“ለብሔራዊ ቡድን መመረጤ ደስታዬን እጥፍ ድርብ አድርጎታል”
“በአፍሪካ ዋንጫው በተደለደልንበት ምድብ ልንሰጋም ልንፈራም አይገባም”
መናፍ አወል /ባህርዳር ከተማ/
ወጣቱ እግር ኳስ ተጨዋች መናፍ አወል ይባላል፤ በአዳማ ከተማ በተለምዶ አጠራር 09 ቀበሌ ውስጥ ነው ተወልዶ ያደገው፤ እግር ኳስን በፕሮጀክት ደረጃ መጫወት በመጀመር ዛሬ ላይ ለሀገሩ ብሔራዊ ቡድን እስከመመረጥ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ ይህ የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች ከዚህ በኋላ በሚኖረው የኳስ ህይወቱ ደግሞ እልምና ግቡ ወደ ውጪ ሀገር በመውጣት በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት መጫወት መሆኑን ከሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ከሆነው ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር ባደረገው ቆይታ ሀሳቡን ገልጿል፡፡
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ ተሳትፎው በባህርዳር ከተማ ክለብ ውስጥ በነበረው ቆይታና ዕድሜያቸው ከ23 ዓመት በታች ለሆናቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከተመረጠም በኋላ በሜዳ ላይ ያሳይ በነበረው አበረታችና ጥሩ እንቅስቃሴ የዋልያዎቹን ስብስብ ለመቀላቀል የቻለው መናፍ አወልን ከኳስ አጀማመሩ ጊዜ አንስቶ አሁን እስከ ደረሰበት ደረጃ አናግረነው የሰጠን ምላሽ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
- ማሰታውቂያ -
ስለ ኳስ ጅማሬው
“በተወለድኩበትና ባደግኩበት አዳማ ከተማ ውስጥ ነው ሮያል በሚባል የፕሮጀክት ቡድን ውስጥ ኳስን መጫወት የጀመርኩት፤ አሰልጣኛችንም ምስጋናው ይባል ነበር፤ ጥሩ ልምምድ ያሰራን ነበር፤ ከዛም ወደ ሌሎች ፕሮጀክቶች ሄድኩና ተጫወትኩ፤ ከዛም አዳማ ከተማ የተተኪ ቡድን ምርጫን ያደርግ ስለነበር እዛ ሙከራ አድርጌ ለቡድኑ ተመረጥኩ፤ የእኔ የኳስ አጀማመር ይህንንም ነው የሚመስለው”፡፡
ኳስን ከመጫወት ጋር በተያያዘ ቤተሰብ ጋር ስለነበረው አመለካከትና ከእሱ ውጪ ሌላ ስፖርተኛ ያለ እንደሆነ
“እኛ ቤተሰብ ውስጥ ስፖርተኛ እኔ ብቻ አይደለውም፤ ሁለት ወንድሞችና ሁለት እህቶች አሉኝ፤ ከእነሱ ውስጥ ታላቅ ወንድሜ ሚፍታህ አወል በመድን ክለብ ውስጥ ኳስን እየተጫወተ ይገኛል፤ ሌላኛው ወንድሜ አብድበር ደግሞ ለዱከም ከተማ በመጫወት ቡድኑን ወደ ብሔራዊ ሊግ እንዲገባ ካደረጉት ተጨዋቾች መካከል አንዱ ሆኗልና የእኛ ቤተሰብ በኳስ ተጨዋቾች እየተሞላ ይገኛል፤ ኳስን ከመጫወት ጋር በተያያዘ ልጅ በነበርኩበት ሰዓት እንዳልጫወት እከለከል ነበር፤ ለትምህርትም ትኩረት ስጥ እባልም ነበር፤ ግን የታላቅ ወንድሜ ኳስ ተጨዋች መሆንና እኔም የእሱን መንገድ የተከተልኩበት ሁኔታና ለኳስ ያለኝ ከፍተኛ ፍቅር ለቤተሰቦቼ ከአቅም በላይ ስለሆነባቸው መጫወቱን ቀጠልኩበትና መከልከሉን እንዲያቆሙ አደረግኩኝ፤ አሁን ላይ እነሱ ለእኔ ጥሩ ድጋፍን የሚያደርጉልኛ ናቸው፤ በዚህ አመሰግናቸዋለው”፡፡
በእግር ኳስ አርአያ ስላደረገው ተጨዋች
“መጀመሪያ ወንድሜ ሚፍታህን ነው ተምሳሌቴ ያደረግኩት፤ ከዛ ደግሞ የባህርማዶ ኳስን በደንብ እከታተል ስለነበር የሪያል ማድሪዱን ሰርጂዮ ራሞስን በማድነቅ አድጌያለው፤ ራሞስ አሁን ወደ ፒ. ኤስ. ጂ በማምራቱም የእነሱ ደጋፊም ሆኛለው”፡፡
ወደ እግር ኳሱ በተከላካይ ስፍራ ብቻ ተጫውተህ ነው የመጣከው….?
