ከእኛና ከጠራናቸው እንግዶች በላይ እግዚአብሄር እንዲከብር ነበር የፈለግነው ደግሞም ተሳክቶልናል….”
“በጥሩ አቋም ለቀጣዮቹ አስር አመታት የመጫወት ብቃት አለኝ”
ምንተስኖት አዳነ/ቅዱስ ጊዮርጊስ/
ፈረሰኞቹ ባሳለፍናቸው ጥቂት ቀናቶች ስማቸው ከእግርኳስ ውጪ በሆነ ነገር ሲጠራ ሰምተናል….የቡድኑ ተጨዋቾች የሆኑት ምንተስኖት አዳነ ከወ/ሮ ኢትዮዽያ አቤል ያለውም ከወ/ሮ ጋር ባለፈው እሁድ ጋብቻቸውን መፈጸማቸው ትኩረት የሳበ ሆኗል…ተጨዋቾቹ ሃላፊነት መሸከም እንደሚችሉና ሃላፊነት መሸከም እንደማይፈሩም ያሳዩበት ተደርጎ ተወስዷል።
የሃትሪክ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ሁለቱንም ተጨዋቾች ቃለ ምልልስ ለመስራት ፈልጎ ወደ ሁለቱ ተጨዋቾች የግል ስልክ ይደውላል በተደጋጋሚ ጊዜ ቢደወልም መልእክት ቢላክም አቤል ያለው ምላሽ ሳይሰጥ በመቅረቱ ልናገኘው አልቻልንም ነገር ግን ምንተስኖት አዳነ በወቅቱ ቤተሰባዊ ፕሮግራም ቢኖረውም ጊዜውን አጣቦ ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር ያደረገው አጠር ያለ ቆይታ የሚከተለውን ይመስላል። በዚህ አጋጣሚ የዝግጅት ክፍሉ ለሁለቱም ተጨዋቾች መልካም ጋብቻ እንዲሆንላቸው ይመኛል።
- ማሰታውቂያ -
ሀትሪክ:- ሀገራችን ኢትዮዽያ እንዴት ናት?
ምንተስኖት:- /ሳቅ በሳቅ/ ሀገሬና ባለቤቴን የሚመለከት ጥምር ጥያቄ ነው/ሳቅ/ በጣም ደህና ናቸው….የኔ ኢትዮዽያም ደህና ናት
ሀትሪክ:- ኢትዮዽያ ለሚለው ስም ያለህ ስሜትስ ምን ይመስላል?
ምንተስኖት:- ስሙ የሚወደድ ስም ነው። እንደ ሀገርም ኢትዮዽያን እወዳለሁ ሀገሩን የማይወድ ሰው የለም የምወዳት የባለቤቴና የሀገሬ ስም መመሳሰሉ ደግሞ ትልቅ ደስታ ይፈጥራል
ሀትሪክ:- ትዳር መስርተሃል..እንዴት አገኘኽው?
ምንተስኖት:- ትዳር ከመሰረትኩ ገና አራት ቀኑ ነው/ቃለ ምልልሱን የሰራነው ሀሙስ እለት ነው/ በአራቱ ቀን ባየሁት አሪፍ ነው አሁንም ገና ከሰርጉ ቀን ስሜት አልተላቀቅንም በራሳችን ጊዜ ላይም አይደለንም አሁንም ከበባ አለው…/ሳቅ/

ሀትሪክ:- ባለትዳር የሚለውን ከጋብቻ በፊትና በኋላ ያለውን ትርጉም እንዴት ትገልጸዋለህ?
ምንተስኖት:- ትልቅ ልዩነት አለው ከጋብቻ በፊት ሁሉ ነገር ራስ ተኮር ብቻ ነበር አሁን ካገባሁ በኋላ ግን ለብቻዬ አልችልም ከሰው ጋር የመኖር ጉዳይ ይሆናል.. ባለቤትህን ታሳቢ አድርገህ ነው የምትጓዘው ፕሮግራምህ የግል አይሆንም በጊዜ መግባት ካለብህ ትገባለህ ወጣ ማለት ብፈልግ ከባለቤቴ ጋር ተነጋግሬ ነው እናም ባለ ትዳር ሲኮን ለብቻህ አይደለም አብረህ የምትኖርለት ሰው አለ..ያ ለውጥ ግን ያስደስታል.
ሀትሪክ:- የሰርግህ እለት ምን ተሰማህ? እንዴትስ አለፈ?
ምንተስኖት:- አሪፍ ጊዜ ነበር ትንሽ ሰው ነው የተጠራው.. ቤተሰቦቻችንና የቅርብ የምንላቸውን እንግዶች ብቻ ነበር የጠራነው… ፕሮግራሙ መንፈሳዊ ይዘቱን ሳይለቅ እንዲሄድ ነበር የፈለግነው… በዚህ መንገድ እንዲካሄድ ስንወስን ፈተና ነበረው..ሰርግ ተሰርጎ መጠጥ እንዴት አይኖርም በሚል ቅሬታ ተነስቶ ነበር…ሁለታችንም ግን ጠንካራ አቋም በመያዛችን፣ እግዚአብሄር እንዲከብር በመፈለጋችን፣ የምንከተለው እምነት አስተምሮ ይህን ስለሚደግፍ የምንፈልገውን አድርገናል እግዜር ይመስገን ከፕሮግራሙ በኋላ የነበረው ሰዉ ሁሉ መደሰቱን ብዙ ነገር መማሩን ገልጾልናል…በዚህም ደስ ብሎናል..ከእኛና ከጠራናቸው እንግዶች በላይ እግዚአብሄር እንዲከብር ነበር የፈለግነው ደግሞም ተሳክቶልናል….
