“ኢት.ቡናን የለቀኩት በቤተሰብ ችግር እንጂ በገንዘብ አይደለም ወደ ቤቴም በመመለሴ ደስ ብሎኛል” በረከት አማረ/ኢት.ቡና/

ሀትሪክ:- እንኳን ወደ ቤትህ ተመለስክ ነው የሚባለው..?

በረከት:- /ሳቅ/ የምወደውን ክለብ በመቀላቀሌ በጣም ደስ ብሎኛል አምና የሄድኩት አባቴ በማረፉ ሀዘን ሆኖ የግድ የቤተሰብ ነገር ሆኖብኝ እንጂ ኢትዮዽያ ቡናን መልቀቅ አልፈለኩም ነበር..ዳግም ይህን እድል ስላገኘሁ ግን ተደስቻለሁ

ሀትሪክ:- ዝውውሩ ፈጠነ..ምናለባት በሁለታችሁም መሃል መፈላለጉ ስለነበር ይሆን?

በረከት:- በሁለታችንም መሃል ፍላጎቱ ስለነበር ነው የቀለለው በደንብ ነው የተፈላለግነው..በዚህም ደስ ብሎኛል

ሀትሪክ:- የተክለ ማርያም ሻንቆ/ጎሜዝ/ ተተኪ መሆን ሃላፊነቱን ከበድ አያደርገውም?

በረከት:- ደጋፊው ከሚፈልገው አንጻር የውጪው ጨዋታ ታክሎበት ጫና ሊኖረው ይችላል እንደምንም ጫናውን እንደምቋቋመው ግን ርግጠኛ ነኝ አምናም ክለቡ ውስጥ በመኖሬ እቸገራለሁ ብዬ አልሰጋም

ሀትሪክ:- በጅማ አባጅፋር የነበረህ ቆይታ ምን ይመስላል?

በረከት:- ከእረፍት ስለመጣሁ አሪፍ ነበር ቡድኑን ደግሞ ጠቅመነው ከመውረድ ተርፏል ያደረግነው ቆይታ ከደመወዝ ጋር እየተንገጫገጨ ቢሆንም በፕሪሚየር ሊጉ መቆየቱ አስደስቶኛል። በርግጥ ደመወዝ ላይ ያለው ሁኔታ ቅር ያሰኛል ሁሉ ተስተካክሎ ኳሱ ላይ ብቻ ማሰብ የግድ ነው እዚያ ግን ደመወዙ ጥቅማ ጥቅሙ ሲቀር ቅር ያሰኛል። ዋናው ማለፉ ቢሆንም ለቀጣዩ መሰራት እንዳለበት ያሳያል። ጅማ አባጅፋር ሲባል 2010 ላይ ዋንጫ የወሰደ ትልቅ ቡድን እንደመሆኑ ችግሮቹ ተወግደው የተሻለ ጊዜ እንዲመጣ እመኛለሁ…

ሀትሪክ:- ከአቤል ማሞ ጋር ለሚኖረው የቋሚ ተሰላፊነት ፍልሚያ ዝግጁ ነህ?

በረከት:- /ሳቅ/ ያው እግር ኳስ ላይ ያለ ነገር ነው..ጥሩ ሆኜ ለመገኘትና ለመሰለፍ እጥራለሁ ፉክክሩ ራሱ ለቡድኑ ትልቅ ጥቅም ይኖራል ብዬ አስባለሁ በሁለታችን መሃል ጤናማ ፉክክር እንደሚኖር ተስፋ አደርጋለሁ
ሀትሪክ:- ብዙ ጊዜ ለተሰላፊነት ያለው ፉክክር ጤናማ አይደለም ይባላል..እናንተ ጋርስ ይሄ ሊከሰት ይችላል?

በረከት:- /ሳቅ/ ተጠባባቂ ግብ ጠባቂ ቋሚ ተሰላፊ የመሆን እድሉ ጠባብ ነው..በቀይ ካርድ ወይም ጉዳት ካልሆነ በስተቀር ቋሚው የመቀየር እድሉ አናሳ ነው…ያም ሆኖ ኳስን በኳስ ባህሪ መያዝ ይኖርብናል ለክለቡ ድል የግብ ጠባቂው ጥሩ መሆንን ካልተመኘህ ተቀይሮ የገባው ላይሳካለት ይችላልና ተሳስቦ መኖር ይቀላል ባይ ነኝ እኔ ጋር ያለው ልብ አሪፍ ነው

ሀትሪክ:- የሀገር ውስጥ ግብ ጠባቂዎች ይመቹሃል?

