“ባህርዳር ጥሩ አቅም ያለው ቡድን ነው፤ ሊጉን በሁለተኛ ደረጃ ሆኖ እንዲፈፅም በማድረግም ለኮንፌዴሬሽን ካፑ ልናሳልፈው ዝግጁ ነን”ፍቅረሚካኤል ዓለሙ /ባህርዳር ከተማ/

“ባህርዳር ጥሩ አቅም ያለው ቡድን ነው፤ ሊጉን በሁለተኛ ደረጃ ሆኖ እንዲፈፅም በማድረግም ለኮንፌዴሬሽን ካፑ ልናሳልፈው ዝግጁ ነን”

“በችሎታዬ ሙሉ ተጨዋች ነኝ ብዬ አላስብም፤ ክፍተቶቼን ሞልቼ የሀገሪቱ ምርጥ ተጨዋች ለመባልና ለዋልያዎቹ ለመመረጥም ጥረትን አደርጋለሁ”

ፍቅረሚካኤል ዓለሙ /ባህርዳር ከተማ/

ለባህርዳር ከተማ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ላይ ከሚጫወቱት የመሀል ሜዳ ተጨዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ፍቅረሚካሄል ዓለሙ ቡድኑን በካፒቴንነት በመምራት የሚታወቅ ሲሆን ሜዳ ላይ በሚያሳየው እንቅስቃሴም በሚጫወትበት የስኪመር ስፍራ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴን እያደረገ ይገኛል።
በባህርዳር ከተማ ክለብ ውስጥ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ቆይታን ያደረገው ይኸው ተጨዋች አቢ በሚለው ቅፅል ስሙም የሚታወቅ ሲሆን ከአጥቂ ጀርባ ሆኖም የመጫወት ብቃት እንዳለው ከከዚህ በፊት የኳስ ህይወቱ በመነሳት እየተናገረም ይገኛል።
ሀትሪክ ስፖርት ይህን ተጨዋች በጋዜጠኛዋ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ አማካኝነት ስለ እግር ኳስ ጨዋታ አጀማመሩ፣ ስለ ክለቡ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአቸው እና ሌሎችንም ተያያዥ የሆኑ ጥያቄዎች አቅርባለት ምላሽን ሰጥቷታል፤ እንደሚከተለውም አንብቧት።

በልጅነት ዕድሜው እግር ኳስ ተጨዋች እሆናለሁ ብሎ አስቦ እንደሆነ

“በፍፁም፤ ያኔ ኳስን በሰፈር ደረጃ ላይ ሆኜ እጫወት የነበርኩት እንደ ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ተጨዋቾች ስሜቴን ለማርካት እንጂ ኳሱን ሲሪየስ ሆኜ በመጫወት እዚህ ደረጃ ላይ እደርሳለሁ ለማለት አልነበረም። አደግ ስልም ነው በኳሱ ጥሩ ደረጃ ላይ ስለመድረስ አስቤ የአሁኑ ስፍራ ላይ ለመገኘት የቻልኩት”።

የእግር ኳስን ተጫውቶ ስላደገበት ስፍራ

“ልጅ ሆኜ መጀመሪያ ላይ ኳስን መጫወት የጀመርኩት በተወለድኩበት ባህርዳር ከተማ ቀበሌ 08 አካባቢ ነው፤ ከዛም ወደ ቀበሌ 14 ከመጣን በኋላም እዛም ልጫወት ችያለሁ። በዚሁ ሰፈርም ነው ረጅም ጊዜም በመኖርም ኳሱን በአብላጫም ሁኔታ ልጫወት የቻልኩት”።
የእግር ኳሱን ሲጫወት ቤተሰብ ጋር ስለነበረው አመለካከት
“ያኔ ተማሪም ነበርኩ፤ አባቴም ከኳሱ ይልቅ እንድማርም ነበር ይፈልግ የነበረው። በኋላ ላይ ግን የእኔ የኳስ ፍቅር ከፍ ሲልበትና ከቁጥጥሩም ውጪ ስሆንበት ጊዜ ምንም ሳይለኝ ቀረና አሁን ላይ ደግሞ በጣም እያበረታታኝና እየደገፈኝ ይገኛል”።

