“ባልተከፈለኝ ደመወዝ ከማዘን ይልቅ ባገኘሁት ዕድል መደሰትን መርጫለሁ” ወንድማገኝ ኃይሉ /ሀዋሳ ከተማ/

የአመቱ ተስፋ የተጣለበት ወጣት” በሚል የተመረጠ ታዳጊ በአሰልጣኙ ትግል ለውጤት ሲበቃ የማየትን ያህል ምን ደስ የሚል ነገር አለ? በሀዋሳ የሆነው ይሄ ነው… እድሜ ለአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ይሁንና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ነገ የሚያስጨፍረውን ተስፋ የጣለበትን ወጣት አግኝቷል፡፡ ሀዋሳዎች ከሚታወቁበት ወጣትን የማሳወቅ መርሃቸው አፈግፍገዋል ወይ? የሚል ጥያቄ እንዲነሳ ያደርጉት የአመቱ ተስፋ የተጣለበት ኮከብ ተብሎ የተመረጠውን ወንድማገኝ ኃይሉን በቢጫ ቲሴራ ያስፈረሙት በአሰልጣኙ ከገጠማቸው “እፈልገዋለው” የሚል ትግል ተረተው ነው፡፡ እስከ ሁለተኛው ዙር ድረስ ለዚህ ተስፋ ያለው ወጣት ደመወዝ ለመክፈል አልፈቀዱም ተስፋ ያልቆረጠው ወጣት ግን በብርታቱ አሸንፏቸው ይሁን ወሬው በመውጣቱ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ክፍያ እያደረጉለት ይገኛሉ… ወንድማገኝ ኃይሉ ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር የነበረው ቆይታ ይህን ይመስላል፡፡


ሀትሪክ፡- እንኳን ደስ አለህ…

ወንድማገኝ፡- እንኳን አብሮ ደስ አለን… አመሰግናለሁ

ሀትሪክ፡- “ተስፋ የተጣለበት ኮከብ” የሚለውን ሽልማት ጠብቀኸው ነበር…?

ወንድማአገኝ፡- በፍፁም አልሰማሁም ምንም መረጃም አልነበረኝም የሚያውቁኝ ሰዎች ግን አንተ ትሆናለህ ይሉኝ ነበር ሸራተን አዳራሽ ውስጥ ገብቼ ነው መመረጤን ያረጋገጥኩት ምርጥ ምሽት ነበር ብዙዎቹ እንኳን ደስ አለህ ብለውኛል ከሁሉም ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አብዱልከሪም መሀመድ እንኳን ደስ ብሎኛል ከዚያ ውጪ የቅርብ ጓደኞቼ ደስታቸውን ገልፀውልኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ከ17 እና 2ዐ አመት በታች የሀዋሳ ከተማ ቡድን ጋር ዋንጫ ወስደሀልና ስለቡድኖቹ እስቲ አውራኝ…?

ወንድማአገኝ፡-ከ17 አመት በታች ቡድኑ ጥሩ ነበር ምድቡን ሁለተኛ ሆነን አጠናቀን የቶርናመንቱን ነው ያሸነፍነው ጥሩ ጊዜ ነበረን ውድድሩ ዝዋይ ነበር የተካሄደው አሪፍ አሪፍ ልጆች ነበሩት… ከ2ዐ አመት በታችም የምድቡን ዋንጫ አሸንፈናል ከ17 አመት በታች ቡድን ላይ የመጣነው እዛው ከቆዩት ተጨዋቾች ጋር ሆነን ዋንጫውን አንስተናል በወቅቱ ከ17 እና 2ዐ አመት በታች ቡድን አሰልጣኝ ብርሃኑ ፈየራ ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- በ2ዐ14 የአመቱ ኮከብ ተጨዋች ተብለህ ትመረጣለህ ብለን እንጠብቅ…?

