ለወልቂጤ ከተማ ክለብ ላለፉት ተከታታይ አመታቶች በመጫወት ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል፤ በተለይም ደግሞ በዘንድሮው ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮና ውድድር ላይ የበርካቶችን ትኩረት በመሳብም ለክለቡ በጥሩ መልኩ ሊንቀሳቀስ የቻለ ሲሆን ክለቡን ከወረደበት ሊግም በወራት ልዩነት ውስጥ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በሰጣቸው አንድ የውድደር እድል በመወዳደር ዳግሞ ወደነበሩበት ሊግም እንዲመለሱ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ከቡድን ጓደኞቹ ጋር ጥሩ አስተዋፅኦን ሊያደርግም ችሏል፡፡
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴን ካሳዩት ተጨዋቾች መካከል አንዱ የሆነው አብዱልከሪም ወርቁን በወልቂጤ ከተማ ውስጥ ስላሳለፈው የውድድር ጊዜና ሌሎችንም ጥያቄዎች ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ አቅርቦለት የሰጠው ምላሽ በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፤ ተከታተሉት፡፡
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ወርዶ የነበረው ወልቂጤ ከተማ በወራት ጊዜ ውስጥ ዳግም ወደነበረበት ሊግ ስለመመለሱ
“የዘንድሮን ውድድር ስንጀምር ጥሩ ነበርን በኋላ ላይ ግን የውጤት መንሸራተቱ መጣና ሊበላሽብን ቻለ፤ በኋላም ላይ ከባድ ጊዜን አሳለፍንና ከቤቲኪንጉ ወረድን፤ ይህ ውጤትም ሲገጥመን በቃ የታሪክ ተወቃሽ ልንሆን ነው ብለን እያሰብን በነበርንበት ሰዓት ወደነበርንበት ሊግ ሊመልሰን የሚያስችል አንድ የውድድር እድል ሊፈጠርልን ቻለና በዓላ እርዳታ በዛ ተጠቃሚ ሆነን ተመልሰን ሊጉን ልንቀላቀል ቻልን በዚህም ልንደሰት ቻልን”፡፡
መጀመሪያ የመውረዳችሁ ሚስጥር ምን ነበር፤ ዳግምስ ወደ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ እንደምትመለሱ እርግጠኞች ነበራችሁ
“የእኛ የመውረድ ሚስጥር በእግር ኳስ የሚያጋጥም ነው፤ ከግማሽ የውድድር ዘመን በኋላ ጥሩ አልነበርንም፤ ያም ነው የጎዳን ከወረድን በኋላም ዳግም ወደ ሊጉ የምንመለስበት የመጫወት እድልን ስናገኝም ሁላችንም የቁጭት ስሜት ነበርና በዛ ውስጥ ሆነን በመጫወት ነው በሙሉ ልብ ሊጉን በድጋሚ እንደምንቀላቀል እርግጣኛ ለመሆን የቻልነውና ያን ልነሳካው ችለናል”፡፡
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ዘንድሮ ጥሩ የውድድር ጊዜን አሳልፎ እንደሆነ
“የሚቀሩኝ ነገሮች ቢኖሩም ካለፈው ዓመት አኳያ ሲታይ ዘንድሮ የተሻልኩ ተጨዋች ነበርኩ፤ በመጪው የውድድር ዘመን ደግሞ ከአሁን የበለጠ አቋሜን በሜዳ ላይ አሳያለው”፡፡
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ የመጪው የውድድር ዘመን እሱን የምንመለከትበት ክለብ
“እስካሁን ባለው ሁኔታና አዲስ ነገር ካልተፈጠረ በስተቀር ከወልቂጤ ከተማ ጋር ቀሪ የአንድ ዓመት ውል ስላለብኝ ከእነሱ ጋር ነው የመጪው ዓመት ላይም የቡድናቸው ተጨዋች ሆኜ የምቀጥለው፤ ከዚህ ውጪ የማውቀው ነገር የለኝም”፡፡
በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ በጣም የምትቆጭበት ነገር
“ከኮትዲቯር ጋር ለነበረን የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ለብሔራዊ ቡድን ተመርጬ ከቆየው በኋላ በእግሬ ላይ የደረሰብኝ ጉዳት ከውድድሩ ውጪ እንድሆን ያደረገኝ ሁኔታ በጣም ያስቆጨኛል”፡፡
ዋልያዎቹ ለአፍሪካ ዋንጫ ሲያልፉ አንተ በጉዳት አልነበርክም በማለፋቸው ዙሪያ ምን አልክ
“ሀገር ከምንም ነገር በላይ ይቀድማልና ዋልያዎቹ ይህን ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማለፍ እልምን ሲያሳኩ በጣም ነው ደስ ያለኝ”፡፡
ዳግም ለብሔራዊ ቡድን ስለመጠራት
“ጠንክረህ ከሰራ ይህን እድል የማታገኝበት ምንም አይነት ምክንያት የለምና በሁሉም ነገር ራሴን አሳምኜው በአዲሱ የውድድር ዘመን ላይ ይህን እድል የማገኘው ይመስለኛል”፡፡
ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ከተጠናቀቀ በኋላ ስላሳለፈው
የእረፍት ጊዜ
“መጀመሪያ ከቤተሰብ ጋር ነው የእረፍት ወቅቴን ያሳለፍኩት፤ ከዛም ወደ ሊጉ ዳግም ለመግባት ለተፈጠረልን ውድድር ወደ ልምምድ ገባውና በዛ ደረጃ ላይ ከቆየው በኋላ ከጓደኞቼ ጋር ኳስን በመጫወት ጊዜውን አሳለፍኩኝ”፡፡
ለአዲስ ከቴ እግር ኳስ ክለብ ማጠናከሪያ ስላደረጉት ውድድር
“በእውነቱ ደስ የሚል ውድድር ነበር፤ የሰውን የኳስ ፍቅርንም በሚገባ ልመለከትበትም ችያለው፤ ድባቡ ያማረ ስለነበርም እንዲህ ያሉ ውድድሮች መዘጋጀታቸው መልካም ነው፤ ለአዘጋጆቹም ትልቅ ምስጋና ነው ያለኝ”፡፡
በመጨረሻ
“ወልቂጤ ከተማን ለእኔ እንደ ቤቴ ያህል የምቆጥረው ክለብ ነው፤ በመጪው የውድድር ዘመን ላይ ከዘንድሮ በተሻለ መልኩም ጥሩ ሆኖ በመቅረብ ስኬታማ ውጤትን ያመጣልና ለእዛ በበቂ ሁኔታ ልንዘጋጅ ይገባል፤ የአዲሱ ዘመን ውድድርም ጥሩ ፉክክክር ይታይበታል”፡፡
አስተያየት ይስጡ