“አይደለም፤ ልጅ በነበርኩበት ሰዓት የአጥቂ ስፍራ ተጨዋችም ነበርኩ፤ ከዛም ነው በተከላካይነትም በመጫወት ወደ ኳሱ የመጣሁት”፡፡
የመጀመሪያ ክለቡ በሆነው አዳማ ከተማ ውስጥ ስለነበረው የተጨዋችነት ዘመን ቆይታውና ስለ ቡድኑ
“አዳማ ከተማ ለእኔ የመጀመሪያዬና አሁን ለደረስኩበትም ደረጃ ብዙ ነገርን ያደረገልኝ የምወደው ቡድኔ ነው፤ እዚሁም ነው ከታችኛው ቡድን አንስቶም በማደግ እስከ ዋናው ቡድን ደረጃም ልጫወት የቻልኩት፤ በዚህ ክለብ በነበረኝ ቆይታዬም ወጣት ከመሆኔ አንፃር መጀመሪያ ላይ ለክለቡ ልጫወት ባልችልም አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ወደ ቡድኑ ከመጣ በኋላ ግን የመጫወት እድሉን አገኘውና በክለቡ ጥሩ ጊዜን በማሳለፌ ባህርዳሮች ወሰዱኝና ለክለቡ ሊያጫውቱኝ ቻሉ”፡፡
ከአዳማ ከተማ ተለያይቶ ወደ ባህርዳር ከተማ ስላመራበት መንገድ
“አዳማዎች ለእኔ ጥሩ ነገር እንደነበራቸው እውቅ ነበር፤ ያም ሆኖ ግን የውል ጊዜዬን ባጠናቀቅኩበት ወቅት በአንድ አንድ ነገሮች ላይ ከክለቡ ጋር ልንስማማ ስላልቻልን ፈላጊ ክለቤ ወደ ሆነው ባህርዳር አምርቼ እየተጫወትኩ እገኛለው”፡፡
በባህርዳር ከተማ ውስጥ ስላለው የቡድኑ ቆይታና ዘንድሮ በቤትኪንጉ ስላስመዘገቡት ውጤት
“በዚህ ቡድን ቆይታዬ ጥሩ ጊዜን ነው እያሳለፍኩ የምገኘው፤ ጥሩ የውድድር ጊዜን በማሳለፌም ለብሔራዊ ቡድን ተጨዋችነት እስከመመረጥ ደረጃም ላይ ደርሻለው፤ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝም የሚሰጠን ልምምድ ጥሩ ስለነበርም አበረታች የሚባል ውጤትን እያስመዘገብንም ነበር፤ በአቋም ደረጃም ቢሆን እኔ በራሴ ላይ ብዙ ለውጦችን ያየሁበት ነበርና ቆይታዬን ወድጄዋለው፤ ከክለባችን ውጤት ጋር በተያያዘ እኛ ያስመዘገብነው ውጤት መጥፎ የሚባል አይደለም፤ ውጤቱ ጥሩ ነው፤ የልምድ ማነስና ጥቃቅን ችግሮች ብቻ ነው ያስቸገሩን፤ ያ ባይሆን ካስመዘገብነው ውጤት በተሻለ መልኩ ወደፊት እንጓዝም ነበር”፡፡
ፋሲል ከነማ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ዘንድሮ ስላሳከው ውጤትና ስለ አቡበከር ናስር የጣምራ ኮከብነት
“ፋሲል ከነማ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ያሸነፈው ከሁሉም ቡድኖች በተሻለ መልኩ የውድድር ጊዜያቶቹን ስላሳለፈ ነው፤ ጠንካራ ቡድን ነበራቸው ያም ለውጤት አብቅቷቸዋልና ድሉ ይገባቸዋል፤ የኢትዮጵያ ቡናው አቡኪም ዘንድሮ ልዩ ነበር፤ ምርጥ ብቃቱን አውጥቶ ተጫውቷል፤ ያገኘው የኮከብነት ክብርም ሲያንሰው እንጂ የሚበዛበት አይደለም”፡፡
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የመጪው ዓመት ተሳትፎው ራሱን በምን መልኩ እንደሚያቀርብ
“በባህርዳር ቆይታዬ ዘንድሮ ጥሩ የውድድር ጊዜን አሳልፌያለው፤ የመጪው ዘመን ተሳትፎዬ ላይም ከአሁን በበለጠ የምሄድበት ጉዞዬ ከውጤት ጋር የታጀበ እንዲሆን ስለምፈልግ ለዛ ከውስጤ ያላወጣሁትን አቅሜን ሳልሳስት አውጥቼ በመጫወት ቡድኑን ለጥሩ ውጤት ለማብቃት የምዘጋጅ ነው የምሆነው”፡፡
ከጋና ጋር ላለብን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅት እያደረጋችሁ ይገኛል፤ የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ድልድል ደግሞ ወጥቷል፤ ሀገራችን ከካሜሩን፣ ከቡርኪናፋሶና ከኬፕቨርዴ ጋር ደርሷታል፤ በዚህ ዙሪያ ምን ትላለህ?
“ጋናን ለምንፋለምበት የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ እያደረግን የምንገኘው ዝግጅት በጣም ጥሩ ነው፤ ከኳስ ጋር የተያያዘ ጥሩ ልምምድ እየተሰጠንም ነው ያለው፤ የቡድናችን መንፈስ መልካም የሚባልም ነውና ከዚህ በኋላ የምንጠባበቀው ነገር ቢኖር ልምምዳችንን አጠናክረን በማስቀጠል የጨዋታውን መዳረሻ ቀን መጠበቅ ነው፤ በአፍሪካ ዋንጫ የወጣልንን የምድብ ድልድል በተመለከተ ከሌሎቹ አንፃር ማክበድ አያስፈልገንም፤ ከማንም ጋር ብንደለደል ምንም የሚያስፈራን ነገር የለም፤ የምንጫወተው ኳስ ነው፤ በተደለደልንበት ምድብ ልንሰጋም ልንፈራም አይገባም፤ ዋናው ነገር የእኛ ጥሩ መሆን ብቻ ስለሆነ ጠንካራ ዝግጅትን አድርገን ወደ ውድድሩ በመጓዝ መልካም የሚባል ውጤትን ለማስመዝገብ ልንጥር ነው የሚገባን”፡፡
ለብሔራዊ ቡድን በመመረጡ ስለተሰማው ስሜት
“ሀገርን በሚወክል ደረጃ ለብሔራዊ ቡድን ስትመረጥ ያለው ስሜት በጣም ደስ ይላል፤ እኔም ይህን እድል መጀመሪያ ላይ እድሜያቸው ከ23 ዓመት በታች ለሆናቸው ቡድን ተመርጬ ሳገኝ የነበረኝ ደስታ ከፍ ያለ ነበር፤ እዛም መጀመሪያ ላይ ከኤርትራ ቀጥሎም ከቡሩንዲ ጋር በነበሩት ጨዋታዎች ላይ ልጫወት ስችል የተሰማኝ የደስታ ስሜት ለየት ይል ነበር፤ አሁን ላይ ደግሞ በእዛ የውድድር ተሳትፎ ላይ ባሳየሁት ብቃት በአሰልጣኝ ውበቱ አማካኝነት የመመረጥ ዕድሉና በማግኘቴ ደስታዬን ይበልጥ እጥፍ ድርብ አድርጎልኛልና የተሰጠኝን ሀላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ጥረትን አድርጋለው፤ ሀገሬንም በጥሩ ሁኔታ እጠቅማታለው”፡፡
ከማጠቃለላችን በፊት ቃለ-ምልልሱን በአንድ ነገር ብትዘጋው
“ይቻላል፤ በኳሱ ደረጃዬ ዛሬ ላይ እኔ ገና ሙሉ ተጨዋች አልሆንኩም የሚቀሩኝ ነገሮች አሉ፤ በጣም ስመ ጥር ተጨዋች ለመሆንና ከሀገር ወጥቶ ለመጫወትም ከዚህ በኋላ ብዙ መልፋት ይጠበቅብኛልና ለዛ ራሴን እየተዘጋጀውኝ ነው፤ ይህን ካልኩ በዚህ ሀሳቤን ልቋጭ እስከአሁን እዚህ ደረጃ ላይ እንድደርስ ፈጣሪዬ ዓላ ትልቁን ድርሻ ይወስዳልና እሱን አመሰገንኩ፤ ሲቀጥል ቤተሰቦቼን፣ በአዳማ ከተማ ክለብ ውስጥ ከስር ባደግኩበት ወቅት የመጫወት እድሉን የሰጠኝ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን፤ በባህርዳር ከተማ ጥሩ ጊዜ እንዳሳልፍ ያደረገኝን ፋሲል ተካልኝንና በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ለተስፋ ቡድኑም ሆነ ለዋናው ብሔራዊ ቡድን የመረጠኝን አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ጨምሮ የማመሰግናቸው ናቸው”፡፡