አቢጃን ላይ አዲስ ታሪክ እናፅፋለን” “የኮትዲቯር ተጨዋቾች መጎዳት ለእኛ ጥቅም የለውም፤ ሁሉም ባሉበት አሸንፈን ማለፍ ነው የምንፈልገው” አቡበከር ናስር

አቢጃን ላይ አዲስ ታሪክ እናፅፋለን”
“የኮትዲቯር ተጨዋቾች መጎዳት ለእኛ ጥቅም የለውም፤ ሁሉም ባሉበት አሸንፈን ማለፍ ነው የምንፈልገው”
አቡበከር ናስር

የኢትዮጵያ ብ/ቡድን የማዳጋስካር አቻውን ባህርዳር ላይ ገጥሞ 4ለ0 ሲያሸንፍ በ41ኛው ደቂቃ ላይ የተቆጠረችው 3ተኛዋ ጎል ለአቡበከር ናስር በነጥብ ጨዋታ የመጀመሪያው ኢንተርናሽናል ጎል ሆና መመዝገቧ ለእግር ኳሱ ክስተት የተለየ ስሜትን በውስጡ ፈጥራለች፡፡

ከሱራፌል ዳኛቸው ጋር በሚያምር የአንድ ሁለት ቅብብል (ደብል ፓስ) በሚያምር አጨራረስ ከማዳጋስካር ግብ ጠባቂ ጀርባ ባለው መረብ ውስጥ የተገኘችው ይህቺ ጎል አቡበከር ናስር በብሔራዊ ቡድን የነጥብ ጨዋታ ላይ ግብ ካስቆጠሩ ተጨዋቾች ተርታ እንዲሰለፍም አድርጋዋለች፡፡

ማዳጋስካርን በሠፊ የግብ ልዩነት በማሸነፋቸው ከወዲሁ ካሜሮንን አሻግሮ መመልከት መጀመሩን የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር ለሆነው ለጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ከጨዋታው በኋላ በስልክ ያጫወተው አቡበከር ናስር አቢጃን ላይ አዲስ ታሪክ ለማፃፍ መዘጋጀታቸውንም ጨምሮ ገልጾለታል፡፡

“በዚህ ስብስብ ውስጥ የሚንተከተክ የውጤትና አንድ ትልቅ ታሪክ የመፃፍ ረሃብ” አለ በማለት የሚናገረው አቡኪ “ኮትዲቯርን አሸንፈን ከስምንት አመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ነው ወደ ስፍራው የምንጓዘው” ሲል ተናግሯል፤“ኮትዲቮዋርን አግዝፈን አንመለከትም፤ባለፈው ሽንፈት ያቀመሰናቸውን ኮትዲቯሮችን እንደምንገጥም አስበን በድጋሚ ለማሸነፍ ነው የምንጓዘው” የሚለው አቡኪ “የኮትዲቯር ተጨዋቾች መጎዳት ጥቅሙም ጉዳቱም ለእነሱ ነው፤በእነሱ መጎዳት እኛ የምንጠቀመው ነገር የለም፤እንደውም እኛ የምንፈልገው ሁሉም ተጨዋች ባለበት አሸንፈን ማለፍ ነው” የምንፈልገው በማለት ሞልቶ የሚፈስ የሚመስል ከፍተኛ የራስ መተማመን ባለበት ስሜት በተለይ ለሀትሪክ ገልጿል፡፡

በ15 ጨዋታ 20 ጎሎችን፣የመጀመሪያ ኢንተርናሽናል ጎሉን ያስቆጠረው የዘንድሮው ልዩ ክስተት ሆኖ ብቅ ያለው አቡበከር ናስር በማዳጋስካሩ ድል ከሰጠመበት የደስታ ባህር ውስጥ ሳይወጣ በቀጣዩ ጨዋታ ዙሪያ ምን ትላለህ? በእርግጥም ከስምንት አመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ እናልፋለን? በማለት የሀትሪኩ ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ፊት ለፊት ጠይቆት ከዚህ በታች ያለውን ምላሽ ሰጥቶታል…