ሀትሪክ:- በሰርጉ እለት የቅዱስ ጊዮርጊስ የቦርድ ፕሬዚዳንት አቶ አብነት ገ/ መስቀል ተገኝተዋል የከለቡ አመራሮችና ተጨዋቾቹ ስለ ስነምግባርህ ምስክርነት ሲሰጡህ ምን ተሰማህ?
ምንተስኖት:- በጣም ደስ ብሎኛል…ያው እንደሚታወቀው ስላንተ ከቤተሰብ በላይ ማንም ምስክርነት መስጠት አይችልም…. ለ13 አመታት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ግልጋሎት ሰጥቻለሁ.. ቅዱስ ጊዮርጊስም ታዳጊ ሆኜ ወጣት የሆንኩበት ወደ ጎልማሳነትም የተጓዝኩበት ክለብ ነው ሌላኛው ቤተሰቤ ነው ማለት እችላለሁ የሚያውቁትን በመመስከራቸው ደስ ብሎኛል..ሁሉንም አመሰግናለሁ..
ሀትሪክ:- ትዳር መያዝህ ሀላፊነት ጨምሮብሃል?
ምንተስኖት:- /ሳቅ/ አዎ ምንም ጥያቄ የለውም ትዳር ሃላፊነት ይጨምራል..እኔ ግን ከትዳር መያዜ በፊት ነው ሃላፊነቱን እየተወጣሁ ያለሁት/ሳቅ/ በተለይ ትዳር ላይ መኖር የለባቸውም የሚባሉት ደባል ነገሮች ስለሌሉብኝ ቀለል ባለ መልኩ ሀላፊነቴን እየተወጣሁ ነው… አስቀድሜም ግን የቤተሰብ ሰው ስለሆንኩ ሀላፊነቱ አልከበደኝም
ሀትሪክ:- ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለህ ግንኙነት ምን ይመስላል?
ምንተስኖት:- አሁን በሰርጌ ደስታ ውስጥ ነኝ ስለዚህ አይነቱ ጉዳይ ማሰብ አልጀመርኩም ምናልባት ከሰኞ በኋላ ነው ስለጉዳዩ መንቀሳቀስ የምፈልገው.. ቀጣዮቹ ቀናቶች የሚያሳውቁን ነገር ይኖራል…

ሀትሪክ:- አሁን ቅዱስ ጊዮርጊስና ምንተስኖት ተለያይተዋል ማለት ይቻላል?
ምንተስኖት:- አሁን ላይ ምንም ማለት አልችልም..እቀጥላለሁ አልቀጥልም የማውቀው ነገር የለም ቀጣዮቹ ቀናቶች የሚያመጧቸው ነገሮች ይኖራሉ ብዙ የጨዋታ አመታቶች እንዳሉኝ ግን ተስፋ አደርጋለሁ ከውሳኔ በፊት ግን ከባለቤቴና ከቤተሰቤ ጋር ቁጭ ብዬ መምከር አለብኝ
ሀትሪክ:- ስንት የተጨዋችነት አመታቶች ይኖሩኛል ብለህ ታምናለህ?
ምንተስኖት:- ቀድሞ የመታወቁ ነገር ካላስረጀኝ በስተቀር በጥሩ አቋም ለቀጣዮቹ አስር አመታት የመጫወት ብቃት አለኝ ። አንድ የማውቀው ታሪክ ልንገርህ.. ልጁ ብዙ ባይታወቅም ልጅ ሆነን ስናድግ እያጨበጨብንለት ኳስ ሲጫወት የምናውቀው ልጅ በስመ ወጣት ነው አሁን እየተጫወተ ያለው..ይሄ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር አሁን ወደ ሃያዎቹ መጨረሻ ላይ ነው የምገኘው ይሄ እድሜ ደግሞ በብቃት ለመጫወት የሚያስችል ነው..
ሀትሪክ:- በቀጣይ የት ልናገኝህ እንችላለን?
ምንተስኖት:- የመጫወት አቅም እንዳለኝ ብቻ ነው የማውቀው… በቅርብ ጊዜ ውስጥ ግን ሁሉም ነገር ሊታወቅ እንደሚችል እንጂ አሁን መልስ የለኝም/ሳቅ/
ሀትሪክ:- ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የምትለው ነገር አለ?
ምንተስኖት:- ትልቅ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ ከወጣትነቴ ጀምሮ ለነበራቸው ድጋፍ ከልብ አመሰግናለሁ በዚሁ አጋጣሚ ከጊዮርጊስ ውጪ ያሉ የሌላ ክለብ ደጋፊዎችም መንገድ ላይ ሲያገኙኝ የሚሰጡኝ አክብሮትና አድናቆት አስደስቶኛል እነሱንም አመሰግናለሁ
ሀትሪክ:- የመጨረሻ ምስጋና ካለህ…?
ምንተስኖት:- የነገሮቼ ጀማሪና ፈጻሚ የሆነውን ልዑል እግዚአብሄርን ከልብ አመሰግናለሁ…መላው ቤተሰቦቼን፣ ውዷ ባለቤቴን፣ ሚዜዎቼን ያገዙኝን ጓደኞቼንም ከልብ አመሰግናለሁ.. ወንድሜ ዮናስ አዳነንም ከልብ አመሰግናለሁ ሁሉ ነገሮች መስመር እንዲይዝ በተለይ የዚህ አይነት የማስተባበር ነገሮችን ቦታ ቦታቸውን እንዲይዙ የማድረግ አቅም የለኝም ሰርግ ቦታ እንኳን ብዙ ጊዜ የምሄድ አይነት ሰው አይደለሁምና ይህን ክፍተት ተረድቶ ሁሉ ነገር ላይ ገብቶ ሀላፊነቱን በሚገባ ተወጥቷልና ከልብ አመሰግናለሁ…