በልጅነት ዕድሜው አድንቆ ስላደገው ተጨዋች

“ይሄ ተጨዋች ሀይማኖት ወርቁ ይባላል፤ ባለው ችሎታ የሚታወቅና ጎበዝ ልጅም ነበር። እሱን እያየው ከማድነቅ ባሻገር ጫማውን አድርጌም ኳስን እጫወትም ነበር”።
ከባህር ማዶ ተጨዋቾች ውስጥ እያደነቀ ስላደገው
“የማንቸስተር ዩናይትዱን ፖል ስኮልስን በቀዳሚነት ብጠራውም ክርስቲያኖ ሮናልዶንም ከልብ ነው የምወደው፤ የሁለቱ አድናቂያቸውም ነኝ”።

የእግር ኳስን ተጫውቶ ስላሳለፈባቸው ክለቦች

“የመጀመሪያ ቡድኔና ሁሉ ነገሬ አሁን እየተጫወትኩበት ያለው የባህርዳር ከተማ ቢ /ወጣት ቡድን/ ነው። ከዛም በአሰልጣኝ አብርሃም መላኩ ጊዜ ሴንትራል ዩንቨርስቲ ክለብን ልቀላቀል ቻልኩ። ከዛም ወደ ባህርዳር አምርቼ ለአንድ ዓመት ያህል ከቆየሁ በኋላ በአሰልጣኝ ደረጄ በላይ እና በኋላም ላይ አብርሃምና ለሁለት ዓመት ያህል ቡድኑን ያሰለጥን የነበረው ደግአረገ ይግዛው በነበረበት ዘመን ላይ አውስኮድ ውስጥ በመጫወት ቆይታን አደረግኩኝ። ከዚህ ቡድን በኋላም ለፋሲል ከነማ ከተጫወትኩ በኋላ ተመልሼ የአሁኑ ቡድኔን በመቀላቀል ይኸው አራተኛ ዓመቴን ልይዝ ችያለሁ”።

ባህርዳር ከተማ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ላይ እያደረገ ስላለው የውድድር ተሳትፎው

“የዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎአችን ለእኛ ጥሩ ቢሆንም በአንድአንድ ግጥሚያዎቻችን ላይ በጣልናቸው ነጥቦች አኳያ ሊጉን እንዳንመራ ወይንም ደግሞ በሁለተኛ ስፍራ ላይ እንዳንቀመጥ አድርጎናል። ያም ቢሆን ግን ክለባችን አሁንም እየተሻሻለ መጥቷልና የእዚህ ዓመት ተሳትፎውን በጥሩ ውጤት ለማጠናቀቅ ተዘጋጅቷል”።

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ከውድድሩ መሪ ፋሲል ከነማ ጋር ስላደረጉትና አቻ ስለተለያዩበት ጨዋታ

“ይሄን ጨዋታ በሚመለከት ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ነበር፤ ግጥሚያውንም እኛ ጥሩ ከመጫወታችን ባሻገር የሚያሰጥ የፍፁም ቅጣት ምትም ተከለከልን እንጂ ማሸነፍ ይገባንም ነበር”።

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ላይ ውጤት ከማምጣት አንፃር አቅደው የተነሱት

“ዋንኛው እልማችን በሊጉ የዋንጫው ተፎካካሪ መሆን መቻል ነበር። ደጋፊዎቻችንም ይህን አውቀው ዋንጫውን እንድናመጣላቸውም በስዕል አድርገው ሁሉ አምጥተውልንም ነበር። ይህን ካወቅንበት ጊዜ ጀምሮም እልማችንን ለማሳካት እየጣርን ነው። ያ ባይሳካ እንኳን ከሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት አጥብበንም ውድድሩን በሁለተኝነት ለመጨረስና በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ላይ ለመሳተፍም ከፍተኛ ጥረትን እናደርጋለን”።