ወንድማአገኝ፡- /ሣቅ/ ዘንድሮ ነው ወደ ዋናው ቡድን ያደኩት….ጥሩ ጊዜ እንደነበረኝ ማሳያ ነው፡፡ በ2ዐ14 ከጌታ ጋር አልሜ ነው ወደ ዝግጅት የምገባው… እርሱ ነው የሚያሳካውና በርሱ አምኜ ነው የምገባው ይሳካልኛል ብዬ እተማመናለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ከ2ዐ አመት በታች ቡድን ጋር ሄደህ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ቀነሰህና ተናደህ “እኔ ዝላታን ኢብራሂሞቪች ነኝ ከዚህ በኋላ ታምኖብኝ እጫወታለሁ እንጂ ለሙከራ አልሄድም ማለትህን ሰማሁ… እውነት ነው…?

ወንድማአገኝ፡-/ሳቅ በሳቅ/ ከየት ሰማኸው? በጨዋታ መሀል ነው ለጓደኛዬ ያልኩት /ሳቅ/ አንዳንዴ በራስህ ላይ ትልቅ እምነት ሊኖርህ ይገባል እግር ኳስ አንዳንዴ ላይመች ይችላል ነገር ግን ልብህ መጠንከር አለበት ምናልባት አሪፍ ስላልሆንክ ነው የቀነስኩህ ይል ይሆናል በውስጤ ያለውን ፅኑ እምነት ስለማውቅ ቅር ብሎኛል በተረፈ ጥሩ ጊዜ ከፊቴ አለ፡፡


ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ ተመስገን ይዞት ለዋንጫ ደርሶ በተሸነፈው ብ/ቡድን ውስጥ አባል ነበርክ… ወደ 1ዐ የሚጠጉ ግቦችን አሲስት አድርገሃል… እስቲ ስለ ብ/ቡድኑ አውራኝ…?

ወንድማአገኝ፡-የመሀል ተጨዋች የሚታወቀው ጎል የሆነ ኳስ በማቀበል ይሆናል አጥቂ የማይሆኑ አማካዮችም ይኖራሉ እኔ ግን ግብ ከማስቆጠር ይልቅ አጥቂውን ከግብ ጠባቂው ጋር ማገናኘት ያስደስተኛል ብሔራዊ ቡድኑ ላይም ጥሩ ጊዜ ነበረን ደስ የሚል ጊዜ አሳልፌያለሁ ምናልባት ዋንጫውን ማጣታችን ካልሆነ በስተቀር…

ሀትሪክ፡- ግብ የሆነ ኳስ በማቀበል የምታደንቀው ተጨዋች ማነው…?

ወንድማአገኝ፡- የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ ማየት የቻልኩት ሀዋሳ ላይ የሀዋሳን ጨዋታ ብቻ ነው፡፡ የአብዛኛውን ቡድኖች ጨዋታ አላየሁም 2ዐ1ዐ ላይ ነው በትክክል ፕሪሚየር ሊጉን ማየት የጀመርኩት… ያኔ ታዲያ ሀዋሳ ላይ የነበሩት እነ ታፈሰ ሰለሞን ደስ ይሉኝ ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- በ24 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ላንተ ምርጡ ተጨዋች ማን ነበር…?

ወንድማአገኝ፡-በሊጉ ብዙ ምርጦች አሉ እነ አቡበከር የባህርዳሩ ፍፁም አለሙ ከሀዋሳ ከተማም ብሩክ በየነ ጥሩ ነበሩ… ውጤታማ ጊዜ አሳልፈዋል፡፡

ሀትሪክ፡- ዲ.ኤስ.ቲቪና ያንተ ወደ ዋናው ቡድን ማደግ መገጣጠሙ እድለኛ ነኝ አያሰብልህም ?

ወንድማአገኝ፡- በጣም ደስተኛ ነኝ እድለኛም ነኝ፡፡ ዲ ኤስ ቲቪ ሊጉ በራሱ እንዲታይ ማድረጉ የታየ እውነት ነው ከኔ ጋር መገጣጠሙ የመጀመሪያም ተስፋ የተጣለበት መባሌ አስደስቶኛል ዲ.ኤስ.ቲቪ ባይኖር ይሄ ሁሉ ላይሆን ይችል ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- ተስፋ ቡድን ላይ በዛብህ ከሚባለው ተጨዋች ጋር ያላችሁ መናበብ ምርጥ ነበር… የተጋጣሚን ተጨዋች አልፋችሁ ካላረካችሁ የራሳችሁንም ተጨዋቾች ሳትተያዩ ተግባብታችሁ ታልፋላችሁ እስኪባል ድገስ ምርጥ ነበራችሁ… ስለሁለታችሁ ግንኙነት ምን ትላለህ …?

ወንድማአገኝ፡-/ሳቅ በሳቅ/ ጥሩ መግባባት አለን የምንኖረው ሀዋሳ እሱ ዐ2 እኔ ዐ3 ሰፈር ነበረና በቅርበት መገናኘት ስለምንችል እየተገናኘን እናወራለን ጥሩ ቅርበትም አለን ጎበዝ ተጨዋች ነው አብዛኛው ተመልካች “ዣቪና ኢኒየሽታ” ይለን ነበር አሁንም አብሬው ብጫወት ደስ ይለኛል በሀዋሳ ከ2ዐ አመት በታች ቡድን ውስጥ ነው ያለው ዘንድሮ ያድጋል ብዬ አስባለሁ… ቢመጣ ደስ ይለኛል ምርጫው ግን የአሰልጣኞቹ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ከ2ዐ13 ዋናው ቡድን ያደከው በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ትግል ነው.. ከርሱ ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል…?

ወንድማአገኝ፡-የአሰልጣኝና ተጨዋች ጥሩ የሚባል ግንኙነት አለን ይህን እድልም ያገኘሁት ሙሉጌታ ከመጣ በኋላ ነው እርሱ ነው አምኖ ያጫወተኝ… ይህን ሽልማት በዚህ እድሜ ለማግኘቴ ከማንም በላይ የርሱ አስተዋፅኦ ትልቅ ነው ብዬ አምናለሁ ማንም ወጣትን አምኖ በማያጫወትበት ጊዜ አምኖ ስላሰለፈኝ ላመሰግነው እወዳለሁ አሰልጣኙ በራስ መተማመኔን ጨምሯል ታዳጊዎች ትልቅ አቅም እንዳላቸው በኔ ውስጥ አሳይቷል፡፡ ኮከብ እጩ ውስጥ እንዳለው ነግሮኛል እንዳንተ ቡድኑን የጠቀመ የለምና ሽልማቱን ያንተ ነው ይለኝ ነበር ለሙሉ ድጋፉም አመሰግነዋለው፡፡

ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በግሉና ከጓደኞቹ እየወሰደ የተወሰነ ገንዘብ ይስጥህ እንደነበርና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ደመወዝ እንዳልተከፈለህ ሰማሁ እውነት ነው ደመወዝ አልነበረህም…?

ወንድማአገኝ፡- ደመወዝማ እስከ 2ኛ ዙር ድረስ አልከፈሉኝም የቡድኑ ተጨዋቾች አሰልጣኞቹ እነ ሙሉኔታና ብርሃኑ ከጓደኞቼ ጋር እኩል እንድንሆን ብለው አዋጥተው ይሰጡኝ ነበር በእርግጥ ስላልተከፈኝ ብዙም አልተከፋሁም የመጫወቱን እድል በማግኘቶ ግን ተደስቻለሁ ብሩ ቀስብሎ ይመጣል ብዬ አምናለሁ አሁን ጥሩ ስለሆንኩ ስራዬን አይተው መክፈል ጀምረዋል ባልተከፈለኝ ደመወዝ ከማዘን ይልቅ ባገኘሁት ዕድል መደሰትን መርጫለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ኮከብ ተብለህ 1ዐ5 ሺ ብር ተሸለምክ.. ካሳ ነው ማለት ይቻላል? ታዳጊ ኢንቨስተር ነኝ አልክ አሉ…?

