“ለ2ኛነት ቦታ ተስፋ ባንቆርጥም ከባድ ፍልሚያ ግን ይጠብቀናል ብዬ እሰጋለሁ” /ሚካኤል ጆርጅ/ሀድያ ሆሳዕና/

ሀትሪክ፡- በሰበታ ከተማ የደረሰባችሁ ሽንፈት ያበሳጫል ምን አስተያየት አለህ..?

ሚካኤል፡- አዎ አለቀ ተብሎ አቻ ወጥተን አንድ ነጥብ አገኘን እያልን ባለበት ደቂቃ ግቡ መቆጠሩ ያበሳጫል ግቡ ተቆጠረ መሃል ሜዳ ሄደን እንደጀመርን ነው ዳኛው ፊሽካውን የነፋው… በነበረን የጨዋታ እንቅስቃሴ ማሸነፍ ሲገባን አቻ ነጥብ ባለቀ ሰዓት ሲወሰድብህ ያማል… ቅር ብሎኛል፡፡

ሀትሪክ፡- የኮንፌዴሬሽን ካፕ ተሳትፍ የማግኘት እድል ካላቸው 4 ክለቦች መሀል ሀዲያ ሆሳዕና አንዱ ነው… የሚሳካ ይመስልሃል…?

ሚካኤል፡-አሁን ያለን ቡድን ልምድ ያለው አይደለም አብዛኞቹ ተጠባባቂ የነበሩና ብዙ ጊዜ ያልተሰለፉ ከወጣቱ ቡድን ያደጉ መሆናቸውን ከግምት ማስገባት ይገባል፡፡ ቀጣይ ተጋጣሚያዎቻችን ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡናና ጅማ አባጅፋር ናቸው ሙሉ ቡድን ቢኖረን ሶስቱንም ነጥብ ማስጣል አይቸግረንም ነበር፡፡ አሁን ትንሽ ከበድ ያለ ትግል ይገጥመናል ብዬ አስባለው፡፡ ለ2ኛነት ቦታ ተስፋ ባንቆርጥም ከባድ ፍልሚያ ግን ይጠብቀናል ብዬ እሰጋለሁ፡፡ ወጣቶቹ ለቀጣዮቹ ጊዜ ተበርቶባቸው ምርጥ ቡድን መገንባት ይቻላል በቀጣይ ጊዜያት ተስፋ እንዳላቸውም በሰበታ ከተማ ጨዋታ አሳይተዋል አሁን ካለን ጊዜና ከምናገኛቸው ተጋጣሚዎች አንፃር እድላችን ፈተና የሚገጥመው ይመስላል፡፡

ሀትሪክ፡- የተፈጠረው ችግር ባይከሰት ኖሮ በተከታታይ ሽንፈት ይገጥማችሁ ነበር… ውስጥህ ምን ይላል..?

ሚካኤል፡- እየሄድንበት ከነበረው ጉዞ አንፃር 2ኛ ሆነን በኮንፌዴሬሽን ካፕ ሀገራችንን የመወከል አቅሙም እድሉም ነበረን እየመጣንበት በነበረው አካሄድ በሀዋሳ ከተማም ሆነ በሰበታ ከተማ እንሸነፋለን ብዬ አልገምትም በጥሩ ሙድ እየተፋለምን ነበር እግር ኳስ ነውና የሚገጥምህ ነገር ከፍ ወይም ዝቅ ሊያደርግህ ይችላል እኛንም የገጠመን ይሄ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- በመጨረሻ…?

ሚካኤል፡- አሁንም ተስፋ አንቆርጥም የሚቻለንን ሁሉ አድርገን ያሰብነውን ለማሳካት እንሞክራለን፡፡ በቀጣይ አመታት ከተሰራባቸው ውጤታማ መሆን የሚችሉ ወጣቶችን ይዘናል ለአሁኑ ግን የሚመጣውን ውጤት በፀጋ ለመቀበል ተዘጋጅተናል፡፡

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport