” ለብሄራዊ ቡድን እመረጣለሁ ብለህ ታስባለህ የሚለውን ጥያቄ ተመልካች ቢመልስ ይሻላል “
” በአሁን ሰዓት በአፍሪካ ውስጥ ጥሩ እግር ኳስን የሚጫወት ብሄራዊ ቡድን አለን ” ሚሊዮን ሰለሞን /አዳማ ከተማ/
የ2014 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሲዳማ ክልል ዋና ከተማ ሀዋሳ ላይ እየተካሄደ ይገኛል ውድድሩም ስምንተኛ ሳምንት ላይ የደረሰ ሲሆን በእነዚህ ሳምንታት ውስጥ በየጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ እያስመለከቱን ያሉ ተጫዋቾች አሉ ።ከእነዚህ ውስጥ በመሐል ተከላካይነት እና በቀኝ መስመር ተከላካይነት ወጥ አቋም እያሳየ ከሚገኘው የአዳማ ከተማው ሚሊዮን ሰለሞን ጋር ሀትሪክ ስፖርት ድህረገጽ ቆይታ አድርጋለች።
ሀትሪክ:- በመጀመሪያ ስለ ራስህ ትንሽ ነገር አጫውተን
ሚሊዮን:- ሚሊዮን ሰለሞን እባላለሁ ውልደቴ እና እድገቴ ዱራሜ ከተማ ነው
ሀትሪክ:- እግር ኳስ አጀማመርህ እንዴት ነበር
ሚሊዮን:- እግር ኳስን መጫወት የጀመርኩት ትምህር ቤት ነው ከዛ ከወጣን በኋላም እንጫወት ነበር የቀድሞ ሀላባ ከተማ ኢትዮጵያ ቡና ሀዲያ ሆሳዕና እና አዳማ ከተማ ተጫዋች አሁን ደግሞ ለሀምበሪቾ ዱራሜ እየተጫወተ የሚገኘው ትዕግስቱ አበራ ስጫወት አይቶኝ እሱ ለሚያሰለጥነው ፕሮጀክት ጠራኝ ከዛ ለቀበሌያችን መጫወት ጀመርኩ ። በዚህ ውድድር ላይ ስጫወት የተመለከተኝ የዱራሜ ከተማ አሰልጣኝ የነበረው ኢያሱ ቡናሮ ለከነማው ጠራኝ ።ከከነማው ጋር ወላይታ ሶዶ ላይ የደቡብ ክልል ክለቦች ሻምፒዮን መሆን ቻልኩ ።ከከነማው በኋላ ሀምበሪቾ ዱራሜን ተቀላቀልኩኝ ።
ሀትሪክ:- በሀምበሪቾ ዱራሜ የነበረህ ቆይታህ እንዴት ነበር?
ሚሊዮን:- በሀምበሪቾ ዱራሜ የነበረኝ ቆይታ በጣም ጥሩ ነበር ከአንደኛ ሊግ ወደ ከፍተኛ ሊግ ክለቡን ማሳደግ ችያለው ከጓደኞቼ ጋር ከዛ በተጨማሪ በክለብ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጫወትኩትም እዛ ስለሆነነ የሀምበሪቾን ቆይታዬን እወደዋለው።
ሀትሪክ:- ከሀምበሪቾ በኋላ ወዴት ነበር ያመራኸው?