ወንድማአገኝ፡- /ሳቅ/ ኧረ በፍፁም አላልኩም… /ሳቅ/ ገንዘቡ ግን እንዳይጠፋ ከቤተሰብ ጋር ተነጋግሬ አንድ ነገር ላይ ማዋሌ አይቀርም የሚገርመው ስለ ኳስ ብዙም አይደሉም ቤተሰቦቼ የልጃቸው ነገር ሆኖ ዜናውን ሲሰሙ እንደኔ ነው የተደሰቱት…ዐ3 ሰፈር ውስጥ ባሉት ጓደኞቼ ደስተኛ ነኝ ከሽልማቱ በፊት ስጫወት ጀምሮ ያበረታቱኝ ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- ለቡድን ጓደኞችህ ጥሩ የተባለ ኳስ አቀብለህ ግብ ሲያስቆጥሩ ደስታህን የምትገልፀው በፈገግታ ብቻ ነው አሉኝ… ለምን..?

ወንድማአገኝ፡- እኔ አቀብዬ ግብ ሲቆጠር ደስ ይለኛል.. ግን ተጨማሪ ነገር ላይ ስለመስራት ስለማስብ የተለየ ደስታ ማሳየት አልሻም የተሻለ ግብ ወደ ማስቆጠር እንድዞር ልቤ ስለሚያስብ በተቆጠረው ግብ ተደስቼ መቆየት አልመርጥም ለዚያ ይሆናል ብዙም ስደሰት ያልታየሁት፡፡

ሀትሪክ፡- “ተስፋ የተጣለበት ኮከብ” ተብለህ ተሸልመሃል ተስፋውን ተግባራዊ አድርጌ ለመስራት አቅሙ አለኝ ብለህ ታምናለህ…?

ወንድማአገኝ፡- በሽልማቱ ደስ ያለኝ ነገዬን ስለሚያሳይ ነው…እግር ኳስን በዲሲፕሊን ስለምጫወት መጪው ጊዜዬ ለኔ መልካም ይሆናል የምችለውን ላደርግ ተዘጋጅቻለሁ እድገቴ ላይ ትልቅ ትኩረት ነው የምሰጠው… በባህሪዬ ብዙም መዝናናት አልወድም ከጓደኞቼ ጋር ዎክ ካደረኩ ይበቃኛል /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- በቀጣይ አመታት ለመጫወት የምታልመው የትኞቹ ክለቦች ጋር ነው…?

ወንድማአገኝ፡- እድሉን ለሰጠኝ ሀዋሳ ከተማ ክብር አለኝ አሁን ባለኝ ቆይታም ደስተኛ ነኝ፡፡ የወደፊቱን ካልከኝ ከልጅነቴ ጀምሮ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ በመሆኔ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የመጫወት ፍላጎት አለኝ ከውጪ ለሪያል ማድሪድና ለማን.ዩናይትድ የመጫወት ህልም አለኝ የምወዳቸው ክለቦቼ ናቸው ለሩኒና ሮናልዶም ትልቅ ፍቅር አለኝ…. የምችለውን ያህል በርትቼ እየሰራሁ ነገዬ ላይ ማለም ደስ ይለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- የመጨረሻ ቃል….?

ወንድማአገኝ፡- ጠብቆ እዚህ ላደረሰኝ አምላኬ እግዚአብሔር ምስጋናዬ ይድረሰዉ ከዚያ በመቀጠል ለቤተሰቦቼ፣ ለጓደኞቼ፣ በተለይ ለሀዋሳ ዐ3 ቀበሌ ነዋሪዎች፣ ለሀዋሳ ስፖርት ቤተሰብ፣ አምነው እድሉን ለሰጡኝ አሰልጣኞች ሙሉጌታ ምህረትና ብርሃኑ ፈየራ እንዲሁም ለኔ ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport