በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 14ተኛ ሳምንት መርሃ ግብር እሁድ ሰኞና ማክሰኞ ሲቀጥል የእሁዱ 9 ሰዓት የፋሲል ከነማና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ትኩረት ስቧል፤ ቡድኖቹ ለዋንጫው በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው በተባለው ግጥሚያ የአጥቂዎቹ ሙጂብ ቃሲምና ጌታነህ ከበደ ፍልሚያም ተጠባቂ ነው፡፡ የሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ በእሁዱ ጨዋታ ዙሪያ ከቅዱስ ጊዮርጊሱ አምበል ጌታነህ ከበደ /ሰበሮም/ እና ከፋሲል ከነማው በረከት ደስታ ጋር ባደረገው ቆይታ ሁለቱም እንደሚያሸፉ ርግጠኝነት በተሞላበት ሂደት ፎክረዋል፡፡ ሁለቱም ተጨዋቾች በነገው ወሳኝ ጨዋታ ዙሪያ ለሀትሪክ የሰጡት ምላሽ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2 ጨዋታ 8 ግብ አስቆጥሯል ወደ ውጤታማነቱ ተመልሷል ማለት ይቻላል?
ጌታነህ፡-ማለት ይቻላል…ነገር ግን ሁለት ጨዋታ አሸንፈን 8 አስቆጥረን 5 ግብ ተቆጥሮብናል ይሄ ደግሞ ድክመታችንንም ያሳያልና ገና መስተካከል አለብን… እንደ መነሻ ግን ጥሩ ነን ማለት ይቻላል፡፡
ሀትሪክ፡- ጌታነህ ከበደ /ሰበሮም/ኮከብ ግብ አግቢነት ላይ አለሁበት እያለ ነው?
ጌታነህ፡-/ሳቅ/ አዎ እንደሚታየው ነው ማለት ይቻላል፤ ስለ ኮከብ ግብ አግቢነቴ ብቻ ሳይሆን ዋነኛ ሃሳቤ ስለ ዋንጫው ነው በዚህ ሰዓት ስለኮከብነቴ ስለግብ ስኬቴ ማሰብ አልሻም ቅድሚያ ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዴት የዋንጫ ባለቤት እናደርጋለን የሚለው ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ኮከብ ግብ አግቢ ሆነህ ከጨረስክምኮ ቡድንህ የዋንጫ ባለድል መሆኑ አይቀርም… በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ…ይሄን አላየኸውም?
ጌታነህ፡- /ሳቅ/ እርሱ ልክ ነው… የኔ ማስቆጠር ብቻ ሣይሆን ግን በተሻለ ስፍራ ላይ ላለው ማቀበል ይጠበቅብኛል፡፡ ከጌታነህ ድል ይልቅ የቡድኑ ውጤት ይቀድማል፡፡ ስለኮከብነቱ ብቻ አስቤ ወደ ሜዳ ከገባሁ አስቸጋሪ ነው አንድ ቡድን ደግሞ በአንድ ሰው ላይ ብቻ መንጠልጠል የለበትም፤ በተለያዩ ክለቦች ላይ ይህን እያየን በመሆኑ በግሌ ስለቡድን ድል እንጂ ስለግል ኮከብነቴ አልጨነቅም፡፡

ሀትሪክ፡- ከክለቡ ቦርድ ጋር የተደረገው ውይይት የለወጡ ምክንያት ነው ማለት ይቻላል?
ጌታነህ፡-ሊሆን ይችላል… ቦርዱ ትንሽ ችግር ሲመጣ ወዲያውኑ ነው የሚሰበስበን… ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት የአቅም ችግር የለም የሚጠበቅበትን ያህል አቅሙን አውጥቶ የመጠቀም ችግር ነው ያለው… ክለቡ ምርጥ ነው እንደእኔ በቅዱስ ጊዮርጊስ የአቅም ችግር ሳይሆን ያለው አቅምን አውጥቶ የመጠቀም ችግር ነው ይሄ ደግሞ የሚስተካከል ይሆናል፡፡
ሀትሪክ፡- ውድድሩ በዝግ መካሄዱና ደጋፊዎቻችሁ አለመኖራቸው እንዲናፍቋችሁ አላደረገም?
ጌታነህ፡-ደጋፊው ይናፍቃል እነርሱ ባይኖሩም ግን በዲ.ኤስ ቲቪ ያለው ድባብ ደስ የሚል ነው፡፡ ደጋፊዎቻችን ባለመኖራቸው ቅር ቢለንም በዲ.ኤስ ቲቪው ተክሰናል ደጋፊው ቢኖር ግን በይበልጥ ደስ ይል ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- ከአሰልጣኙ ጋር ያላችሁ ግንኙነት ጥሩ ነው ማለት ይቻላል?
ጌታነህ፡- /ሳቅ/ ከአሰልጣኙ ጋር ጥሩ አይደሉም የሚለው መረጃ ልክ አይደለም…ከአሠልጣኙ ጋር ያለን ግንኙነት መልካም ነው በጋራ ለክለቡ ድል እየሰራን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ከአሰልጣኙ ወሰድኩ ጨመረልኝ የምትለው ነገር አለ?
ጌታነህ፡- /ሳቅ/ ሲጀመር አካባቢ ከአሰልጣኙ ጋር ልዩነት ተፈጥሮ ነበር በመልሶ ማጥቃት እንድንጫወት የተደረግንበት ሁኔታ አልተመቸንም አሁን ግን ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው አሁን ከኳስ ጋር ጥሩ እየተንቀሳቀስን ነው… በበፊቱ አካሄድ ግን አልስማማም ነበር በጨዋታ ሂደት ረጅም ኳስ መጫወት ይቻል ይሆናል እንጂ ቋሚ አካሄድ መሆኑ ግን አልተመቸኝም ነበር… አሁን ግን እኛ በምንፈልገው መንገድ መጫወት ጀምረናል በዚህም ደስ ብሎኛል ሜዳው አሪፍ መሆኑን ተከትሎ በሁለት ጨዋታዎች የታየውም እውነት ይሄው ነው እንደ አሰልጣኝ ቡድኑን እንድመራ ሙሉ ኃላፊነት ሰጥቶኛል በዚህም ደስተኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ከፋሲል ከነማ ጋር ያላችሁ ጨዋታ ወሳኝ ነው… ምን ውጤት እንጠቅብቅ?
ጌታነህ፡- ፋሲል ከነማ ከሰበታ ከተማ ጋር ተጫውተው ነጥብ መጣላቸው ፉክክሩን ጥሩ አድርጎታል… ሰበታን አሸንፈው ቢሆን ኖሮ እሁድ የሚጫወቱት ለአቻ ውጤት የተለየ አድቫንቴጅ ይዘው ይገቡ ነበር ነጥብ መጣቸው ግን ፉክክሩን ክፍት አድርጎታል ብዬ አምናለሁ ውጤቱን እሁድ እለት እናየዋለን ብዬ አስባለሁ /ሳቅ በሳቅ/
ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ የዋንጫ ህልሙን ለማሳካት ይሄ ጨዋታ ወሳኝ ይመስልሃል?
ጌታነህ፡- ገና የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች አሉን እነኛንም ጨዋታዎች ማሸነፍ ይኖርብናል ይሄ ጨዋታ ሞራል ከመገንባት አንፃር ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ በግሌ ደግሞ መቼም ቢሆን ወደ ሜዳ ስገባ ግብ አስቆጥራለሁ የሚል አቋም ይዤ ነው ያም ቢሆን ታዲያ ቅድሚያ የምሰጠው ለቡድኔ ነው… እናም ግብ የማስቆጠር ፍላጎቱ አለኝ ደግሞ እንደማደርገው ርግጠኛ ነኝ፡፡ በነገራችን ላይ ለፋሲል ከነማ የተለየ ስሜት አይኖረኝም ሁሉም ክለቦች ላይ በማስቆጥራቸው ግቦች ደስተኛ ነኝ ልዩነትም አልፈጥርም ያም ሆኖ ፋሲል ከነማ ላይ በርግጠኝነት አስቆጥራለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ዋንጫው የቅዱስ ጊዮርጊስ ነው ማለት ይቻላል ልብህ የሚነግርህ ይህን ነው?