በረከት:- ሁሉም ምርጥ ናቸው በግሌ ግብ ጠባቂ የሆንኩት አዲግራት ላይ እያየሁ ያደኩት የማነ የሚባል ግብ ጠባቂ ፈለግ ተከትዬ ነው የጀመርኩትና ሁሉም ለኔ አሪፍ ናቸው እነ አቤል ጎሜዝና እነ ጀማል ጥሩ የሚባሉ ናቸው በረኞቻችን ጎበዝ መሆናቸውን አውቃለሁ..

ሀትሪክ:- የውጪ በረኛ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ አልተከለከለም..በብሄራዊ ቡድን ላይ ተጽእኖ አይፈጥርም?

በረከት:- ተጽእኖውማ አይቀርም በደንብ ነው የሚፈጥረው ትልቁ ችግር ደግሞ በአቋምህ ብትበልጥም ቋሚ ሆኖ መሰለፉ ራሱ አጠራጣሪ ነው በልጠህም ቢሆን በብዙ ገንዘብ ስለሚገዟቸው እነሱን ቤንች ማድረግ ይከብዳቸዋል..ያ ደግሞ ሀገር ይጎዳል።ፌዴሬሽኑ ቢያየው ደስ ይለኛል

ሀትሪክ:- ኢትዮዽያ ቡና የገባኸው ካሳዬን ስለምትወድ ወይስ የቡና ወዳጅ ስለሆንክ?

በረከት:- ሁለቱም ይመስለኛል…ወልዋሎ አዲግራት እያለሁም ኢትዮዽያ ቡናን እወደው ነበር… አጋነንከው አትበሉኝ እንጂ ከቡና ጋር እየተጫወትኩ መዝሙራቸው ይመስጠኝና ኳሱን ትቼ ስለ ክለቡ የማስብበት ጊዜ ነበር ..ለዚህ ክለብ ምነው በተጫወትኩ ያሰኛል..በካሳዬ ስር ለመሰልጠን ስስማማና እድሉን ሳገኝ በይበልጥ ክለቡን ልወደው ችያለሁ…በካሳዬ ስር መሰልጠን ያስደስታል… ለሀገር የሚጠቅም ትልቅ ሃሳብ የያዘ አሰልጣኝ ስር መሰልጠኔ የበለጠ ቡናን እንድወድ አድርጎኛል ሁለቱንም ወድጄ ነው የመጣሁት…በሀዘን ምክንያት ቡናን መልቀቄ አሁን ድረስ ያበሳጫኛል…ኢት.ቡናን የለቀኩት በቤተሰብ ችግር እንጂ በገንዘብ አይደለም ወደ ቤቴም በመመለሴ ደስ ብሎኛል

ሀትሪክ:- በአውሮፓ የአንተን ልብ የያዙ ግብ ጠባቂዎች እነማን ናቸው…?

በረከት:- ሁለት በረኞችን በጣም እወዳቸዋለሁ እነሱም የባርሴሎናው ቴርስቴገንና የማን.ሲቲው ኤደርሰን ናቸው በጣም አደንቃቸዋለሁ

ሀትሪክ:- ምናልባት በእግርም መጫወት ስለምትወድ ይሆን? /በካሳዬ እምነት ግብ ጠባቂምኮ ተጨዋች ነው ይላል/

በረከት:- እውነት ነው ሲጀመር ራሱ በረኛ የሆንኩበት ምክንያት ግራ ይገባኛል..ኳስ ስጀምር ፕሮጀክትም ስጫወት አጥቂ ነበርኩ በእግር መጫወት በጣም እወዳለሁ..በርግጥ ግብ ጠባቂ ከሆንኩ በኋላ የገባኝ ቡድኔ የሚያጠቃው በበረኛ ነው ትርፍ ተጫዋቹ እርሱ ነውና…በረኛ በእጅ ብቻ ነው ብሎ ለሚያስብ የአሰልጣኝ ካሳዬም እምነት ትክክል ነው መታሰብ ያለበት ማጥቃትም ከበረኛ ይጀመራል

ሀትሪክ:- ለኢትዮዽያ ቡና ደጋፊዎች የምትለው ነገር ካለ…?

በረከት:- እግዚአብሄር ይመስገን በጥሩ ሁኔታ ተቀብለውኛልና አመሰግናለሁ አንዳንዶች በፊት በብር.ጉዳይ እንደወጣው አድርገው አስበዋል.. በፍጹም ግን ቡናን በብር ትቼ አልወጣሁም ይህን እንዲያውቁልኝ እፈልጋለሁ…ሌላው ቡና ሁለተኛ ሆኖ ማጠናቀቁ አሪፍ ነው ከእግዚአብሄር ጋር ለዋንጫ ለአንደኝነቱ የምንፋለምበት አመት እንደሚሆን አምናለሁ..ከአጨዋወቱ ጋር ተያይዞ አሪፍ ነገር የምናሳይም ይሆናል። ደጋፊው የሚደሰትበት አመት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ…ስለ አቀባበላችሁም አመሰግናለሁ…

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *