ሀትሪክ፡- በቅርቡ ትዳር መስርተሃልና መልካም ትዳር እንዲሆንልህ እመኛለሁ ትዳርን ግን እንዴት አገኘኸው?
በረከት- ቆንጆ ነው ምንም አይል.. ተመችቶኛል ማለት ነው የምችለው… በልጅነት አይደል ኃላፊነት የወሰድኩት /ሳቅ በሳቅ/ ጥሩ ትዳር አለኝ በዚህም ደስተኛ ነኝ አይበቃም፡፡
ሀትሪክ፡- ጥሩ የመሆንህ ምስጢር የትዳርህ ሠላም መሆን አይመስልህም?
በረከት፡- ትክክል… ከሚስቴ ጋርም ሠላም መሆኔ ትልቅ አቅም ሆኖኛል… ጥሩ የሆንኩትም በዚህ ይመስለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ከሰበታ ከተማ ጋር አቻ መለያየታችሁ ምን አይነት ቁጭት ፈጠረባችሁ?
በረከት፡- በውጤቱ የፈጠረብኝ ቁጭት የለም ትምህርት ሆኖን ግን አልፏል ዋናው ምክንያት መድከማችን ነው ሰበታ ከተማ 4 ቀን አርፎ ሲመጣ የኛ እረፍት 2 ቀን ብቻ በመሆኑ ተዳክመን ነው የመጣነው ብዙ ጉልበት አውጥተናል የባህርዳር ሜዳ ደግሞ ጉልበትና አቅም ይፈልጋል በዚያ ምክንያት ተዳክመናል በተለይ ከ12 ሳምንት ጨዋታዎች የተዳከምንው ከሰበታ ከተማ ጋር ባደረግነው ጨዋታ ላይ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የጨዋታ ብልጫ ተወስዶባችሁ ነበርኮ?
በረከት፡-አዎ ብልጫማ ተወስዶብናል.. ሙሉ ጨዋታው ላይማ ብልጫ ነበራቸው ከዕረፍት በፊት ወደመነሳሳቱ ላይ ነበርን…በጨዋታ ቢበልጡንም በግብ ሙከራ እኛ የተሻልን ነበርን ኳሱን በመያዝ በልጠውናል ያገኘነውን እድል በርግጥም አልተጠቀምንም ወደ ዋንጫ የሚሄድ ቡድን ስለያዝን የሚስፈልገንን ውጤት ብቻ ነበር ግን አልሆነም ያገኘነውን እድል አምክነናል አቻ ውጤትኮ አይከፋም የትላንቱን ውጤት እኛን ማስተማር ካለበት መሸነፍ ነበረብን ብዬ የማስበው፡፡
ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማ ተመችቶሃለ.. አሰልጣኙስ?
ጌታነህ፡-ለኔ ከአዳማ ቀጥሎ የተሰማማኝ ክለብ ነው ደስተኛ ነኝ፡፡ ለመልመድም አልተቸገርኩም ያሉት ተጨዋቾችና ሙሉ አባላቱ አዳማን የሚያስታውሱኝ ናቸው አሰልጣኙን በተመለከተ ከአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቀጥሎ ያየሁት ጥሩ አሰልጣኝ ስዩም ከበደን ነው በአሰልጣኙ ደስተኛ ነኝ ለተጨዋቾች ያለው ክብር ደስ ይላልና በቡድኑም ሆነ በአሰልጣኙ ደስተኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ውድድሩ በዝግ መሆኑ ምን አይነት ስሜት ፈጠረብህ?
በረከት፡- ፋሲል ከነማን የተቀላቀልኩበት አንደኛው ምክንያት ደጋፊው ነው ነገር ግን እነርሱን ሳላይ በዝግ ሆነ… በቀጣይ በደጋፊዎቻችን ታጅበን የምንጫወትበት ሁኔታ ናፍቆኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ቀጣይ ተጋጣሚያችሁ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነውና ምን አይነት ውጤት እንጠብቅ?
ጌታነህ፡-/ሳቅ/ በቃ ከእግዚአብሔር ጋር 3 ነጥብ ይዘን መሪነታችንን እናጠናክራለን ብዬ አምናለው ጫናው እኛ ላይ የለም እነርሱ ጋር ነው ጫናው ያለውና እናሸንፋለን ብዬ አስባለሁ ቅዱስ ጊዮርጊሶች እኛ ላይ ለመድረስ ሲሉ ተጨናንቀው ስለሚገቡ እናሸንፋቸዋለን የኛ አዕምሮ ከነርሱ ይሻላል፡፡
ሀትሪክ፡- ከፊት ያሉት የጊዮርጊስ ተጨዋቾች አያስፈሩም?
በረከት፡- በፍፁም አያስፈሩኝም… እንዲህም አይነት ስሜትም የለኝም አጨዋወታችን ተመሳሳይ ስለሆነ ብዙ የሚያስፈራ ነገር የላቸውም ብዙም አንሰጋም አልፈራንም፡፡
ሀትሪክ፡- ቀጣይ ተጋጣሚዎቻችሁ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡናና ጅማ አባጅፋር ናቸው አልሰጋችሁም?
በረከት፡- እነኚህን ጨዋታዎች አሁን ማግኘታችን ደስ ይላል ለዋንጫ ጉዟችን ተከታዩን ማሸነፍ የግድ ይላል መሠረት የምንጥለውም በዚህ ጨዋታ በመሆኑ ትኩረት ሰጥተን ነው የምንገባውና በሶስቱ ጨዋታዎች ጠንክረን እንድገባ ያደርገናል ባይ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- አጠቃላይ ዳኝነቱ ምን ይመስላል?