ሚሊዮን:- በ2009 ከሀምበሪቾ ጋር ወደ ከፍተኛ ሊግ ካደግን በኋላ ድሬ ዳዋ ላይ ወደ ከፍተኛ ሊግ ያደጉ ክለቦች ውድድር ነበራቸው እዛ ውድድር ላይ ባሳየሁት ጥሩ ነገር አዲስ አበባ ከተማን መቀላቀል ችያለው
ሀትሪክ:- ከመዲናዋ ክለብ ነው ወደ ሲዳማ ቡና ያመራኸው ማለት ነው
ሚሊዮን:- አዎ ለአዲስ አበባ ከተማ አመቱን ሙሉ በቋሚነት ነው የተጫወትኩት የአሁኑ የሀዋሳ ከተማ አሰልጣኝ የሆነው ዘርአይ ሙሉ ይከታተለኝ ነበርና ለሲዳማ ቡና እንድፈርም አደርገኝ ።በሲዳማ ቡናም ብዙም አልተቸገርኩም ምክንያቱም የቡድኑ ተጫዋቾች አሰልጣኞች እና ደጋፊው ጥሩ አቀባበል ነበር ያደረጉልኝ በሲዳማ ቤትም ደስ የሚል ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት።
ሀትሪክ:- ለ2013 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሲዳማ ቡና ጋር ዝግጅት እያደረክ ባለህበት ሰዓት ጉዳት አጋጥሞህ እስከ ውድድሩ አጋማሽ ድረስ ህክምና ላይ ነበርክ ።ህክምናህን ጨርሰህ ወደ ክለቡ ስትመለስ የተሰጠህ ምላሽ ምን ነበር?
ሚሊዮን:- በዝግጅት ላይ የደረሰብኝ ጉዳት የጡንቻ መሳሳብ ነበር ለረጅም ጊዜም ህክምና ላይ ነበርኩ :ህክምናዬን እንደጨረስኩ የሲዳማ አሰልጣኝ የነበረው ዘርአይ ክለቡን ለቀቀ እኔም ወደ ክለቡ ስመለስ ከክለቡ ሃላፊዎች የተሰጠኝ ምላሽ አዲሱ የክለቡ አሰልጣኝ ልምምድ ላይ ከጉዳት ማገገምህን እና ያለህበትን አቋም ማየት ይፈልጋል ስለዚህ በዚህ መንገድ ነው ወደ ክለባችን መቀላቀል የምትችለው አሉኝ : በዛው ሰዓት ደግሞ አሰልጣኝ ዘርአይ አዳማ ከተማን ተረከበ አዳማን ከተረከበ በኋላ ክለቡን እንድቀላቀል ጠየቀኝ እኔም ሳላመነታ ጥያቄውን ተቀበልኩኝ ።

ሀትሪክ:- የአዳማ ቆይታህ እንዴት ነው?
ሚሊዮን:- አዳማ ትልቅ ክለብ ነው በርካታ ደጋፊዎች አሉት ለዚህ ክለብ መጫወት ክብር ነው በእስካሁን ቆይታዬ በጣም ደስተኛ ነኝ ከክለቡ ጋርም ስኬታማ ጊዜን አሳልፋለው ብዬ አስባለው ።
ሀትሪክ:- በ2014 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሰባቱ ሳምንት ጨዋታ ወጥ አቋምህን እያሳየህ ትገኛለህ : ለዘንድሮ ውድድር የተለየ ዝግጅት አድርገኸል ?
ሚሊዮን:- የተለየ ዝግጅት እንኳን አላደረኩም ከዝውውር ጋር በተገናኘ ከአዳማ ጋር ረጅም ሰዓት ድርድር ላይ ነበርኩ ከዛ በኋላ ግን በግሌም እየሰራው ራሴን በሚገባ ሳዘጋጅ ነበር ።የክለባችን አሰልጣኞችም በጣም አግዘውኛል በእያንዳንዷ ልምምድ ላይ ማስተካከል ያሉብኝን ነገሮች ይነግሩኛል አሁን ላለሁበት አቋም የእነሱ እግዛ ከፍተኛ ነው።
ሀትሪክ:- ስለ ብሔራዊ ቡድን ምን ታስባለህ?
ሚሊዮን:- ሁሉም እግር ኳስ ተጫዋች አንድ አላማ አለው እሱም ሀገሩን መወከል ነው ከልጅነቴ ጀምሮ ለብሔራዊ ቡድን መጫወትን አልም ነበር ያ ጊዜም ይመጣል ብዬ አስባለው : ዘንድሮ ከነበሩኝ አላማዎች አንዱ ለብሔራዊ ቡድን መጫወት ነው ለዚህም ነው ጠንክሬ እየሰራው ያለሁት ።
ሀትሪክ:- አሁን እያሳየህ ባለኸው አቋም ለብሔራዊ ቡድን እመረጣለው ብለህ ታስባለህ?
ሚሊዮን:- ይሄን ጥያቄ ተመልካቹ ቢመልስ ይሻላል
ሀትሪክ:- ለምን?
