“ከባስኬት ቦል ተጨዋችነት ተመልምዬ ነው ግብ ጠባቂ የሆንኩት”
“በባህርዳር ከተማ ክለብ ቆይታዬ የተሳካ ጊዜን አሳልፋለው”
ፋሲል ገ/ሚካሄል /ባህርዳር ከተማ/
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን /ዕድሜያቸው ከ23 ዓመት በታች/ ለሆናቸው በሴካፋ ውድድር ላይ በግብ ጠባቂነት ተመርጦ ተጫውቷል፤ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ላይ ደግሞ በሰበታ ከተማ ክለብ ውስጥ ጥሩ የውድድር ጊዜን ካሳለፈ በኋላ በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ለባህርዳር ከተማ ፊርማውን በማኖር አዲሱ ክለቡን ተቀላቅሏል፤ ከዚሁ ግብ ጠባቂ ፋሲል ገ/ሚካሄል ጋር የሀትሪክ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ በኳስ ህይወቱ ዙሪያና በዝውውር መስከቱ ወደ ባህርዳር ስለማምራቱ እንደዚሁም በሴካፋ ተሳትፎአቸው ዙሪያ አጠር ባለ መልኩ አናግረነው የሰጠንን ምላሽ በሚከተለው መልኩ ለእናንተ ውድ አንባቢዎቻችን አቅርበንላችኋል፡፡
ስለ ውልደቱ፣ እድገቱና ኳስ አጀማመሩ
“በጎንደር ከተማ ቀበሌ 04 ውስጥ ነው ተወልጄ ያደግኩት፤ በእዛም አካባቢ ነው ኳስንም ባስኬት ቦልንም ከልጅነት ዕድሜዬ አንስቶም በመጫወት የጀመርኩት፤ ያኔ ኳሱን ስጫወትም በቤተሰብ ዘንድ ፈቃድን ካለማግኘት ጋር በተያያዘና ለትምህርቴም ትኩረትን እንድሰጥ ስለሚፈለግ ከቤት እንዳልወጣ ሁሉ እከለከል ነበር፤ በኋላ ግን ሊፈቀድልኝ ችሎ መጫወቱን ቀጠልኩ”፡፡
በቤተሰቡ ውስጥ ስፖርተኛው እሱ ብቻ እንደሆነ
“አምስት ወንድሞችና ሁለት እህቶች ናቸው ያሉኝ፤ ከእነዛ ውስጥ ሰለሞን ገብረ ሚካሄል እንደ እኔው ግብ ጠባቂ ነበር፤ ሌላው በአሜሪካ ሀገር የሚገኘው ወንድማችን አበበ ገ/ሚካሄል ደግሞ በፋሲል ከነማ ክለብ ውስጥ ተጨዋቾችን ከማስፈረም አንስቶ በኮሚቴ ውስጥ ይሰራ ስለነበር በስፖርት ውስጥ ያለፈ ቤተሰብ ነው ያለን”፡፡

ወደ ክለብ ተጨዋችነት ስለመጣበት መንገድ
“ከእግር ኳሱ በፊት መጀመሪያ ላይ ባስኬት ቦልን ነበር በደብረሰላም በትምህርት ቤት ውስጥ በፕሮጀክት ደረጃ ስሰለጥንና ስጫወት የነበረው፤ መረብ ኳስንም እጫወት ነበር፤ አዘላለሌም የሚገርም ነበር፤ ከዛም በተለይ በባስኬት ቦሉ ላይ የምጫወትበት ቡድን ዋንጫ ሲያነሳና እኔም ኮከብ ተጨዋች ተብዬ ስሸለም በጊዜው ወደ ፕሪምየር ሊጉ ገብቶ የነበረው የዳሽን ቢራ እግር ኳስ ቡድን ከባስኬት ቦል ተጨዋችነት እኔን በክለቡ አመራር አቶ ተገኜ እቁባይ አማካኝነት በማምጣት ለታዳጊው ቡድን በግብ ጠባቂነት እንድጫወት አደረጉኝና ወልዲያ ላይ በተደረገው ውድድር የእኛ ቡድን ሻምፒዮና ሆኖ እኔም በኮከብ ግብ ጠባቂነት ተመርጬ 1ሺ ብርና ዋንጫን በተሸለምኩበት ሰዓት ከአንድ ዓመት የታዳጊ ቡድን ቆይታዬ በኋላ ነው ወደ ዋናው ቡድን አድጌ ወደ ግብ ጠባቂነቱ ልመጣና ወደ ክለብ ተጨዋችነትም ልዘልቅ የቻልኩት”፡፡
ሌሎች የተጫወተባቸው ክለቦች
“ወደ መጀመሪያ ክለቤ የዳሽን ቢራ ዋናው ቡድን ካደግኩኝና ለመጫወት ከቻልኩ በኋላ ቡድኑ ፕሪምየር ሊግ በገባበት ዓመት ላይ ሲፈርስ እኔ በቀጥታ ያመራሁት በወቅቱ ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ለሆነው የታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ከእነ አቡበከር ናስር፣ ጫላ ተሺታና ከመሳሰሉት ተጨዋቾች ጋር ተመርጬ ስለነበር እዛ ባሳየሁት ብቃት ጭምር ነው ወደ ቀጣዮቹ ቡድኖች ውስጥ ገብቼ ልጫወት የቻልኩት፤ እነሱም ደደቢት በመቀጠል ደግሞ የከፍተኛ ሊግ ተወዳዳሪ ለነበረው አክሱም ከተማ ካመራው በኋላ በአሰልጣኝ ውበቱ አማካኝነት እሱ ፋሲል ከነማ በነበረበት ሰዓት ስሜን ለቡድኑ ሊያስተላልፍ ቢችልም እሱ ከእነሱ ጋር በመለያየቱና ግዙፍ የሆነ ዜጋ በረኛንም ስላስመጡ ወደ ሰበታ ከተማ እንድመጣ ካደረገኝ በኋላ ነው ለሰበታ ከተማ የሊጉ ውድድር በኮቪድ የተነሳ ዓምና ከተቋረጠበት ጊዜ አንስቶ በጥሩ መልኩ ተጫውቼ አሁን ደግሞ አዲሱን ቡድኔን ባህርዳር ከተማን ለመቀላቀል የቻልኩት”፡፡

ለባህርዳር ከተማ ፊርማውን ስለማኖሩ
“በሰበታ ከተማ በነበረኝ የተጨዋችነት ቆይታዬ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ስርም ሆነ በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ስር ጥሩ የውድድር ጊዜን አሳልፌያለው፤ ከቡድኑ ጋር ውሌን እንዳጠናቀቅኩም ባህርዳርን አብርሃም ሊይዘው ስለቻለና በእሱም ከኳስ ጋር በተያያዘ ስልጠና አቅሜን የበለጠ ማጎልበት እፈልጋለውና ለዛም ነው ቡድኑን የመጀመሪያዬ ምርጫ በማድረግ ፊርማዬን ለማኖር የቻልኩት”፡፡
እያሳለፍክ ባለው የኳስ ህይወት ደስተኛ ነህ?
“በጣም፤ ምክንያቱም ገና በወጣትነት ዕድሜዬ ተጫውቼ ላሳለፍኩባቸው ክለቦች ተደጋጋሚ የመሰለፍ እድልን አግኝቼያለውና፤ ከሁሉም ባሻገር ደግሞ የአብዛኛው እግር ኳስ ተጨዋች ትልቅ እልም በሆነው ሀገርን ወክለህ ለምትጫወትበት ብሔራዊ ቡድን ደረጃም ማሊያውን ለብሼ ስለተጫወትኩ ከዚህ ውጪ ምን እድለኝነት አለ፤ ወደፊትም ደግሞ የዋናውን ብሔራዊ ቡድን መለያም መልበሴ አይቀርምና በኳስ ህይወቴ ደስተኛ ሆኜ ነው እያሳለፍኩ ያለሁት”፡፡

በሰበታ ከተማ በነበረህ ቆይታ ቤትኪንግ ተሳትፎአችሁን በተመለከተ
“ከኢትዮጵያ ቡና ቀጥሎ በኳስ ቁጥጥሩ ጥሩ የነበርነው እኛ ነበርን፤ በቡናም ብቻ ነበር በእንቅስቃሴ የተበለጥነው፤ ቡድናችን ላይ ክፍተቶች ቢኖሩም በቶፕ አምስት ውስጥ ሊጉን ማጠናቀቃችን መልካም የሚባል ውጤት ነው”፡፡
በመጨረሻ….
“በእግር ኳሱ እስካሁን ለመጣሁበት መንገድ ቅድሚያ ፈጣሪዬንና ቤተሰቦቼን አመሰግናለው፤ በተለይ ወንድሜ ሰለሞን ባሉኝ ክፍተት ቦታዎች ላይ ብዙ ነገሮችን እየነገረኝ ራሴን እንዳሻሽል አድርጎኛል፤ ሌላው በአሜሪካ የሚገኘው ወንድሜም ተጠቃሽ ነው፤ ከእነሱ ውጪም የብሔራዊ ቡድናችን አሰልጣኝ ውበቱ አባተና ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እንደዚሁም በፕሮጀክት ከባስኬት ቦል ወደ እግር ኳስ እንድመጣና እንድጫወት ያደረጉኝ አቶ ተገኜ እቁባይ እንደዚሁም ደግሞ የግብ ጠባቂ አሰልጣኜ ሆኖ ከእኔ ጋር ብዙ የሰራውን አዳሙ ኑመሮን ላመሰግናቸው እፈልጋለው”፡፡
አስተያየት ይስጡ