“የድል ውጤቱ ያስፈልገን ስለነበር ተሳክቶልናል”
“እኔ ያስቆጠርኩትን ግብም በፊልም በተደጋጋሚ እንደተመለከትኩት ትክክለኛ ይመስላል”
ፍፁም ገ/ማሪያም /ሰበታ ከተማ/
ባህርዳር ላይ በተጀመረው የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ዛሬ ሰበታ ከተማ ወልቂጤ ከተማን በፍፁም ገብረ ማሪያም ብቸኛ ግብ 1-0 ሊያሸንፍ የቻለ ሲሆን ይህን ጨዋታ አስመልክቶ እና በሜዳ ላይ ስላጨቃጨቁት ጎሎች እንደዚሁም ደግሞ ከቡድናቸው አቋም ጋር በተያያዘ ግብ አስቆጣሪውን ፍፁምን የሀትሪክ ስፖርት ድረ-ገፅ በጋዜጠኛው መሸሻ ወልዴ አማካኝነት አናግሮት ከተጨዋቹ ምላሽ ተሰጥቶታል፤ ተከታተሉት።
ወልቂጤ ከተማን ስላሸነፉበት የዛሬው ጨዋታ
“በባህርዳር ያደረግነው የዛሬው ጨዋታ የሜዳው ሳር አቅምን የሚፈልግ እና ለብዙዎቹ ተጨዋቾችም አዲስ ከመሆኑ አንፃር ከበድ የሚል ግጥሚያ ነበር። በዛ ላይ የእኛ ቡድን አስቀድሞ ውጤቶችን አጥቶ ስለነበር በጫና ውስጥም ያደረግነው ነበር። ያም ሆኖ ግን ይህ ውጤት ለቡድናችን ያስፈልገን ስለነበር በማሸነፋችን ደስ ብሎኛል”።

ወላይታ ዲቻዎች አስቆጥረው ስለተሻረባቸው ግብ እና እሱ አስቆጥሮ ስለፀደቀለት ግብ ጭቅጭቅ ስለማስነሳቱ
“የዳኝነት ውሳኔዎችን በሚመለከት ከዚህ በፊት ባደረግናቸው ጨዋታዎች ላይ የእኛ ቡድን ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ስህተቶች ተፈጥረው ውጤትን ያጣንባቸው ክስተቶች ተፈጥረዋል። በዛሬው ጨዋታም ላይ ወልቂጤዎች ካስቆጠሩት ግብ ጋር በተያያዘ በእንቅስቃሴ ላይ እያሉና በአቋቋም ደረጃም ላይ በተደራቢ ቦታ ላይ የነበረው ተጨዋቻቸው ትክክለኛ ግብ ሊሆን የሚችለውን ኳስ የመስመር ዳኛውን ውሳኔ ያሳተው ያህልም መስሎ ታይቶኛል ያ ካልሆነ ደግሞ ምንአልባት አዲስ ህግ ይኑር ይሁን አላቅም በዛ ምክንያት ጎሉ ተሽራልና ዳኝነቱን በሚመለከት እኔ ብዙ ባልል እና ትክክለኛ ውሳኔውም ከሰሞኑ መታወቅ የማይቀር ነው። እኔ ካስቆጠርኩት ግብ ጋር በተገናኘ ደግሞ እንደ እነሱ ሁሉ ብዙ ስለተባለ ከጨዋታው በኋላ ፊልሙን ደጋግሜ እየተመለከትኩት ነው። ኳሱ ክሮስ ሲደረግ በእኔ ትይዩ የእነሱ አንድ ተጨዋች ነበር። ኳሱ ብረት ገጭቶ ሲመለስ ብዙዎች አጠገቤ ጋር ያሉትን እንጂ ያን ልጅ ስላልተመለከቱት ለዛ ነው ግቤን ከጨዋታ ውጪ ያሉትና ለእኔ ግን አልመሰለኝም”።
ሰበታ ከተማ በሊጉ ላይ ስላለው አቋም
“በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እየተመራ ያለው የዘንድሮው ቡድናችን የአሁን ሰዓት ላይ እየተከተለ ያለው የጨዋታ ታክቲክ እና እሳቤ በአብዛኛው ኳስን ፖሰስ አድርጎ በመጫወት ውጤትን የሚያመጣ አዲስ አይነት የጨዋታ እንቅስቃሴ ስለሆነ ይህን ሜዳ ላይ ሙሉ ለሙሉ ካለመተግበር ጋር በሚፈለገው መልኩ ውጤትን ልናመጣበት ባንችልሞ የተቸገርንበት ሁኔታዎችም ሊኖሩ ቢችሉም በእንቅስቃሴው ዙሪያ ሁላችንም መግባባቱ ላይ ሙሉ ለሙሉ ስንመጣ ግን አጠቃላይ ተጨዋቾቻን ጥሩ ለመጫወት ነፃ የሚወጡበት ሁኔታና እኔም በዚሁ አጨዋወት ውስጥ ጎሎችን እንዳገባም ስለሚያደርገኝ ያንን እንቅስቃሴ እየጠበቅኩት ነው”።
ሰበታ ከተማ ባደረጋቸው የመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች ላይ ተቀይሮ ስለገባባቸው ምክንያቶችና ጎሎችን እያስቆጠረ ስለመሆኑ እንደዚሁም ስለ ቀጣይ ጊዜ ጉዞው
“በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ አርፈን ወደ ዝግጅት ስንገባ በልምምድ ሰዓት ላይ እኔን የጡንቻ መሸማቀቅ /አምስትሪንግ/ ህመም ያጋጥመኝ ስለነበር ለዛ ነው በመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎቻችን ላይ ተቀይሬ እገባ የነበረው። ተቀይሬ ገብቼም ጎል አገባም ነበር። አሁን በቋሚነት ተሰልፌም ጎል እያገባው ነውና ይሄን ጎል ማግባቴን በቀጣይነትም በማስቀጠል ቡድኔን ከጓደኞቼ ጋር ለውጤት የማበቃው ነው የሚሆነው”።