ሀትሪክ፡- …ማዳጋስካር ላይ ለተመዘገበው ድል እንኳን ደስ አለህ…?…

አቡበከር፡- …እንኳን አብሮ ደስ አለን…

ሀትሪክ፡-? …ከድሉ በኋላ የነበረው የደስታ ሌሊትን ግለፅልኝ ብልህ እንዴት ነው የምትገልፀው…?…

አቡበከር፡- …በጣም የተለየ ሌሊት ነበር…በጣም ከመደሰቴ የተነሣ እንቅልፍ አልተኛሁም… ስገላበጥና ቁጭብዬ ነበር ያደርኩት ማለት ይቀለኛል…ምክንያቱም ይሄ ህዝብ…ድል፣ደስታ ነው የሚገባው…ህዝብ በዚህ ደረጃ ተደስቶ ማየት አያስተኛም…

ሀትሪክ፡- …በ41ኛው ደቂቃ ያስቆጠርከው ሶስተኛው ግብ በብ/ቡድን የመጀመሪያው የነጥብ ጨዋታ ጎልህ ነው…ምን ስሜት ፈጠረብህ…?…

አቡበከር፡- …የደስታዬን መጠን ከፍ ያደርገውም ይሄ ነው…በብ/ቡድን ደረጃ በነጥብ ጨዋታ አንድም ጎል አልነበረኝም…አሁን ግን የጎል አካውንት በመክፈቴ በጣም ተደስቻለሁ…ቡድናችን 4ለ0 አሸንፎ ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ እድሉን ባሰፋበት ጨዋታ የመጀመሪያ የሆነውን ግብ በማስቆጠሬ ተደስቻለው…አሁን አንድ ብዬ የጀመርኩትን ግብ ማስቆጠር ይበልጥ የማሳደግ ፍላጎቱም አለኝ…

ሀትሪክ፡- …ከጨዋታ በፊት 4ለ0 በሚያክል ሰፊ ውጤት እናሸንፋለን የሚል ግምቱ ነበረህ…?…

አቡበከር፡- …በጎሉ ቁጥር ላይ ሣይሆን ከሁለት ጎል በላይ አግብተን ማሸነፍ አለብን የሚል ነገር በውስጣችን ነበር…ምክንያቱም እነሱ ከቻሉ ማሸነፍ ካልቻሉ አቻ መውጣትን ታርጌት አድርገው ነው የመጡት…እኛ ደግሞ እድላችንን ለማሳካት የግድ ከሁለት ጎል በላይ ማስቆጠር አለብን የሚል ሂሣብ ሠርተን ነበር የገባነው…ያ ሂሣባችን ተሳክቶልን 4 ጎል አግብተን አሸንፈናል…

ሀትሪክ፡- …ቡድኑ ከእረፍት በፊትና በኋላ ሁለት መልክ ነበረው…ከዕረፍት በፊት በጣም ጥሩ ነበር…ከዕረፍት መልስ ግን ተዳክሞ፣ብልጫ ተወስዶበት ታይቷል የሚሉ አሉ…ይሄ የተከሰተው ሶስት ጎል በማግባታችሁ ጨዋታው እንዳለቀ ቆጥራችሁ ተዘናጋታችሁ ነው…?…

አቡበከር፡- …አይደለም…ከእረፍት በፊት እነሱ ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት ካላቸው ፍላጎት ዘግተው ነበር የተጫወቱት…እኛ ደግሞ ለማስከፈት ተደጋጋሚ ጫና ስንፈጥር ነበር…በዚህ መሀለ ነው ሶስት ጎል ያስቆጠርነው…ከእረፍት መልስ ግን እነሱ ሶስት ጎል ስለገባባቸው ለማጥቃት ሲሉ ከፍተው መጫወት ጀመሩ…ይሄ ነው ልዩነት እንጂ…ጨዋታው አልቋል ብለን አልተዘናጋንም…4ኛው ጎልም የተቆጠረው እኮ ከእረፍት መልስ ነው…

ሀትሪክ፡- …ከ8 አመት በፊት ሱዳንን አሸንፈን ለአፍሪካ ዋንጫ አልፈናል…ከ8 አመት በኋላስ ይሄ ታሪክ በእናንተ ተደግሞ ለአፍሪካ ዋንጫ የምናልፍ ይመስልሃል…?…

