” ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፈን የባሰ ደስታ እናመጣለን ” ያሬድ በቀለ /ሀዲያ ሆሳዕና/

በዚህ ሳምንት በሊጉ ከታዪ አዲስ ፊቶች መካከል ወጣቱ የሀድያ ሆሳዕና ግብ ጠባቂ ያሬድ በቀለ አንዱ ነው ።

የዘንድሮውን የውድድር ዓመት በሀድያ ሆሳዕና ከ 20 ዓመት የወጣት ቡድኑ ላይ ሲጫወት ያሳለፈው ያሬድ በቀለ በክለቡ ያጋጠመውን ወቅታዊ ችግር ተከትሎ ጥሪ ከቀረበላቸው በርካታ ወጣት ተጫዋቾች መካከል ነው ።

ትውልድ እና እድገቱ በሆሳዕና ከተማ ያደረገው ግብ ጠባቂው ያሬድ በቀለ እግር ኳስን አንድ ብሎ በሰላም የእግር ኳስ ክለብ የታዳጊዎች ፕሮጀክት መጀመር ችሏል ።

ታዳጊው ግብ ጠባቂ ያሬድ በቀለ በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታውን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮችን ከሀትሪክ ስፖርት ፀሀፊው ቅዱስ ዮፍታሔ ጋር ቆይታን አድርጓል ።

በ ወጣት ቡድኑ የዘንድሮው የውድድር ዓመት ቆይታ ?

” በዘንድሮው የውድድር ዓመት ገራሚ ጊዜን አሳልፌያለው ብዬ አስቤያለው ፣ ቡድኔ አሪፍ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ከእኔ የሚጠበቀውን አድርጌያለው ብዬ አስባለው ።

አሰላ በነበረን ቆይታ እንደ ቡድን አሪፍ ባንሆንም በግል ጥሩ ነበርኩኝ ብዬ አስቤያለው ፣ ከጉዳት መልስም ለክለቤ ያለኝን ሁሉ በማድረግ የተሻለ ነገር ይዘን እንድናጠናቅቅ የተቻለኝን ሁሉ በማደረግ አምላክ ረድቶን እዚህ ደረጃ ደርሰናል ።


ጥሪውን ስለሰማበት ክስተት ?

ከ ሀዋሳ ከተማ ጋር ያደረጉትም ጨዋታ ተመልክቼ ነበር ፣ ሀድያ በስምንት ተጫዋች በመጫወቱ በጣም ተሰምቶኝ ነበር ።

ጎደኞቼ በስልክ ደውለው ነበር የነገሩኝ ሐዋሳ እስክንደርስ በጣም ጓጉቼ ነበር ።

ጥሪው ሲቀርብልኝ የምመኛው እና የማስበው ነገር ስለሆነ ለክለቤ ብዙ ነገር ማድረግ ስለምፈልግ በጣም ደስ ብሎኝ ነው ቡድኑን የተቀላቀልኩት ፣ የመጀመሪያውን ጨዋታ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ነበርኩኝ እንደ ጌታ ፈቃድ ሆኖ ከ ጊዮርጊስ ጋር በነበረው ጨዋታ ተሰልፌ መጨወት ችያለው ።

ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር እንደምሰለፍ ሳውቅ ብዙም አልደነገጥኩም አሰልጣኛችን የነገረኝን ነገር በመተግበር እሱን በማስደሰቴ በጣም ደስ ብሎኛል ፣ ከዚህ በኋላም የሚሰጠኝን ምክር እየሰማሁ ወደፊት የተሻለ ደረጃ ለመድረስ እሰራለው ።

እነሱን ስታይ የሆነ ስሜት ፈጥሮብኛል የጊዮርጊስ አጥቂዎች ልምድ ያላቸው ትልልቅ ተጫዋቾች ናቸው ትንሽም ቢሆን የፍርሀት ስሜት ነበረው ነገር ግን አሰልጣኜ የነገረኝ ብዙ ነገር ስለነበረ ምንም የመደናገጥ ስሜት አልፈጠረብኝም ።

ከጨዋታ በኋላ የነበረው ድባብ ?

ከጨዋታው በኋላ በስሜት በጣም አልቅሼ ነበር በዚህ ስብስብ ጊዮርጊስን ማሸነፋችን እራሱ በጣም ትልቅ ነገር ነው ።

ብዙ ሰው በውጤቱ ተገርሟል ገና ብዙ እናስገርማለን ብዬ ተስፋ አድርጋለው ።ከድሉ በኋላ የነበረው ሁነት በጣም ደስ ይላል ፣ ሁሉም ተጫዋች በመልበሻ ክፍል የተለየ ደስታ ውስጥ ነበር ፣ ሆሳዕና ያሉ ብዙ ደጋፊዎችም ደስታቸው እጥፍ ነበር ።

በታናናሽ ልጆች ይህ ድል በመምጣቱ በጣም ተደስተዋል ፣ ይህን ደስታ እጥፍ ድርብ ለማድረግ ቡናን አሸንፈን የባሰ ደስታ እናመጣለን ብዬ አስባለው ” ሲል ወጣቱ ግብ ጠባቂ ከ ሀትሪክ ስፖርት ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሯል ።

ሀድያ ሆሳዕና የፊታችን ዕሁድ በዘጠኝ ሰዓት ከ ኢትዮጵያ ቡና ጋር መርሐ ግብራቸውን የሚያካሂዱ ይሆናል ።

Hatricksport website Editor

Twitter

kidus Yoftahe

Hatricksport website Editor