ስለ ተጋጣሚያቸው ወልቂጤ ከተማ
“በጣም ጥሩ ቡድን ነው አላቸው። እንደ እነ አብዱልከሪም ወርቁ እና አሜ መሀመድን የመሳሰሉ በጥራት ደረጃ ሊጠቀሱ የሚችሉ ጥሩ ልጆችንም ቡድኑ ይዟል። እንደ እኛ ሁሉም በአሪፍ ሁኔታም ነው ቡድኑ የተገነባው። የሚከተሉትም አጨዋወት ከእኛ ጋር የሚቀራረብ አይነትም ነውና ተመሳሳይነት ይታይብናል”።
ስለያዙት የተጨዋቾች ስብስብ
“ምርጥ ስብስብ ነው ያለን። አብዛኛዎቹም ወጣቶች እና አዲሶችም ናቸው። ጥሩ አቅም ስላላቸውም ከእኛ ሲኒየር ተጨዋቾች ጋር ተጣምረው ለቡድኑ ውጤት ማማር ብዙ ነገርን ማድረግም የሚችሉ ናቸው”።
ካለፉት ግጥሚያዎቹ አንፃር ሰበታ ከተማ እየተሻሻለ መጥቷል
“አዎን፤ ቡድናችን ተሻሽሏል። በተለይ ደግሞ በራስ መተማመኑ ላይ የጨመረው ነገር አለ። አሁን እርስ በርስ የመላመዱን ነገር እያሳየን ስለሆንም ከዚህ በኋላ ብዙ የምንቸገር አይመስለኝም”

በመጨረሻ
“በቤት ኪንግ ተሳትፎአችን እስካሁን ስኬታማ ውጤትን ላለማምጣታችን ከላይ የገለፅኩት ነገር ቢኖርም ለዛ ምክንያት ከሆኑ ነገሮች ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የዝግጅት ጊዜያችንን ከሌላ ቡድኖች አኳያ በአንድ ወር ያህል ዘግይተን ስለጀመርንና ልንከተለው ካሰብነው አጨዋወት አኳያም በደንብ ሳንቀናጅ ቶሎ ወደ ውድድር ውስጥ በመግባታችን እንቅስቃሴያችንም ቅርፅ እንዳይኖረው ስላደረገብን እና ከዛ ሌላም በቡድኑ ውስጥ ከደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ሳይፈቱ የነበሩ ችግሮች ስለነበሩና ያም አሁን ላይ ሊፈታ በመቻሉ ነው። ከዛ ሌላ የሀገራችን እግር ኳስ በዲኤስቲቪ መተላለፍ መቻሉ ሊጉን አንድ ደረጃ ወደ ላይ ከፍ ያደርገዋል ብዬ ተስፋን ሰንቄያለው። ጨዋታዎቹ እየተላለፉ መሆኑም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ዙሪያ ሰዉ ላይ የነበረውን አመለካከት ቀይሮታል። ይህ እንዳለ ሆኖ የሊጉ ሁሉም ተጨዋቾችም በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ በትልቅነቱ በሚነገርለት የዲኤስቲቪ ቻናል ራሱን የሚያስመለክትበት ሁኔታንም ፈጥሮለታልና ይሄ በጣም አስደሳች ነው”።
አስተያየት ይስጡ