ጌታነህ፡-/ሳቅ/ አዎ የሚነግርኝ እውነት ይህ ነው ገና ማሸነፍ ስንጀምር ይኸው ጀመሩ እንግዲህ ተባለ አንድ ታሪክ ልንገርህ ደደቢት እያለሁ ቅዱስ ጊዮርጊስን በ10 ነጥብ ልዩነት እየመራን አንድ ሁለት ጨዋታዎችን ሲያሽንፍ መጣ እንግዲህ ይባል ነበር አሁንም የሚባለው መጣ እንግዲህ እየተባለ ነው /ሳቅ በሳቅ/ ከደደቢት ጋር ዋንጫ እንዳነሳሁ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋርም በአምበልነቴ ዋንጫ እንደማነሳ ርግጠኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- እሁድ የሚኖረው ጨዋታ የዋንጫ አሸናፊውን ያሳያል?
ጌታነህ፡- ገና ነው ለእሱ ገና በርካታ ጨዋታዎች ይቀራሉ ግን ይሄ ጨዋታ ወሳኝ መሆኑን አውቃለሁ እኛ ፋሲልን ካሸነፍን እነርሱ ላይ የሚደርስ የሞራል ውድቀት ይኖራል ይሄ ደግሞ ለዋንጫ ጉዟችን ወሳኝነት አለው ያም ቢሆን ዋንጫውን ማንሣታችንን እስክናረጋገጥ ድረስ ተጋጣሚዎቻችንን ማሸነፍ አለብን፡፡ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ የማንሣት ጉዟችንን ፋሲል ከነማን በመርታት እናስቀጥላለን፡፡
ሀትሪክ፡- የሊጉ ፉክክርን እንዴት አገኘኸው? ቀነሰ ወይስ በጣም ጨምሯል?
ጌታነህ፡- አዎ ፉክክሩ እንዲህ ይጠናከራል ብዬ አላሰብኩም ነበር ግን ያለው ፉክክር የሊጉን መርሃ ግብር አድምቆታል ደስ የሚል የውድድር ጊዜ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በርካታ ግቦች እየተቆጠሩ ነው… የአጥቂዎቹ ጥንካሬ፣ የተከላካዮቹ ድክመት ወይስ የዲ.ኤስ.ቲቪ መምጣት….?
ጌታነህ፡- ሶስቱም አይደለም… የዲ.ኤስ.ቲቪ መምጣትም አይደለም የአጥቂዎች ድክመትና የተከለካዮች ጥንካሬ ጋርም አይያያዝም ተዟዙሮ መጫወቱ መቆሙና በአንድ ቦታ ውድድሩ መካሄዱ ያመጣው ውጤት ነው፤ ደጋፊ አለመኖሩም ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፤ ክልል ላይ ሲዳማ፣ አርባምንጭ ወይም ወላይታ ድቻ ሜዳ ሄዶ ግብ ማስቆጠርኮ ይከብል፡፡ ከበረታህ 0ለ0 አለበለዚያ 1ለ0 ተሸንፈን ነው የምንመጣው… 16 ቡድን ካለ 15 ጨዋታ ከሜዳህ ውጪ 15ቱ ደግሞ በሜዳህ የምታደርገው ነው ከሜዳው ውጪ ባሉት 15 ጨዋታዎች አንድም ግብ ላታስቆጥር ትችላለህ አዲስ አበባ ብቻ ነው የምታገባው የደጋፊውና የዳኞቹ ተፅዕኖ ከባድ ነበር አስቸጋሪ ጊዜ ይገጥማል የሜዳው አለመመቸትም ሳይዘነጋ ነው፤.. የደጋፊ አለመኖርም የዳኞች ተፅዕኖ መቅረቱ፣ የተመረጡ ሜዳዎች አሪፍ መሆናቸው ብዙ ግብ እንዲቆጠር አድርጓል ባይ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ወልቂጤዎች 3ኛ ግብ አሲያስቆጥሩ የተበሳጨውን የጌታነህ ፊት በዲ.ኤስ.ቲቪ እያየን ነበር.. ስሜት ይጎዳል አይደል?
