“ለቅ/ጊዮርጊስ የድል ጎሎችን ማስቆጠር ልጀምር እንጂ ገና በምርጥ ብቃቴ ላይ አይደለውም” ጌታነህ ከበደ

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና ቅ/ጊዮርጊስ ሰበታ ከተማን የቡድኑ ካፒቴን ጌታነህ ከበደ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች እና በሌሎቹ የቡድን አጋሮቹ አቤል ያለው እና ወደ ሜዳ ተቀይሮ በገባው ጋዲሳ መብራቴ ግቦች 4-2 በሆነ ውጤት አሸንፎ በመሪነት ላይ ተቀምጧል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ድል ባደረገበት የዛሬው ጨዋታ እና የቡድናቸውን አቋም አስመልክቶ ለክለቡ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው ጌታነህ ከበደ ከጨዋታው በኋላ ከሀትሪክ ስፖርት ድረ ገፅ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ቅ/ጊዮርጊስ ሰበታ ከተማን ድል ስላደረገበት ጨዋታ

“ጨዋታው ጥሩ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ እነሱ ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት ሞክረዋል፤ እኛ ያሸነፍነው ይሄ ቡድን በጣም ጠንካራ እና በጥሩ አሰልጣኝ የሚመራም ነው። ከዛም ውጪ ወጣት እና ልምድ ያላቸው ተጨዋቾችም ተጣምረው የሚጫወቱበትም ክለብ ነውና ከእዚህ አኳያ በዛሬው ጨዋታ እነሱን በሰፊ ግብ ማሸነፋችን የኛን ጥንካሬ ያሳየም ሆኗል”።

ለክለቡ የድል ግቦችን ማስቆጠሩ

“ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ስኬታማነት እያመራ ባለበት ጨዋታ ለክለቤ የድል ግቦችን ማስቆጠር መቻሌ በጣም ነው ያስደሰተኝ። አንድ አጥቂም ግብ ማስቆጠር ከጀመረም የራስ መተማመን ብቃቱም በዛው ስለሚጨምር የእኔም እንደዛ ነው እየሆነ ያለውና ይሄ ግብ ማስቆጠሬ ወደፊትም የሚቀጥል ነው የሚሆነው”።

በፍፁም ቅጣት ምት ግቦችን ስለማስቆጠር ብቃቱና ከዚህ በፊት የሳተባቸው አጋጣሚዎች ካሉ

“ለቅ/ጊዮርጊስ የፍፁም ቅጣት ምቶችን በተደጋጋሚ እየመታው ያለሁት የቡድኑ አንደኛ መቺ ስለሆንኩ ነው። በእዚህም ጥሩ ብቃት እንዳለኝ አምናለው። በመሳት ደረጃ ደግሞ ከእዚህ በፊት ያጋጠመኝ አንዴ ለደደቢት በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ጨዋታ ከሱዳኑ አልአህሊ ሼንዲ ጋር ስንጫወት የሳትኩት እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆኜ ደግሞ ከጉዳት አገግሜ እንደመጣው ከስዑል ሽረ ጋር ስንጫወት የሳትኩት ነው”።

አቤል ያለው አንተ ሶስተኛ ግብ እንድታስቆጥር አድርጎ ስለነበረው ጥረት

“አቤል ባይሳካለትም ራሱ ማስቆጠር የሚችለውን ኳስ ነው እኔ ሀትሪክ እንድሰራ ከመፈለጉ አኳያ ሊያቀብለኝ ብሎ ኳሷ ልትበላሽበት የቻለችው”።


ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁን ላይ ስላለው ወቅታዊ አቋም

“የልምምድ ሜዳው ላይ ከምንሰራው አኳያ ገና ወደ ምርጡ ብቃታችን አልመጣንም። ይቀረናልም። መቶ ፐርሰንት ወደ አቋማችን ስንመጣ ግን አስፈሪው ቡድናችን ይታያል”።

እሱን ጨምሮ በርካታ ቢጫ ካርድ ስለማየታቸው

“እኔ ያየሁት ካርድ አሰልጣኜ ጠርቶ ሲመክረኝ ነው። አዲስ በወጣ ህግም ሊሆን ይችላል ካርዱን የተመለከትኩት። ከዛ በተረፈ የቡድናችን ብዙዎቹ ተጨዋቾች አንዳንዴ በእዚህ መልኩ ኳስ ከሚጫወት ቡድን ጋር ቻሌንጅ አድርገህ ካልተጫወትክ ልትቸገር ትችላለህ እና በኳስ በሚያጋጥም ሁኔታ ነው በእርግጥ የማያሰጥ ቢጫ ካርድም ቢኖር ተጨዋቾቻችን ሊመለከቱ የቻሉት”።

በምርጥ ብቃትህ ላይ ነው የምትገኘው

“ለቅዱስ ጊዮርጊስ የድል ግቦችን ማስቆጠር ልጀምር እንጂ ገና በምርጥ ብቃቴ ላይ አይደለሁም፤ ገና ይቀረኛል”።

Hatricksport website editor

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Hatricksport website editor