ጌታነህ፡- በእስካሁኑ ሂደት ዳኝነቱ አይከፋም ነገር ግን ትችቱ ያለው ኦፍሳይድ የሚይዙበትና የሚለቁበት ሂደት ላይ በመሆኑ ይበልጥ መስራት አለባቸው፡፡ ከሰበታ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ ዳኝነቱ አልተመቸኝም እኛ ላይ የተቆጠረው ግብ የተገኘው ከቅጣት ምት ነው ዳኛው ቅጣት ምቱን የሰጡበት ሁኔታ አልተመቸኝም ትክክለኛ ጥፋት ነው ብዬ አላምንም… አለም ላይ ግን በቫርም እየተዳኘ ነው እኛ ጋር ግን የለም በሶስት ዳኞች ነው የሚወሰነው… መስተካከል ያለበት ነገር አለ ሊያስተካክሉ ይገባል ባይ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ዳኛን የሚያሸንፍ ቡድን አልገጠመኝም ሪጎሬ ለከለለ፣ የገባ ጎል ሻረ፣ ኦፍሳይዱን አፀደቀ፣ በረኛው ተነቃንቆ ሪጎሬው አልተደገመም የሚሉት ቅሬታዎች ይደመጣሉ በሰፊ ግብ የሚያሸንፍ ቡድን ቢኖር ይሄ ሰበብ አይፈጠርም ነበርና በአንተ በኩል ይሄንን እንዴት አየኸው?
በረከት፡-በኔ በኩል በፍፁም ዳኛን ሰበብ አድርጌ አላውቅም ክለቦች በዳኛው ላይ ሲያሳብቡ ደስ አይለኝም ዳኝነቱ መስተካከል ቢኖርበትም ለውጤት ማጣት ዳኛውን ተጠያቂ ማድረግ ግን አልወድም፡፡ ዳኛውን የሚያሸንፍ ቡድን መፍጠር አለብን ብዬ ነው የማምነው፡፡
ሀትሪክ፡- በዘንድሮ ውድድር ላይ ጎልቶ የወጣብህ ተጨዋች ማነው?
በረከት፡- የኢትዮጵያው ቡናው አቡበከር ናስር ጎልቶ የወጣ ተጨዋች ነው ከርሱ ውጪ በሊጋችን ዳዊት እስጢፋኖስን የመሰለ ተጨዋች ማየት አለመቻላችንን ታዝቤያለሁ፡፡ ሊጉ ዳዊትን የመሰለ ትልቅ ተጨዋች መፍጠር ወይም ማሣየት ተስኖታል ብዬ ነው የማስበው … አሁንም እንደ ድሮው ነው ያለው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ዳዊትን ስናየው ለኔ ትልቅ አቅምና ብቃት እንዳለው አሳይቶኛል፤ አሁንም ድረስ ልዩ ነው ትልቅ ተጨዋች ነው አድናቂው ስለሆንኩ በአጨዋወቱ ሁሌ እደሰታለሁ

ሀትሪክ፡- ከትልቅ ቡድኖች ጋር ስትጫወት የበለጠ እልኸኛ ትሆናለህ… ይህንን ሁኔታህን ታውቀዋለህ?
በረከት፡-ከትልልቅ ቡድኖች ጋር ስንጫወት ራሴን ለማሳየት እልኸኛ ሆኜ ልታይ እችላለሁ ይህንን አባባል ብዙ ጊዜ ሲነገር እሰማለሁ ከትልልቆቹ ጋር አግሬሲቭ ሆኜ ልጫወት እችላለው ከሌሎቹ ጋር ስጫወት ግን ቀለል አድርጌ ልገባ እችላለሁ ነገር ግን ይህን ማድረጌን አላውቅም ተመልካቹ ነው የሚነግረኝ… ቅዱስ ጊዮርጊስም ሆነ ሰበታ ከተማን አስቤ አበላልጬ አልገባም ሜዳ ስገባ የሚሆነውን ግን አላውቅም፡፡
ሀትሪክ፡- ለዋሊያዎቹ የመመረጥ ፍላጎትህ ምን ይመስላል?
በረከት፡- ከዚህ በፊት ከ23 አመት በታችም ይሁን ለዋሊያዎቹ ተጠርቻለሁ በተለያዩ ምክንያቶች ግን ዋናው ቡድን ላይ መጫወት ባልችልም በቀጣዮቹ አመታት የሚሳካ ይመስለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ከማዳጋስካር ጋር ለምናደርገው ጨዋታ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቢጠራኝ ብለህ ተመኝተሃል?
በረከት፡- አይ … አይ… አሁን ባለኝ ስሜት ለማዳጋስካሩ ጨዋታ ብመረጥ ብዬ አላስብም ቀጣይ ግጥሚያዎች አሉ.. በነርሱ ላይ ነው ተስፋ የማደርገው በምፈልገው ደረጃ ጥሩ አቋም ላይ ነኝ ለብሔራዊ ቡድን መመረጥ አለብኝ የሚያስብል ደረጃ ላይ ገና አልደረስኩም ምርጥ አቋሜን ከፋሲል ከነማ ጋር አሳይቼ የአሰልጣኙን ልብ የመማረክ ፍላጎቱ አለኝ፡፡ /ሳቅ/
ሀትሪክ፡- ለደጋፊዎቻችሁ የምትለው ነገር አለ?
በረከት፡-ለደጋፊዎቻችን የምለው ከእሁዱ ጨዋታ 3 ነጥብ ብቻ ጠብቁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ሽንፈትም ሆነ አንድ ነጥብ አንፈልግም መሪነታችንን አጠናክሮ የሚያስቀጥል 3 ነጥብ ጠብቁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡
አስተያየት ይስጡ