ጌታነህ፡- ግብ ሲቆጠር በራሱ ያበሳጫል ነገር ግን 4ለ1 እየመራህ ሁለት ግቦች ሲቆጠሩ ንዴትህ ይጨምራል…ግቦች ይጠቅማሉ እኛና ኢትዮጵያ ቡና በነጥብ እኩል ሆነን ኢትዮጵያ ቡና የሚበልጠን በሶስት ግብ ነው፡፡ የግብ ክፍያ ምን ያህል ጥቅም እንዳለው እያየን ግቦቹ ሲገቡ ያናድዳል ለዚያ ነው የተበሳጨሁት፡፡
ሀትሪክ፡- በረኛው ለአለም ላይ የሚደርሰው የማህበራዊ ድረ ገፅ ተቃውሞ ትንሽ መስመር ያለፈ ይመስላል… እንደ አምበልነትህ ለደጋፊዎቹ የምትለው ነገር አለ?
ጌታነህ፡- ሁሉንም ደጋፊዎች አይወክልም ሁሉም ደጋፊ አንድ አይነትም አይደለም እንደ ቡድን ቅዱስ ጊዮርጊስ ውጤታማ ሲሆን ብቻ ሣይሆን ደከም ብሎም ውጤት ሲጠፋ ደጋፊው ከጎናችን ሊሆን ይገባል የሚያበረታቱን ሲሆን ነው ውጤት የሚገኘውና ደጋፊው በሙሉ ከጎናችን ሆኖ ድጋፉን እንዲሰጠን እጠይቃለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- የኮከብ ግብ አግቢነት ሪከርዱን በ25 ግብ የያዝከው አንተ ነህ…ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ አቡበከር ናስር ይሰብረዋል ብለህ ታስባለህ?
ጌታነህ፡-አዎ ባለው ሁኔታ ሊሰብረው ይችላል ብዬ እገምታለሁ ሜዳውም አመቺ ነው ሁለተኛው ዙር እየጠነከረ እንደሚሄድ እገምታለሁ ያም ሆኖ ግን አሁን ካገባቸው ግቦች አንፃር ሪከርዱን ይሰብረዋል የሚል ግምት አሳድሬያለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- አቡበከር ናስር ላይ እደርሳለሁ ብለህ አታስብም?
ጌታነህ፡-እደርሳለሁ እንጂ… ለምን አልደርስም? አሪፍ አቋም ላይ ነው ያለሁት በባህርዳር ጨዋታዎች ላይ ግቦችን እያስቆጠርኩ ነው የማልደርስበት ምክንያት የለም አቡበከር ላይ እደርሳለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- የአንተ የአቡበከርና የሙጂብ ፍልሚያ ለዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የቋሚ ተሰላፊነት ምርጫ ፈተና አይሆንም?
ጌታነህ፡- አይሆንም… የታየውም ፈተና አለመሆኑ ነው… በክለብ ጨዋታ ጥሩ ነህ ማለት ለብሔራዊ ቡድን የግድ ትመረጣለህ ማለት አይደለም፡፡ በኔ እምነት አሰልጣኙ ይቸገራል ብዬ አልሰጋም አሁን አማኑኤል ገ/ሚካኤልን ተመልከት ከክለብ ይልቅ ቀዳሚ ተመራጭነቱ ለብሔራዊ ቡድን ነው፡፡ ይህን ያህል አሰልጣኙ የሚያስቸግር ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም ፉክክራችን ግን ለብሔራዊ ቡድኑ ጥቅም ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ፡፡
አስተያየት ይስጡ