አቡበከር፡- …በዚህ ቡድን ውስጥ አዲስ ታሪክ የማፃፍ ከፍተኛ ረሃብ አለ…በሁሉም የቡድኑ ተጨዋቾች፣አሰልጣኞች ላይም የምታነበው ይሄንን ነው…አሁን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለመመለስ በትክክለኛው መንገድ ወይም ሰዓት ላይ ነን ብዬ ነው የማስበው…በሁሉም የቡድኑ ተጨዋቾች ላይ ለአፍሪካ ዋንጫ እንደምናልፍ የእርግጠኝነት ስሜት አለ…ከአላህ ጋር እንደምናሳካውም እርግጠኛ ነኝ…

ሀትሪክ፡- …የምትጫቱት በርካታ ስመ-ጥር ተጨዋቾችን ከያዛቸው…በአህጉሪቱ እግር ኳስ ትልቅ ስም ካላት ኮትዲቯር ጋር ከመሆኑ አንፃር አግዝፈህ ነው የምትመለከተው…?…

አቡበከር፡- …ማግዘፍ ብሎ ነገር የለም…ለቡድኑ ትልቅ ክብር አለን…ከዚህ በዘለለ ግን አግዝፈን የምናይበት ምንም ምክንያት የለም…ምክንያቱም ማክሰኞ የምንገጥማት ኮትዲቯር እዚህ የገጠምናትና፣ያሸነፍናትን ኮትዲቯርን ስለሆነ በተለየ አግዝፈን አናይም…ከዚህ በፊት ያሸነፍነውን ቡድን እንደምንገጥም አስበን ነው የምንጓዘው…ወደ ሜዳም የምንገባው…

ሀትሪክ፡- …ቁርጥ ያለ መልስ ስጠኝ…ከአቢጃን ምን ይዛችሁ ትመለሳላችሁ…?…

አቡበከር፡- …ከጨዋታ በፊት እንደዚህ ላይባል ይችላል…በውስጣችን ያለው የእርግጠኝነት ስሜት ግን ይሄንን እንድንል የሚያስገድደን ነው…የመጀመሪያው ግባችን ሶስት ነጥብ መንጠቅ ካልተቻለ ደግሞ አቻም ቢሆን ወጥተን የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ትኬታችን እዛው ቆርጠን መመለስ ነው…

ሀትሪክ፡- …አቡበከር በግሉስ ከወዲሁ ምን ያስባል…?…

አቡበከር፡- …ህዝቤን የማስደሰት ሀገሬን ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማሳለፍ ትልቅ ጉጉትና ረሃብ አለኝ…ይሄን ስሜትም ይዤ ነው የምጓዘው…የምንጫወተው እንደ ቡድን በመሆኑ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን አዲስ ታሪክ የማፃፍ ጉጉት አለኝ…በጨዋታው ማንም ያግባ ማንም…ሀገራችንን ማሳለፉ ላይ ነው ቅድሚያ የምንሰጠው…ለዚህ ደግሞ በትክክለኛው መንገድ ላይ ነን ብዬ ነው የማስበው…

ሀትሪክ፡- …የኮትንዲቯር ወሳኘ ተጨዋቾች የመጎዳታቸው ዜና በስፋት እየተደመጠ ነው…ይሄ መሆኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ጥሩ አጋጣሚ ነው ብለህ እንድታስብ ያደርግሃል…?…

አቡበከር፡- …የኮትዲቯር ተጨዋቾች መጎዳት ጥቅሙም ሆነ ጉዳቱ ለእነሱ ነው…ሁለትና ሶስት ምርጥ ተጨዋቾችን ከቤስት ውስጥ ማጣታቸው ወይም መኖራቸው ጉዳቱም ሆነ ጥቅሙ ለእነሱ ነው…ከዚህ ውጩ እኛን የሚጠቅመን ነገር የለም…እኛ የአፍሪካ ዋንጫን የምናሳካው በእነሱ ጉዳት ላይ ተንጠልጥለን አይደለም…ማንም ይግባ…ማንም…አሸንፈን ድል ይዘን መመለስ ነው የምንፈልገው…እንደውም ሁሉም በተሟሉበት ሁኔታ አሸንፈን ማለፍን ነው የምንፈልገው…

ሀትሪክ፡- …በባህርዳር ብ/ቡድኑ ሽንፈት የአለመቀመሱን አጋጣሚ እንዴት ታዘብከው…?…

አቡበከር፡- …ባህርዳር በሁሉ ነገርዋ የምትመች ከተማ ናት…በባህርዳር ደስ የሚልና የማይረሣ ጊዜ ነው ያሳለፍነው…ለእግር ኳስ የተለየ ፍቅር አላቸው…ከሆቴሉ ጀምሮ ህዝቡ እስከመጨረሻው ከእኛ ጋር ስለነበር በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እወዳለሁ..አጠገባችን ሆነው ሲያግዙን ሲደግፉን ነው ያሳለፉት…ከድሉ በኋላም መውጣት እስኪያቅተን…ሲያበረታቱን… ሲደግፉን ነው ያመሹት…ለነገሩ የኢትዮጵያ ደጋፊ በሀገሩ ጉዳይ የሚደራደር አይደለም… በአጠቃላይ በባህርዳር ያለመሸነፍ ሪከርዳችን በመቀጠሉ በጣም ደስተኛ ነኝ…የውጤታማነታችን መገለጫ ከተማ በመሆንዋም እንደዚሁ ትልቅ ደስታ ነው ያለኝ…

ሀትሪክ፡- …በአሁን ሰዓት በሀገሪቱ ግጭቶች፣የሠላም እጦት ባለበት በዚህ ሰዓት ብ/ቡድኑ በሠፊ ውጤት ማሸነፉ የሚያስተላልፈው መልዕክት ይኖራል ትላለህ…?…

አቡበከር፡- …በጣም ትልቅ መልዕክት ነው የሚያስተላልፈው…ውጤቱም ከጨዋታ በላይ ትልቅ ቁምነገር አለው…ውጤቱ በሠላም ማጣት፣በተለያዩ ግጭቶች ከፊቱ ደስታ የራቀው ህዝባችን በአንድነት ተደስቶ እንዲያሳልፍ፣በአንድነት ስለ ሀገሩ እንዲዘምር፣እንዲደሰት ያደረገ…የጠፋውን ፈገግታም የመለሰ ጥሩ አጋጣሚ ነው…እኛም በሙያችን ሀገራችን አንድ እንድትሆን፣ሠላም እንድትሆን፣ህዝቡም በውጤቱ አንገቱን እንዳይደፋ፣እንዲደሰት የምንችለውን አድርገናል ብዬ አስባለው…

ሀትሪክ፡- …ከጨዋታው በኋላ ለፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ…“ኢሳያስ ለሀገር ይሠራል ገና”…እያላችሁ መዘመራችሁ አስገርሞኝ ነበር…እንዲህ ለመዘመር ያበቃችሁ ምንድነው…?…

አቡበከር፡- …(ሣቅ)…አንድ አመራር የእግር ኳሱ መሪ የሆነ ሰው ከጨዋታው በኋላ መልበሻ ቤት ድረስ መጥቶ…“ኮርተንባችኋል”…ብሎ ሲያበረታታህ በውስጥህ የሚፈጠር ትልቅ የመነሳሳት ስሜት አለ…አቶ ኢሳያስ መልበሻ ቤት ድረስ መጥተው “እናመሰግናለን” ሲሉን በጣም ደስ ብሎን ነው እንደዛ ያልነው…በየሚዲያው በየቦታው ሰው ስለድሉ ሲነጋገር ስታይ “ኮርተናል” ሲልህ ተጫዋቾችን የበለጠ ያነሳሳል…

ሀትሪክ፡- …በመጨረሻ…ከማክሰኞ ጨዋታ በኋላ የሚሰማው ዜና ምን ይሆናል…?…የሚለውን ጥያቄ በድጋሚ ጠይቄህ እንለያይ…?…

አቡበከር፡- …ከላይም ገልጬልሃለሁ…ከጨዋታው በፊት እርግጠኛ መሆን ያልተለመደ ቢሆንም…በሁላችንም ስሜት ውስጥ ካለው እርግጠኛነት በመነሣት ኮትዲቯርን አሸንፈን…ካልሆነ ነጥብ ተጋርተን ከአላህ ጋር ወደ አፍሪካ ዋንጫ የሚያስገባንን ትኬት ይዘን እንመለሳለን ብዬ ነው ተስፋ የማደርገው…ለሁም ግን እሱ ይረዳን…

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.