“ለቅዱስ ጊዮርጊስ ባይመጥንም በኮንፌዴሬሽን ካፕ ለመሳተፍ ብለን ጠንክረን እየሰራን ነው” ምንተስኖት አዳነ /ቅዱስ ጊዮርጊስ/

ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ በ34 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል በኮንፌዴሬሽን ካፕ ለመሳተፍ ያላችሁ እድል ለመጠቀም ምን ያህል እየተዘጋጃችሁ ነው?

ምንተስኖት፡- እውነት ለመናገር 2ኛ ሆኖ በኮንፌዴሬሽን ካፕ መሳተፍ ለጊዮርጊስ የሚመጥን አይደለም፡፡ አሁን ግን ያለን እድል ይሄ ቦታ ብቻ በመሆኑ በኮንፌዴሬሽን ካፕ ለመሳተፍ ብለን ጠንክረን እየሰራን ነው በቀሪ 3 ጨዋታዎች 9 ነጥብ የግድ ያስፈልገናል የኢትዮጵያ ቡና ነጥብ መጣልን ጠብቀን እድሉን ለመጠቀም 3ቱን ጨዋታ ለማሸነፍ የምንችለውን እናደርጋለን ብለን እናስባለን፡፡

ሀትሪክ፡- ከሲዳማ ቡና ጋር በነበራችሁ ጨዋታ ላይ ደካማ አቋም ነው ያሳያችሁት…ምክንያቱ ምን ይሆን?

ምንተስኖት፡- እውነት ነው ጥሩ አልነበርንም የግብ ሙከራም አሳዳረግንም አቋማችንም ልክ አይደለም ጥሩ የውድድር አመት ነው ያሳለፍነው ማለት አልችልም ብዙ ጨዋታ ተሸንፈናል አቻም ወጥተናል ይሄ የቅዱስ ጊዮርጊስ አቋምም አልነበረም፡፡ ከሲዳማ ቡና ጋር ካደረግነው ጨዋታ አስቀድሞ ከባህርዳር ከተማ ጋር በከፍተኛ ተነሳሽነት ስንጫወት ነበር የዝናም ጨዋታ በመሆኑ ከፍተኛ ጉልበትን አውጥተን ነበርና ድካም ተሰምቶን እንደነበር ያስታውቃል እንደ ብቸኛ ምክንያት ባይሆንም ድካሙ አስተዋፅኦ አድርጓል ብዬ አምናለው በሜዳ ላይ የነበረው እንቅስቃሴም ጥሩ አልነበረምና ሲዳማ ቡና በተቃራኒው የግብ እድሎችን ፈጥሮ ሁለት ግቦችንም አስቆጥሮ አሸንፎናል፡፡

ሀትሪክ፡- በዚህ አያያዝ 2014 ለቅዱስ ጊዮርጊስ አያሰጋም?

ምንተስኖት፡- ትልቅ የቤት ሥራ ይጠብቀናል አሁን ያለው እውነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ሻምፒዮን ሲሆን እንደነበረው ጊዜ አይደለም… ጠንካራ ቡድኖች ተፈጥረዋል ሁሉም ቡድኖች ዋንጫ መውሰድ ይቻላል የሚል እምነት ውስጥ ገብተዋልና ፉክክሩን ጠንካራ አድርጎታል፡፡ አሁንም ቢሆን ጥሩ የተጨዋቾች ስብስብ አለን ጥራት ያለው እኛ ጋር ነው እንደቡድን ለመጫወት የተሻለ ስራ ይጠበቅብናል እንጂ ክፍተት ባለው ቦታ ላይ ማስተካከያ ከተደረገበት ጥሩ ቡድን እንደምንሆን አልጠራጠርም የሚታወቀውን ኃያልነት ለመመለስ እንቸገራለን ብዬም አልሰጋም፡፡

ሀትሪክ፡- ከውጪ ሀገር አሰልጣኝ ይልቅ ኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ ይሻላል የሚሉ ወገኖች አሉ ትስማማለህ…?

ምንተስኖት፡-የውጪ አሰልጣኝ ችግር ነው ብዬ አላምንም በክለብ ደረጃ የተጫወትኩት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ ነው፤ በጊዮርጊስ ማሊያ የሰለጠንኩት በውጪ አሰልጣኝ ብቻ ነው… በውጪ አሰልጣኞች ዋንጫ አምጥተንም እናውቃለን ራሣቸውን በሚገባ ያሳዩ የውጪ አገር አሰልጣኞች አሉኮ… ችግሩ የእነሱ ነው ብዬ አላምንም ከወቅታዊ ደካማ አቋማችን ጋር ተያይዞ እንጂ በነጮቹ አሰልጣኞች ውጤት አምጥተናል፡፡ በውጪ አሰልጣኞችም ዋንጫ አይወሰድም ብዬም አላምንም… የትኛው የተሻለ ይጠቅማል የሚለውን የሚያውቀው ደግሞ ክለቡ ይመስለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ቀጣይ ጨዋታ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ነው ሀዲያ ሆሳዕና በወቅታዊ አቋሙ ደካማ ነው እየተባለ ነውና ከጨዋታው…3 ነጥብ አይገኝም?

ምንተስኖት፡- ጨዋታው ይቀለናል ብዬ አልጠብቅም ኢትዮጵያ ውስጥ የተጨዋች ልዩነት አለ ብዬ አላምንም ሁሉም ተጨዋች አንድ ነው ሠፈር ውስጥ ያለው፣ ታዳጊ ነው የሚባለው ሲኒየር የሚባለው ጭምር በሙሉ ልዩነቱ ልምዱ ብቻ ይመስለኛል ኢትዮጵያ ውስጥ ከሳላሀዲን ሰይድ ውጪ ሁሉም ተጨዋች እንደ ቻይና ህዝብ ተመሳሳይ ነው /ሳቅ/ እናም ልዩነት አለው ብዬ አላምንም ታዳጊዎች ቢሆኑም በትልቅ ተነሳሽነት ነው የሚገጥሙን… ራሣቸውን ለማሳየት ስለሚጥሩም ጨዋታው ይከብዳል ብዬ አምናለሁ፡፡ ወጣቶቹ ጉልበት አላቸው ከሰበታ ከተማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ጥሩ ተፎካክረው ባለቀ ሰዓት በተቆጠረ ግብ ነውና የተሸነፉት ቀላል ተጋጣሚ ናቸው ብለን አናስብም ነገር ግን 9 ነጥብ ስለሚያስፈልገን ይህን ጨዋታ ጨምሮ ሌሎቹን ሁለቱን ጨዋታዎች ማሸነፋችን የግድ ነው፡፡

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport