዳቸውን ክብሮች ሲያጣ በቡድኑ ውስጥ ከፍተኛ ቁጭትን ነው የፈጠረው፤ ይሄን ቁጭት
ለማጥፋት ዓምና ጥሩ ቡድንን ገንብተን ለመወዳደር ብንችልም ኮቪድ በመግባቱ የተነሳ የሊግ ውድድሩ ሊቋረጥ ችሏል፡፡

ሀትሪክ፡- ቅ/ጊዮርጊስ በኮቪድ ውድድሩ ባይቋረጥ ኖሮ ዋንጫውን ያነሳ ነበር?

ሀይደር፡- የሊጉ ፉክክር ቀላል የሚባል አልነበረም፤ 14 ያህል ጨዋታዎችም ነበር የሚቀሩትና እንደ እግር ኳስ አሁን
ላይ ዋንጫውን እናነሳ ነበር ብሎ ለመናገር በጣም ይከብዳል፤ ከዛ ይልቅ ግን ቡድናችን የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት
የሚያስችል አቅም ነበረው ብል ብቻ ለእኔ በቂዬ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- አዲሱን 2013 ዓ/ምን እንዴት ነበር የተቀበልከው?

ሀይደር፡- እንደ አዲስ ዓመት መልካም የሆኑ ነገሮችን በመመኘት ነው የተቀበልኩት፤ ምክንያቱም አገራችን በኮቪድም
ሆነ በፖለቲካው ያለችበት ሁኔታ የሚያሳስብ ነውና፤ ስለዚህም ይህን አውቄ ወረርሽኙ እንዲጠፋና በፖለቲካውም ሰላም
የምንሆንበትን ነገር ልመኝ ችያለው፡፡

ሀትሪክ፡- 2012ስ እንዴት አለፈ?

ሀይደር፡- ለእኛ ለኢትዮጵያኖች ጥሩ ጊዜ አልነበረም፤ በተለይ ደግሞ የኮቪድ ወደ አገራችን መግባት እግር ኳሱ ላይ ብዙ
ነገሮችን ሊያበላሽም ችሏልና ከበሽታውም ሆነ ከሌላው ጉዳይ ጋር በተያያዘ ጥሩ ወቅትን አላሳለፍንም፡፡

ሀትሪክ፡- ከእግር ኳስ ከራቅህ በርካታ ወራቶችን አስቆጥረሃል፤ ኪሎ ጨመርክ?

ሀይደር፡- በፍፁም፤ ምክንያቱም ልምምዴን በአግባቡ እየሰራው እና አመጋገቤንም እያስተካከልኩ እየተጓዝኩ ስለሆነ፡፡

ሀትሪክ፡- ከኮቪድ መግባት በኋላ ማግኘት ፈልገህ ልታገኘው የናፈቀህ ነገር?

ሀይደር፡- ኳሷን ነዋ!

ሀትሪክ፡- ከተቃራኒ ቡድን ተጨዋቾች ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚያስቸግርህ?

ሀይደር፡- የኢትዮጵያ ቡናው ታፈሰ ሰለሞን እሱን በተለያዩ ቡድኖች ውስጥ ሳለ ተቃራኒ ሆኜ ገጥሜዋለው፤ በጣም
የማደንቀውም ተጨዋች ነው፤ በብሔራዊ ቡድን ውስጥም አብረንም ነው ያለነውና ይሄ ጎበዝ ተጨዋች ለእኔ
አስቸጋሪው ተጨዋች ነው፡፡

ሀትሪክ፡- በተቃራኒነት ከምትፋለማቸው ቡድኖች ውስጥ ከማን ጋር ስትጫወቱ ግጥሚያው ይቀልሃል?

ሀይደር፡- ሁልጊዜ ወደ ሜዳ ስገባ ለሁሉም ቡድኖች እኩል ግምትን ነው የምሰጠውና በጨዋታ ዘመኔ ይሄ ቡድን ጋር
ስጫወት ይቀለኛል፤ ከዚህ ቡድን ጋር ስጫወት ይከብደኛል ያልኩበት ጊዜ የለም፡፡

ሀትሪክ፡- የእግር ኳስ ጅማሬህ ከፕሮጀክት የተነሳ ነው፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ በሆነው አቶ

ዮሴፍ ተስፋዬ ተቋቁሞ የነበረውን የቢኒ ትሬዲንግ የልጅነት ቡድንህንም በተደጋጋሚ ጊዜ ታነሳለህ፤ በዛ ዙሪያ አንድ
ነገር ብትል?

ሀይደር፡- የእውነት ነው ቢኒ ትሬዲንግን በተደጋጋሚ ጊዜ የማነሳው ያለ ምክንያት አይደለም፤ ይሄ የልጅነቴ ቡድን እግር
ኳስ ወዳድ በሆኑት አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ አማካኝነት በተቋቋመ ሰዓት ለእኛ ታዳጊ ለነበርነው እግር ኳስ ተጨዋቾች የተሻለ
ደረጃ ላይ እንድንደርስ ጥሩ አማራጭ ሆኖልን ነበርና እዛ ከ10ም ከ13ም ዓመት በታች ላሉት ቡድኖች ስንጫወት
በአሰልጣኝ አፈወርቅ ጉርሙ አማካኝነት ለውጥን ማምጣት ችለን ነበር፤ የፕሮጀክቱ ባለቤትም አቶ ዮሴፍ ኳስ የሚችሉ
ልጆችንም በጣም ይወዱ ስለነበርም ብዙ ነገርን ያደርጉልን ነበርና በእዚህ እንደ ቤተሰቤ በማየው ክለብ ውስጥ
ተጫውቼ በማለፌ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ አቶ ዮሴፍ ላደረጉልን ነገርም ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- በመጨረሻ?

ሀይደር፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነቴ ልጫወት ከምመኛቸው ቡድኖች ውስጥ ለቅዱስ ጊዮርጊስና ለብሔራዊ ቡድን
ልጫወት ችያለሁ፤ የቀጣዩ ጊዜ ምኞቴ ደግሞ እንደ እነ ሽመልስ በቀለ፣ ቢኒያም በላይ፣ ዑመድ ሁኩሪና ጋቶች ፓኖም
ወደ ውጪ ወጥቼም መጫወትን እፈልጋለውና ያን ማሳካት ነው የምፈልገው፤ ከዛ ውጪም በኳሱ አሁን ላይ ገና ብዙ
የሚቀረኝ ተጨዋች ብሆንም እስካሁን ለመጣሁበት መንገድ ግን ከፈጣሪ ቀጥሎ ከልጅነቴ አንስቶ ያሰለጠኑኝን
አሰልጣኞች እና ቤተሰቦቼን እንደዚሁም ደግሞ የሰፈሬ አማኑኤል ልጆችንና ጓደኞቼን ማመስገን እፈልጋለውኝ፡፡

 

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website