ሚሊዮን:- ምክንያቱም ውጪ ያለው ተመልካች ነው በደንብ የሚያየኝ ስለዚህ የማሳየው እንቅስቃሴ ለብሔራዊ ቡድን እንደሚመጥን እና እንደማይመጥን እነሱ ስለሚያውቁት ነው
ሀትሪክ:- ስለ ብሔራዊ ቡድናችን የምትለው ነገር አለህ?
ሚሊዮን:- ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ያለ ብሔራዊ ቡድን ነው በአሁን ሰዓት አፍሪካ ውስጥ ጥሩ እግር ኳስን የሚጫወት ብሔራዊ ቡድን አለን በአፍሪካ ዋንጫ ላይም የተሻለ ውጤት እንደምናመጣ እርግጠኛ ነኝ
ሀትሪክ:- የወደፊት አላማህ ምንድነው?
ሚሊዮን:- ለረጅም አመት ሀገሬን ማገልገል እፈልጋለው ከዛ ውጪ ከሀገር ወጥቼ መጫወትም እፈልጋለው ለዚህ ደግሞ ጠንክሬ መስራት አለብኝ ያንን እያደረኩ ነው ከእግዚአብሔር ጋር ይሳካልኛል ብዬ አስባለው
ሀትሪክ:- ትርፍ ጊዜህን በምንድነው የምታሳልፈው?
ሚሊዮን:- ትርፍ ጊዜዬን ለረጅም ሰዓት በመተኛት ነው የማሳልፈው የግድ ከልምምድ እና ከጨዋታ በኋላ እረፍት ስለሚያስፈልገኝ እተኛለው ከዛ በተረፈ ከጓደኞቼ ጋር ሻይ ቡና እንላለን

ሀትሪክ:- ለአንተ አርአያ የሆነ ተጫዋች ማነው?
ሚሊዮን:- ልጅ እያለው ጀምሮ ስለ ደጉ ደበበ እየሰማው ነው ያደኩት ሲጫወት ሳላየው ነበር የምወደው ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ለብሔራዊ ቡድናችን ሲጫወት አየሁት ከዛ እንደሱ መሆን አለብኝ ብዬ ወሰንኩ።አብረውኝ ከተጫወቱ ተጫዋቾች ደግሞ ፈቱዲን ጀማል ይመቸኛል።
ሀትሪክ:- ከሀገር ውጪ የምትደግፈው ክለብ እና ተጫዋች አለ?
ሚሊዮን:- ከሀገር ውጪ የሰርጂዮ ራሞስ አድናቂ ነኝ ከክለብ የቼልሲ ደጋፊ ነኝ
ሀትሪክ:- በመጨረሻ ማለት የምትፈልገው ነገር ካለ
ሚሊዮን:- ማመስገን የምፈልጋቸው ሰዎች አሉ በመጀመሪያ እዚህ ላደረሰኝ ልዑል እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ በመቀጠል ውድ ቤተሰቦቼን አመሰግናለሁ ፕሮጀክት ላይ ያሰራኝን ትዕግስቱ አበራን አመሰግናለው: እዚህ ደረጃ እንደምደርስ ደጋግሞ ይነግረኝ የነበረው እና እግር ኳስን ለማቆም በወሰንኩ ሰዓት አይሆንም በማለት ለዱራሜ ከነማ እንድጫወት ያደረገኝን አሰልጣኝ ኢያሱ ቡናሮ(ካምፓላን) በጣም አመሰግናለሁ : ሀምበሪቾ ስጫወት የተለያዩ ቦታዎችን መጫወት እንድችል በብዙ ነገር የረዳኝን አሰልጣኝ ተረፈ ታደሰ(ላጠው) አመሰግናለው: አሰልጣኝ ዘርአይ ሙሉንም እጅግ በጣም አመሰግናለው: ከዛ በተረፈ የብሔራዊ ቡድናችን ምክትል አሰልጣኝ አስራት አባተ : የአዳማ ከተማ የአሰልጣኞች ስታፍን እና ተጫዋቾችን ከልብ አመሰግናለው
አስተያየት ይስጡ