ከእግር ኳስ ውጪ ጊዜውን በምን እንደሚያሳልፍ

“በአብዛኛው ቤቴ ውስጥ ነው የምገኘው። በቂ እረፍትን ማድረግ ስለምፈልግም እዛው አሳልፋለሁ”።

ስለ ትዳር ህይወቱ እና ስለ ባለቤቱ

“የትዳር ህይወቴን ምርጥ ከሆነችው እና በጣምም ከምወዳት ባለቤቴ ማስተዋል ቢሆነኝ ጋር በጥሩ ሁኔታ እየመራሁት ነው የምገኘው። በቆይታችንም የሁለት ዓመት ከአንድ ወር ልጅንም ልናፈራም ችለናል።
ባለቤቴን በተመለከተ ባለፉት ሰባት ዓመታት ቆይታችን እሷ ለእኔ ምርጧ አጣማሪዬ ነች። ሁለታችንም ተያይተን ከተጠባበስንበት ጊዜ ጀምሮም በእግር ኳሱ አሁን ለደረስኩበት ደረጃ የእሷ አስተዋፅኦ ከፍ ያለም ስለሆነ ላመሰግናት እወዳለሁ”።

ስለ ወደፊት እልሙ

“በአሁኑ ሰዓት ምርጥ በሆነው ቡድናችን ውስጥ መልካም የሚባል የጨዋታ እንቅስቃሴን እያደረግኩኝ እና በአቋሜም በኩል በጣም እየተሻሻልኩኝ ነው። እግር ኳስን መጫወት ስጀምር እዚህ ደረጃ ላይ እደርሳለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። አሁን ግን ለብሄራዊ ቡድን ተመርጦ እስከመጫወት ድረስን እያለምኩ ነው። እስካሁን አለመመረጤ ይቆጨኛል። ይሄ ደግሞ የአሰልጣኝ ውሳኔ ነው። ከዚህ በኋላ ግን ለብሄራዊ ቡድን ተመርጦ መጫወትን በጣም ስለምፈልግ በምንም ነገር ተስፋን ሳልቆርጥ ኳስ መጫወቴን እቀጥልበታለሁ”።
በእግር ኳስ ራሱን ሙሉ ተጨዋች አድርጎ ያስብ እንደሆነ
“በፍፁም፤ እኔ ራሴን በዛ ደረጃ የምገልፅ ተጨዋች አይደለሁም። በችሎታዬ ሙሉ ተጨዋች ነኝ ብዬም አላስብም። የሚጎለኝ ነገር አለ። የሚቀረኝን ነገር በመሙላት የሀገሪቱ ምርጥ ተጨዋች ለመባል ጥረትን አደርጋለሁኝ”።

ስለ ቡድናቸው አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ

“በጣም ጥሩ አሰልጣኝ ነው፤ የማሰልጠን አቅሙም ከፍተኛ ነው። ወጣት ስለሆነም በብዙ ነገሮችም ይረዳካልና ክለቡን እያስጓዘበት ያለው መንገድ ሊያስደንቀው ይገባል”።
ባህርዳር ከተማ በአንተ አንደበት ሲገለፅ
“ስለዚህ ቡድን ለመናገር ቃላቶች ናቸው የሚያጥሩኝ፤ ምን እንደምልም አላውቅም። ባህርዳር በጣም የምወደው ክለቤ ነው። ደጋፊዎቹም የሚገርሙ ናቸው። ይህ ክለብም ለእኔ ሁሉንም ነገር ሰጥቶኛል። እኔም ውለታውን መክፈል ስላለብኝ ጥሩ ነገርን መስጠቴን እየቀጠልኩበት ነው የምገኘው”።

በመጨረሻ

“ቤተሰቦቼን በቅድሚያ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ የምፈልገውን ነገር ሁሉ አበርክተውልኝ ለእዚህ ስላበቁኝ ላመስግናቸው። ከዛ ቀጥሎ በህይወት ያሉና የሌሉ ብዙ ሰዎችም ለእኔ ብዙ ነገርን አድርገውልኛል። ከእነሱ ውጪም ውዷ ባለቤቴ አለች። እንዲሁም ደጋፊዎቻችንም አሉ። ሌሎቹ የሰፈር ጓደኞቼና ያሰለጠኑኝም አሰልጣኞች ጭምርም ስለሚገኙ ለእነሱም ክብርና ምስጋናም አለኝ”።

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website